በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 4፥71 የመርየም ልጅ አል-መሢሕ ዒሣ የአላህ መልእክተኛ ብቻ ነው።
إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللَّهِ

"ረሡል" رَسُول የሚለው ቃል "አርሠለ" أَرْسَلَ ማለትም "ላከ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መልእክተኛ" ማለት ነው፥ "ሪሣላህ" ማለት "መልእክት" ማለት ሲሆን "ሙርሢል” مُرْسِل ማለት ደግሞ "ላኪ" ማለት ነው። አምላካችን አሏህ "ሙርሢል" ሲሆን ዒሣ ኢብኑ መርየም ደግሞ "ረሡል" ነው፦

ቁርኣን 4፥71 የመርየም ልጅ አል-መሢሕ ዒሣ የአላህ መልእክተኛ ብቻ ነው።
إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللَّهِ

አሏህ ለዒሣ እንዲያስተላልፍ የሰጠው "ሪሣላህ" ኢንጂል ነው፥ መልእክተኛ የራሱ ሙሉ ዕውቀት ስለሌለው የላከው ዕውቀት የሚያስለላልፍ ነው።
ወደ ባይብል ስንመጣ ኢየሱስ የአንዱ አምላክ መልእክተኛ ስለሆነ አንዱ አምላክ ለኢየሱስ እንዲያስተላልፍ መልእክት ሰቶታል፦

ዮሐንስ 17፥8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና።

"የሰጠኸኝን ቃል" የሚለው ይሰመርበት! ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ቃል አለው፥ ይህን የዘለዓለም ሕይወት ቃል የሚሰጠው አብ እንዲሰጥ ሥልጣን ስለሰጠው እንጂ እርሱ ከራሱ ምንም ማድረግ አይችልም፦

ዮሐንስ 6፥68 አንተ "የዘላለም ሕይወት ቃል" አለህ።
ዮሐንስ 12፥49 እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና፤ ነገር ግን የላከኝ አብ እርሱ የምለውን የምናገረውንም "ትእዛዝ ሰጠኝ"።
ዮሐንስ 12፥50 "ትእዛዙም የዘላለም ሕይወት እንደ ሆነች" አውቃለሁ። ስለዚህ እኔ የምናገረውን አብ እንደ ነገረኝ እንዲሁ እናገራለሁ።

ኢየሱስ የሚለው እና የሚናገረው ከራሱ ካልሆነ እና የሚለው እና የሚናገረው ትእዛዙ የላከው ከሰጠው ያ የተሰጠው ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት ነው። የዘላለም ሕይወትን የሆነውን ይህንን ትእዛዝ ለአማኞች እንዲሰጥ ሥልጣን የሰጠው አብ ነው፦

ዮሐንስ 17፥2 በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።

የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ሥልጣን ከተሰጠው ይህም የዘላለም ሕይወት ዕውቀት እንደሆነ ዐውደ ንባቡ ይናገራል፦

ዮሐንስ 17፥3 እውነተኛ አምላክ ብቻህን የሆንህ አንተን እና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።
αὕτη δέ ἐστιν ἡ αἰώνιος ζωή, ἵνα γινώσκωσιν σὲ τὸν μόνον ἀληθινὸν θεὸν καὶ ὃν ἀπέστειλας Ἰησοῦν Χριστόν.
1ኛ ዮሐንስ 5፥20 የአምላክም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ መረዳት እንደ ሰጠን እናውቃለን።
οἴδαμεν δὲ ὅτι ὁ Υἱὸς τοῦ Θεοῦ ἥκει, καὶ δέδωκεν ἡμῖν διάνοιαν ἵνα γινώσκομεν τὸν ἀληθινόν·

"ይህቺ" ተብሎ በአምልካች ተውላጠ ስም የተቀመጠው የዘላለም ሕይወት አብን ብቻውን እውነተኛ አምላክ መሆኑን እና ኢየሱስ የእውነተኛው አምላክ መልእክተኛ መሆኑን "ማወቅ" ነው። በዚህም መልእክተኛው ወልድ እውነተኛ አምላክን የሆነውን አብን ለማወቅ መረዳት(ዕውቀት) ሰጥቷል፥ "እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ መረዳት እንደ ሰጠን እናውቃለን" የሚለው ይህንኑ ነው። ኢየሱስ ከአብ የሰማውን ዕውቀት አስታውቋል፦

ዮሐንስ 15፥15 ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።

ኢየሱስ፦ "ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ" በሚል ኃይለ ቃል ውስጥ "ለሰጠኸው" ሲል ከአብ ለወልድ የተሰጡት አማኞች ናቸው፦

ዮሐንስ 10፥29 "የሰጠኝ" አባቴ ከሁሉ ይበልጣል።
ዮሐንስ 17፥6 ከዓለም "ለሰጠኸኝ ሰዎች" ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም "ሰጠሃቸው"።

ኢየሱስ ከአብ የተሰጠውን ቃል፣ ትእዛዝ፣ ዕውቀት ለአማኞችም ስለሚሰጥ "ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ" ማለቱ ይህንን ታሳቢ እና ዋቢ ያደረገ ነው፦

ዮሐንስ 10፥28 እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ።

"ለበሬ ሁሉ ነገር ጭድ ይመስለዋል" ለየት ያለ ጥቅስ ሲገኝ ጎትጉቶ እና ጎትቶ ለኢየሱስ አምላክነት መደረብ ሚሽነሪዎች ዋንጫ የወስዱበት ጉዳይ ነው፥ በድፍ ቅል ጉሳንጉስ የሥነ መለኮት ቅመራ ከመቀመር ይልቅ ማጥናት ይገባል። "የዘላለም ሕይወት" የተባለው ቃል፣ ትእዛዝ፣ ዕውቀት እንደሆነ ከተረዳን ዘንዳ ይህንን የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ሥልጣን ተሰቶታል እንጂ ኢየሱስ ከራሱ ምንም ነገር ማድረግ አይችልም፦

ዮሐንስ 5፥30 እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም።

"እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም" "እኔ ከራሴ አልተናገርሁምና" ካለ እርሱ የዘላለምን ሕይወት የሆነውን መልእክት ከላኪው ከአብ እንዲያስተላልፍ ሥልጣን የተሰጠው መልእክተኛ ብቻ ነው፥ ኢየሱስ "እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ" ብሎ የተናገውን ንግግር ይዞ ለአምላክነት መሞገት ዛብ የሌለው ፈረሰኛ ምሳ የሌለው ኮሰኛ ነውና ሙግቱ ያልፋፋ እና ያልዳበረ ሙግት ነው። ይህንን ሰው የሆነ መልእክተኛ የምታመልኩ አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም