በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

22፥75 አሏህ ከመላእክት ውስጥ መልእክተኞችን ይመርጣል፥ ከሰዎችም እንደዚሁ ይመርጣል። አሏህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡
اللَّهُ يَصْطَفِي مِنَ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا وَمِنَ النَّاسِ ۚ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ بَصِيرٌ

"የሰውን ልጅ የሚመስል" የሚል ቃል እንደየ ዐውዱ ለተለያየ ፍጡር ይውላል፥ ለምሳሌ፦ ለዳንኤል የተገለጠለት መልአክ "የሰው ልጅ የሚመስል" ተብሎአል፦

ዳንኤል 10፥16 እነሆም "የሰው ልጅ የሚመስል" ከንፈሬን ዳሰሰኝ።

ራእይ ላይም አንድ በስም ያልተገለጠ መልአክ "የሰውን ልጅ የሚመስል" ተብሎአል፦

ራእይ 14፥14 አየሁም እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ "የሰውን ልጅ የሚመስል" ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው።

ይህ መልአክ በስም ያልተገለጠ ፍጡር መሆኑን የምናውቀው ሌላ ፍጡር መልአክ በትእዛዛዊ ግሥ፦ "ስደድ" "እጨድ" ብሎ ያዘዋል፦

ራእይ 14፥15 "ሌላ" መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፦ "የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድ እና እጨድ! የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና" ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። Καὶ ἄλλος ἄγγελος ἐξῆλθεν ἐκ τοῦ ναοῦ, κράζων ἐν φωνῇ μεγάλῃ τῷ καθημένῳ ἐπὶ τῆς νεφέλης Πέμψον τὸ δρέπανόν σου καὶ θέρισον, ὅτι ἦλθεν ἡ ὥρα θερίσαι, ὅτι ἐξηράνθη ὁ θερισμὸς τῆς γῆς.

እዚህ አንቀጽ "ሌላ" የሚለው የገባው ቃል "አሎስ" ἄλλος ሲሆን "ሌላ ተመሳሳይ ዓይነት"Another the same kind" ማለት ነው፥ ስለዚህ ታዛዡ መልአክ እና አዛዡ መልአክ ሁለቱም ተመሳሳይ ተፈጥሮ ያላቸው ፍጡራን መላእክት ናቸው። "ሄቴሮስ" ἕτερος እራሱ ተመሳሳይ ተፈጥሮ ላላቸው ይገባል፦

ማቴዎስ 8፥21 ከደቀ መዛሙርቱም "ሌላው"፦ “ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፡” አለው። ἕτερος δὲ τῶν μαθητῶν εἶπεν αὐτῷ Κύριε, ἐπίτρεψόν μοι πρῶτον ἀπελθεῖν καὶ θάψαι τὸν πατέρα μου.

"ሄቴሮስ" ἕτερος በብሉይ ኪዳን ግሪክ ሰፕቱአጀንት ላይ ተመሳሳይ ተፈጥሮ ላላቸው ውሏል፥ ዘፍጥረት 29፥10 ዘፍጥረት 30፥24 ተመልከት!ይህንን ከተረዳን ዘንዳ ዘካሪያስ ጋር የመጡት ሁለት መላእክት ተመሳሳይ ተፈጥሮ ያላቸው ፍጡራን መላእክት ናቸው፦

ዘካርያስ 2፥3 እነሆም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው "መልአክ" ወጣ፥ "ሌላም" መልአክ ሊገናኘው ወጣ።
וְהִנֵּ֗ה הַמַּלְאָ֛ךְ הַדֹּבֵ֥ר בִּ֖י יֹצֵ֑א וּמַלְאָ֣ךְ אַחֵ֔ר יֹצֵ֖א לִקְרָאתֹֽו׃

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሌላ" ለሚለው ገላጭ ቅጽል የገባው ቃል "አኼር" אַחֵ֔ר ሲሆን ሁለቱም ተመሳሳይ ተፈጥሮ ያላቸው ፍጡራን መላእክት መሆናቸውን አመላካች ነው፥ "ሌላ ሰው ይመጣል" ብል ፊተኛው ሰው እና ሌላው ሰው ተመሳሳይ ተፈጥሮ ያላቸው ፍጡራን ሰዎች አመላካች እንደሆነው ማለት ነው። ሌላይኛው መልአክ ፊተኛውን መልአክ፦ "ሩጥ" "በለው" በማለት በትእዛዛዊ ግሥ ያዘዋል፦

ዘካርያስ 2፥4 እንዲህም አለው፦ “ሩጥ፥ ይህንም ጕልማሳ እንዲህ በለው፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎች እና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች"።

"እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ" ባዩ ያህዌህ ስለሆነ ሁለተኛው መልአክ፦ "እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ" ይላል ያህዌህ" በማለት ይናገራል፦

ዘካርያስ 2፥5 "እኔ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ፥ በውስጥዋም ክብርን እሆናለሁ" ይላል ያህዌህ።

ሁለተኛው መልአክ "ይላል ያህዌህ" ማለቱ በራሱ ያህዌህ ሲናገር የሚያስተላልፍ ፍጡር መልአክ መሆኑ ቁልጭ እና ፍንትው አርጎ ያሳያል፥ መልአኩም፦ "አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ! ኰብልዪ" ያህዌህ እንዳለ ይነግረናል፦

ዘካርያስ 2፥7 “አንቺ ከባቢሎን ሴት ልጅ ጋር የምትኖሪ ጽዮን ሆይ! ኰብልዪ” እንዲህ ይላልና ጸባዖት ያህዌህ። הֹ֥וי צִיֹּ֖ון הִמָּלְטִ֑י יֹושֶׁ֖בֶת בַּת־בָּבֶֽל׃ ס כִּ֣י כֹ֣ה אָמַר֮ יְהוָ֣ה צְבָאֹות֒

"እንዲህ ይላልና ጸባዖት ያህዌህ" ቁጥር 8 ላይ ቢኖርም ቁጥር 7 ላይ ያለውን መልአኩ "ይላልና" በማለት እየተናገረ ነው፥ መልአኩ በመቀጠል፦ "ልኮኛል" በማለት የያህዌህ መልእክተኛ መሆኑን ይናገራል፦

ዘካርያስ 2፥8 ከክብሩ በኋላ ወደ በዘበዙአችሁ አሕዛብ "ልኮኛል"፤ የሚነካችሁ የዓይኑን ብሌን የሚነካ ነውና።
ዘካርያስ 2፥9 እነሆ እጄን በላያቸው አወዛውዛለሁ፥ ተገዝተው ለነበሩት ብዝበዛ ይሆናሉ፤ ጸባዖት ያህዌም እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።

"ጸባዖት" የሚለው የግዕዝ ቃል "ሰባኡት" צְבָא֖וֹת ከሚል የዕብራይስጥ የተገኘ ሲሆን "ሠራዊት" ማለት ነው፥ ያህዌህ የሠራዊቱ የመላእክት ጌታ መሆኑን ለማሳየት የገባ ነው። መልአኩም "ይላል ያህዌህ" በማለት ንግግሩን ይቀጥላል፦

ዘካርያስ 2፥10 "የጽዮን ልጅ ሆይ! እነሆ መጥቼ በመካከልሽ እኖራለሁና ዘምሪ ደስም ይበልሽ" ይላል ያህዌህ።

"በመካከልሽ እኖራለሁ" የሚለው ያህዌህ ነው፥ በቀጣይ "በመካከልሽም እኖራለሁ" የሚለው ሁለተኛው ፍጡር መልአክ ነው፦

ዘካርያስ 2፥11 በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ ያህዌህ ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ ጸባዖት ያህዌህም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ።

ይህ የሚያሳየው መልአኩ ያህዌህ መሆኑን ሳይሆን የያህዌህ መልአክ የያህዌህ ወኪል፣ ልኡክ፣ እንደራሴ መሆኑን ነው። ለምሳሌ፦ የያህዌህ ታቦት የሰው እጅ ሥራ ፍጡር ነው፥ ግን ታቦቱ የያህዌህ መገኘት እንደ ራሴ ነው፦

2ኛ ሳሙኤል 7፥2 ንጉሡ ነቢዩን ናታንን፦ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የያህዌህ ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ "ተቀመጠ" እይ" አለው።

በመጋረጃ ድንኳን የተቀመጠው የያህዌህ ታቦት ሆኖ ሳለ ያህዌህ ግን "በድንኳን እና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት "አልተቀመጥሁምና" ብሎአል፦

2ኛ ሳሙኤል 7፥5 ሂድ፥ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው፦ ያህዌህ እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳን እና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት "አልተቀመጥሁምና" አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም"።

የያህዌህ ታቦት የያህዌህ መገኘት እንጂ ታቦቱ ያህዌህ እንዳልሆነ ሁሉ የያህዌህ መልአክም የያህዌህ መገኘት እንጂ ያህዌህ በፍጹም አይደለም። የያህዌህ ታቦት ወደ ሰፈሩ በገባ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን፦ "አምላክ ወደ ሰፈሩ ገብቷል" አሉ፦

1 ሳሙኤል 4፥6 የያህዌህም ታቦት ወደ ሰፈሩ እንደገባ አስተዋሉ። וַיֵּ֣דְע֔וּ כִּ֚י אֲרֹ֣ון יְהוָ֔ה בָּ֖א אֶל־הַֽמַּחֲנֶֽה׃1
ሳሙኤል 4፥7 ፍልስጥኤማውያንም ፈርተው፦ "አምላክ ወደ ሰፈሩ ገብቷል" አሉ። וַיִּֽרְאוּ֙ הַפְּלִשְׁתִּ֔ים כִּ֣י אָמְר֔וּ בָּ֥א אֱלֹהִ֖ים אֶל־הַֽמַּחֲנֶ֑ה

ሁለቱም ጥቅስ ላይ "ገባ" ለሚለው የገባው ቃል "ባ" בָּ֖א ሲሆን "መጣ" ማለት ነው፥ ወደ ሰፈሩ የመጣው ማን ነው? ታቦት ወይስ አምላክ? የታቦቱ መምጣት የአምላክ መምጣት እንጂ ታቦቱ አምላክ ካልሆነ የመልአኩ መኖር የአምላክ መኖር እንጂ መልአኩ አምላክ አይደለም። ሙሴ በታቦቱ መጓዝ እና ማረፍ ጊዜ ያህዌህን ያነጋግር ነበር፦

ዘኍልቍ 10፥35 ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ፦ ያህዌህ ሆይ! ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ" ይል ነበር። ባረፈም ጊዜ፦ ያህዌህ ሆይ! ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ" ይል ነበር።

ሙሴ "ተነሳ" "ተመለስ" እያለ በሁለተኛ መደብ ታቦቱን አላኮ እና አስታኮ መናገሩ ታቦቱ ያህዌህ ነው ወይስ የያህዌህ ነው? ታቦቱ እኮ የሙሴ የእጅ ሥራ ነው፦

ዘዳግም 10፥3 ከግራርም እንጨት ታቦትን ሠራሁ።

"መልአክ" በዕብራይስጥ "ማላህ" מֲלְאָךְ ሲሆን "መልእክተኛ" ማለት ነው፥ "መላሆት" מַלְאֲכוּת ማለት "መልእክት" ማለት ሲሆን መልእክተኛው ከላኪው ተቀብሎ የሚናገረው መልእክት የላኪው እስከሆነ ድረስ "በመካከልሽ እኖራለሁ" የሚለውን መልእክት መልአኩ ቢናገርም እንኳን የሚያስረዳው መልአኩ ላኪው ያህዌን መሆኑን ሳይሆን መልአኩ መልእክት አድራሽ መሆኑን ብቻ ነው እንጂ ፍጡር መልአክ ፈጣሪ አይሆንም። ፈጣሪ ፈጣሪ ከላከ ሁለት ፈጣሪ ይሆናልና አያስኬድም፥ ፈጣሪ ግን አንደ ነው። አሏህ ከመላእክት ውስጥ መልእክተኞችን ይመርጣል፦

22፥75 አሏህ ከመላእክት ውስጥ መልእክተኞችን ይመርጣል፥ ከሰዎችም እንደዚሁ ይመርጣል። አሏህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡
اللَّهُ يَصْطَفِي مِنَ الْمَلَائِكَةِ رُسُلًا وَمِنَ النَّاسِ ۚ إِنَّ اللَّهَ سَمِيعٌ بَصِيرٌ

"ለዘካሪያስ የተገለጠው ሁለተኛው መልአክ ኢየሱስ ነው" የሚለው ትምህርት እንዲህ ድባቅ ይገባል፥ ኢየሱስን ብሉይ ኪዳን ላይ አስገብቶ መልአክ የማድረግ አባዜ የተጠናወታቸው ሰዎች ለአሁኑ አልተሳካላቸውም። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

✍️ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሰላሙ አለይኩም