በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 49፥10 ምእመናን ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ! ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡
إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ فَأَصْلِحُوا بَيْنَ أَخَوَيْكُمْ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ

"ኢስላሕ" إِصْلَاح የሚለው ቃል "አስለሐ" أَصْلَحَ‎ ማለትም "አስታረቀ" "አስማማ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ማስታረቅ" "ማስማማት" ማለት ነው፦

ቁርኣን 4፥114 ከውይይታቸው በምጽዋት ወይም በበጎ ሥራ ወይም በሰዎች መካከል በማስታረቅ ከሚያዙ ሰዎች ውይይት በስተቀር በብዙው ውስጥ ደግ ነገር የለበትም፡፡ የአላህን ውዴታ ለመፈለግ ይህንን የሚሠራ ሰው ታላቅ ምንዳን እንሰጠዋለን፡፡
لَّا خَيْرَ فِي كَثِيرٍ مِّن نَّجْوَاهُمْ إِلَّا مَنْ أَمَرَ بِصَدَقَةٍ أَوْ مَعْرُوفٍ أَوْ إِصْلَاحٍ بَيْنَ النَّاسِ ۚ وَمَن يَفْعَلْ ذَٰلِكَ ابْتِغَاءَ مَرْضَاتِ اللَّهِ فَسَوْفَ نُؤْتِيهِ أَجْرًا عَظِيمًا

እዚህ አንቀጽ ላይ "ማስታረቅ" ለሚለው የገባው ቃል "ኢሥላሕ" إِصْلَاح ሲሆን የአሏህ ውዴታ ለመፈለግ የሚያስታርቅ ሰው ታላቅ ምንዳ አለው። የማስታረቅ ምንዳ ከሶላት፣ ከሲያም እና ከሶደቃህ በላጭ ነው፦

ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 43, ሐዲስ 147
አቢ አድ-ደርዳህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ከሶላት፣ ከሲያም እና ከሶደቃህ ደረጃ በላጭ ነገር አልነግራችሁምን? ሶሓባዎችም፦ "እንዴታ" አሉ። እርሳቸውም፦ "በሰዎች መካካል ማስታረቅ ነው፥ በሰዎች መካከል የሚያበላሹ(የሚያጣሉ) ግን አጥፊዎች ናቸው" አሉ"።
عَنْ أَبِي الدَّرْدَاءِ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏"‏ أَلاَ أُخْبِرُكُمْ بِأَفْضَلَ مِنْ دَرَجَةِ الصِّيَامِ وَالصَّلاَةِ وَالصَّدَقَةِ ‏"‏ ‏.‏ قَالُوا بَلَى ‏.‏ قَالَ ‏"‏ إِصْلاَحُ ذَاتِ الْبَيْنِ وَفَسَادُ ذَاتِ الْبَيْنِ الْحَالِقَةُ ‏"‏ ‏.‏

ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት የማይሆን ነው፥ ማስታረቅ ብዙዎች የዘነጋነው ኸይር ሥራ ነው። ሙእሚን የሆኑ ሁለት ወንድሞቻችን ቢቀያየሙ ማስታረቅ ፈርድ ነው፦

ቁርኣን 49፥10 ምእመናን ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ! ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡
إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ فَأَصْلِحُوا بَيْنَ أَخَوَيْكُمْ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "አስታርቁ" ለሚለው ትእዛዛዊ ግሥ የገባው ቃል "አስሊሑ" أَصْلِحُوا መሆኑ በራሱ ማስታረቅ ፈርድ ነው። ከወንድማማችነት በላይ ሁለት ጭፍሮች ቢጋደሉ በመካከላቸው ማስታረቅ ፈርድ ነው፦

ቁርኣን 49፥9 ከምእምናን የኾኑ ሁለት ጭፍሮች ቢጋደሉ በመካከላቸው አስታርቁ፡፡ ከሁለቱ አንደኛይቱም በሌላይቱ ላይ ወሰን ብታልፍ ያችን ወሰን የምታልፈውን ወደ አላህ ትዕዛዝ እስከምትመለስ ድረስ ተጋደሉ፡፡
وَإِن طَائِفَتَانِ مِنَ الْمُؤْمِنِينَ اقْتَتَلُوا فَأَصْلِحُوا بَيْنَهُمَا ۖ فَإِن بَغَتْ إِحْدَاهُمَا عَلَى الْأُخْرَىٰ فَقَاتِلُوا الَّتِي تَبْغِي حَتَّىٰ تَفِيءَ إِلَىٰ أَمْرِ اللَّهِ

"ወሰን አትለፉ" ወደሚለው ወደ አሏህ ትእዛዝ ከተመለሱ ስናስታርቅ ሳናዳላ በፍትሕ ማስታረቅ አለብን፦

ቁርኣን 49፥9 ብትመለስም በመካከላቸው በትክክል አስታርቁ፡፡ በነገሩ ሁሉ አስተካክሉም፡፡ አላህ አስተካካዮችን ይወዳልና፡፡
فَإِن فَاءَتْ فَأَصْلِحُوا بَيْنَهُمَا بِالْعَدْلِ وَأَقْسِطُوا ۖ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ الْمُقْسِطِينَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ትክክል" ለሚለው የገባው ቃል "ዐድል" عَدْل ሲሆን በነገሩ ሁሉ በፍትሕ ማስተካከል ግዴታ ነው፥ አሏህ አስተካካዮችን ይወዳልና። ያስታረቀ ሰው አሏህ ዘንድ ምንዳው ያለ ግምት ነው፦

ቁርኣን 42፥40 ይቅርም ያለ እና ያስታረቀ ሰው ምንዳው በአላህ ላይ ነው፡፡
فَمَنْ عَفَا وَأَصْلَحَ فَأَجْرُهُ عَلَى اللَّهِ

ምንዳው ያለ ግምት የሆነው አስታራቂ ብቻ ሳይሆን ተበድሎ ይቅር ያለ ሰውም ጭምር ነው። ጀነት ከሰዎችም ይቅርባዮች ለኾኑት ተደግሳለች፦

ቁርኣን 3፥134 ለእነዚያ በድሎትም ኾነ በችግር ለሚለግሱት፣ ቁጭትንም ገቺዎች ከሰዎችም ይቅርታ አድራጊዎች ለኾኑት ተደግሳለች፡፡
ٱلَّذِينَ يُنفِقُونَ فِى ٱلسَّرَّآءِ وَٱلضَّرَّآءِ وَٱلْكَٰظِمِينَ ٱلْغَيْظَ وَٱلْعَافِينَ عَنِ ٱلنَّاسِ
ቁርኣን 42፥37 ለእነዚያም የኀጢኣትን ታላላቆች እና ጠያፎችን የሚርቁ በተቆጡም ጊዜ እነርሱ ይቅር የሚሉ ለኾኑት፡፡
وَٱلَّذِينَ يَجْتَنِبُونَ كَبَٰٓئِرَ ٱلْإِثْمِ وَٱلْفَوَٰحِشَ وَإِذَا مَا غَضِبُوا۟ هُمْ يَغْفِرُونَ

የተጣላ ሰውም አስታራቂ መጥቶ "ታረቁ" ሲል መታረቅ አለብን፥ መታረቅ መልካም ነው። የበደለንን ይቅርታ ሲጠይቅ ይቅር ማለት አሏህ ወንጀላችንን ይቅር ይለናል፦

ቁርኣን 4፥128 መታረቅ መልካም ነው፡፡
وَالصُّلْحُ خَيْرٌ
ቁርኣን 4፥149 ደግ ነገርን ብትገልጹ ወይም ብትደብቁት ወይም "ከበደል ይቅርታ ብታደርጉ" አላህ ይቅር ባይ ኃያል ነው፡፡
إِن تُبْدُوا۟ خَيْرًا أَوْ تُخْفُوهُ أَوْ تَعْفُوا۟ عَن سُوٓءٍۢ فَإِنَّ ٱللَّهَ كَانَ عَفُوًّۭا قَدِيرًا
ቁርኣን 2፥263 መልካም ንግግር እና ይቅርባይነት ማስከፋት ከሚከተላት ምጽዋት በላጭ ነው፡፡ አላህም ተብቃቂ ታጋሽ ነው፡፡
قَوْلٌۭ مَّعْرُوفٌۭ وَمَغْفِرَةٌ خَيْرٌۭ مِّن صَدَقَةٍۢ يَتْبَعُهَآ أَذًۭى ۗ وَٱللَّهُ غَنِىٌّ حَلِيمٌۭ

ይቅርባይነት ማስከፋት ከሚከተላት ሶደቃህ በላጭ ነው። ቂም፣ ቁርሾ እና በቀል ልብ ውስጥ ሲቀመጥ ግን የሚጎዳው በቂም ያቄምንበትን፣ በቁርሾ ያቀረሸንበት፣ በበቀል የምንበቀለውን ሰው ብቻ ሳይሆን እራሳችንንም ጭምር ነው። ቂም፣ ቁርሾ እና በቀል በልብ ውስጥ ማስቀመጥ ኪሳራ እና ጉዳት እንጂ ትርፍ እና ጥቅም የለውም፦

ቁርኣን 35፥10 እነዚያም መጥፎ ሥራዎችን የሚዶልቱ ለእነርሱ ብርቱ ቅጣት አላቸው፡፡ የእነዚያም ተንኮል እርሱ ይጠፋል፡፡
وَٱلَّذِينَ يَمْكُرُونَ ٱلسَّيِّـَٔاتِ لَهُمْ عَذَابٌۭ شَدِيدٌۭ ۖ وَمَكْرُ أُو۟لَٰٓئِكَ هُوَ يَبُورُ

ነገርን በማብረድ ከማስታረቅ ይልቅ በማንደድ ሰዎችን የሚያነካክሱ እና የሚያባሉ አጥፊዎች ናቸው። እነዚህ ወሬ የሚያዋስዱ ሰዎች ወንጀሉ ከፍተኛ ስለሆነ ጀነት አይገቡም፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 1 ሐዲስ 196
ሑዘይፋህ የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ ሲሉ ሰምቶ አስተላልፏል፦ "ነገር አዋሳጅ ጀነት አይገባም"።
فَقَالَ حُذَيْفَةُ سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم يَقُولُ ‏ "‏ لاَ يَدْخُلُ الْجَنَّةَ نَمَّامٌ ‏"‏

አምላካችን አሏህ ወሬ አዋሳጆች ከመሆን ይጠብቀን! አታራቂዎች እና ይቅርባዮች ከሚላቸው ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

✍ከዐቃቤ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም