በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 29፥46 በሉም «በዚያ ወደኛ በተወረደው ወደ እናንተም በተወረደው አመንን፡፡ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፡፡ እኛም ለእርሱ ታዛዦች ነን፡፡»
وَقُولُوا آمَنَّا بِالَّذِي أُنزِلَ إِلَيْنَا وَأُنزِلَ إِلَيْكُمْ وَإِلَـٰهُنَا وَإِلَـٰهُكُمْ وَاحِدٌ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ
"አህለል ኪታብ" أَهْلَ الْكِتَاب ማለት "የመጽሐፉ ባለቤቶች" ማለት ሲሆን እነዚህም አይሁዳውያን እና ክርስቲያኖች ናቸው፥ እኛ ሙሥሊሞችን እና እነርሱን የፈጠረ አምላካችን አንድ አምላክ ነው፦
ቁርኣን 29፥46 የመጽሐፉን ባለቤቶችም በዚያች እርሷ መልካም በኾነችው ክርክር እንጂ አትከራከሩ፡፡ ከእነርሱ እነዚያን የበደሉትን ሲቀር፡፡ በሉም «በዚያ ወደኛ በተወረደው ወደ እናንተም በተወረደው አመንን፡፡ አምላካችንም አምላካችሁም አንድ ነው፡፡ እኛም ለእርሱ ታዛዦች ነን፡፡»
وَلَا تُجَادِلُوا أَهْلَ الْكِتَابِ إِلَّا بِالَّتِي هِيَ أَحْسَنُ إِلَّا الَّذِينَ ظَلَمُوا مِنْهُمْ ۖ وَقُولُوا آمَنَّا بِالَّذِي أُنزِلَ إِلَيْنَا وَأُنزِلَ إِلَيْكُمْ وَإِلَـٰهُنَا وَإِلَـٰهُكُمْ وَاحِدٌ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ
በእኛ እና በእርሱ መካከል ትክክል ወደ የሆነች ቃል 'ተውሒድ" ናት፥ ነገር ግን ክርስቲያኖች አንድ በሚለው ቃል ላይ ሦስት በማለት ተሥሊሥን ጨምረዋል። አይሁዳውያን ግን እስካሁን የሚያመልኩት አንድ አምላክን ነው፥ አይሁዳውያን አሏህ አንድ አምላክ እንደሆነ ብቻ ያምናሉ። መሢሑ ደግሞ ከዳዊት ዘር የሚመጣ የአሏህ ነቢይ እንጂ አሏህ ጋር አብሮ የሚኖር ወይም አሏህ ነው ብለው አያምኑም፥ እኛም ይህ መሢሕ ኢየሱስ ሲሆን ከዳዊት ዘር የሚመጣ የአሏህ ነቢይ እንጂ አሏህ ጋር አብሮ የሚኖር ወይም አሏህ ነው ብለን አናምንም።
እኛ እና አይሁዳውያን ልዩነታችን ምንድን ነው ታዲያ? ከተባለ፦
1ኛ. አይሁዳውያን በነቢያችን"ﷺ" ነቢይነት እና ቁርኣን የአሏህ ቃል መሆኑን አያምኑም።
2ኛ. "ኢየሱስ መሢሕ ነው" ብለው ከማመን ይልቅ "ሐሠተኛ ነቢይ፣ የዝሙተኛ ልጅ፣ ዕብድ ነው" ብለው ያምናሉ።
3ኛ. ሊቃውንቶቻቸው ባወጡላቸው ሰውኛ ሸሪዓህ ሐራሙን ሐላል፣ መክሩሕ የሆነውን ሙሥተሐብ፣ ሙባሕ የሆነው ፈርድ እያረጉ በአሏህ ጌትነት ላይ ሊቃውንቶቻቸውን አርባብ በማድረግ አሻርከዋል።
አይሁዳውያን እኛን የሚጠሉን በተውሒድ አር-ሩቡቢያህ ነው እንጂ የአብርሃምን አምላክ በብቸኝነት እንደምናመልክ ጠንቅቀው ያውቃሉ። አንድ ጊዜ አንድ ራባይ(የአይሁድ መምህር) ሲነግረኝ፦ "ሙሥሊሞች በምኩራባችን ገብተው ሶላት መቆም ይችላሉ፥ ነገር ግን ክርስቲያኖች ሦስት አካላትን ስለሚያመልኩ ለክርስቲያኖች አይፈቀድም። አንድ አይሁድ የጸሎት ሰዓት ደርሶበት መሥጂድ ገብቶ መጸለይ ይፈቀድለታል፥ ቤተክርስቲያን ውስጥ ግን አይፈቀድለትም" አለኝ፥ ለምን ስለው "ሙሥሊሞች የምታመልኩት በአንድነቱ ሦስትነት የሌለበትን ነው" አለኝ።
በእርግጥ ቪድዮ ላይ የምትመለከቱት ራባይ፦ "አሏህ በሁሉም ጊዜ የነበረ ቃል ነው። እኛ ከዐረብ ጋር ተመሳሳይ አምላክ አለን፥ ተመሳሳይ በሆነ በአንድ አምላክ እናምናለን። ይህ እንቆቅልሽ ነው፥ ክርስቲያኖች በሥላሴ ያምናሉ። ነገር ግን የክርስቲያኖች አምላካቸው አይሁዳውያን የሚጠሩት የዛ ክፍል ነውን? ያ የእኛ እምነት አይደለም። እንደዛ(እንደ ሥላሴ) እንድናምን አልተፈቀደልንም፥ በአጠቃላይ እኛ በክርስቲያን አስተሳሰብ ከዐረቦች እንሻላለን፥ በጥቅሉ ሲናገሩ። ነገር ግን የጋራ ነጥብ ያለን ከዐረቦች ጋር ነው፥ ተመሳሳይ አምላክ አለን ብለን የምናምነው ከዐረቦች ጋር ነው" ብሏል። አንዱ ጠያቂም፦ "ሙሥሊም የአምላክን ስም ለይተዋልን? ለውጠዋልን? ብሎ ጠየቀ፥ ራባዩ፦ "የአምላክን ስም አለወጡም፥ አሏህ እኮ በተመሳሳይ "አለካህ" ነው። ለምን ይቀይራሉ? ከአብርሃም እና ከእስማኤል ልጆች የመጡ ናቸው፥ እኛ ከይስሐቅ መጣን እነርሱ ከእስማኤል መጡ" በማለት ተናግረዋል።
እርግጥ ነው! ከአይሁዳውያን ዳራ የመጡት ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ ሥላሴን አላስተማሩም፥ ተውሒድን ብቻ አስተምረዋል። ክርስቲያኖች ሥላሴን የቀየጡት ከግሪክ እና ከሮም ጋር ለመመሳሰል ነው፥ ሥላሴ ለአይሁዳውያን እንግዳ እና ባዕድ ትምህርት ነው። እስራኤላውያን የሚያመልኩት አንድ ማንነት እና ምንነት የሆነ አምላክ ነው፥ ከዚህ ውጪ እነርሱ የማያውቁት የሥላሴ ትምህርት ማሳሳቻ ነው፦
ዘዳግም 13፥6 አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት "እናምልክ" ብሎ ቢያስትህ እሺ አትበለው።
"አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን" የሚለው ይሰመርበት! ሥላሴን አይሁዳውያን አያውቁትም። አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም