በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 34፥28 አንተንም "ለሰዎች ሁሉ በመላ" አብሳሪ እና አስጠንቃቂ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፡፡
وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِّلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا

"ነዝር" نَذْر የሚለው ቃል "ነዘረ" نَذَرَ ማለትም "አስጠነቀቀ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ማስጠንቀቂያ" ማለት ነው፥ ቁርኣን ማስጠንቀቂያ ሆኖ በነቢያችን"ﷺ" ላይ የተወረደ ነው። አምላካችን አሏህ እርሳቸው፦ "አስጠንቅቅ" በማለት አዟቸዋል፦

ቁርኣን 74፥2 ተነሳና አስጠንቅቅ፡፡
قُمْ فَأَنذِرْ

"አስጠንቅቅ" ለሚለው የገባው ትእዛዛዊ ግሥ "አንዚር" أَنذِرْ ሲሆን ነቢያችን"ﷺ" ማስጠንቀቅ እንዲጀምሩ የታዘዙት ከቅርብ ዘመዳቸው ነው፦

ቁርኣን 26፥214 ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ፡፡
وَأَنذِرْ عَشِيرَتَكَ الْأَقْرَبِينَ

አሏህ፦ "ቅርቦች ዘመዶችህንም አስጠንቅቅ" ስላለ የቁርኣን ማስጠንቀቂያ የመጣው "ለቅርብ ዘመድ ብቻ ነው" የሚል ቂል ከሌለ በተመሳሳይ የቁርኣን ማስጠንቀቂያ የመጣው "ለዐረቦች ብቻ ነው" የሚል ካለ ከቂልም በላይ ቂላቂል ነው፦

ቁርኣን 36፥6 አባቶቻቸው ያልተስጠነቀቁትን ሕዝቦች ልታስጠነቅቅበት ተወረደ፡፡ እነርሱ ዘንጊዎች ናቸውና፡፡
لِتُنذِرَ قَوْمًا مَّا أُنذِرَ آبَاؤُهُمْ فَهُمْ غَافِلُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ብቻ" የሚል ኃይለ-ቃል ሽታው የለም፥ "ኢነማ" إِنَّمَا የሚለው ገላጭ ቅጽል "ብቻ" ማለት ሲሆን ቁርኣን ውስጥ አንጻራዊ ወይም ፍጹማዊ ገደብን ለማሳየት ብዙ ቦታ መጥቷል። ነገር ግን የቁርኣንን መልእክታዊ ማስጠንቀቂያነትን ለመገደብ አንድም ጊዜ መጥቶ አያውቅም፥ ይህንን ከተረዳን ዘንድ ይልቁንስ ነቢያችን"ﷺ" ለአህሉል ኪታብ ማለትም ለአይሁዳውያን እና ለክርስቲያኖችም ጭምር አስጠንቃቂ ሆነው መጥተውላቸዋል፦

ቁርኣን 5፥19 እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! «አብሳሪ እና አስጠንቃቂ አልመጣልንም» እንዳትሉ ከመልእክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሲኾን ሕጋችንን የሚያብራራ ኾኖ መልእክተኛችን በእርግጥ "መጣላችሁ"፡፡ አብሳሪ እና አስጠንቃቂ በእርግጥ "መጣላችሁ"፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
يَا أَهْلَ الْكِتَابِ قَدْ جَاءَكُمْ رَسُولُنَا يُبَيِّنُ لَكُمْ عَلَىٰ فَتْرَةٍ مِّنَ الرُّسُلِ أَن تَقُولُوا مَا جَاءَنَا مِن بَشِيرٍ وَلَا نَذِيرٍ ۖ فَقَدْ جَاءَكُم بَشِيرٌ وَنَذِيرٌ ۗ وَاللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

"ነዚር" نَذِير ማለት "አስጠንቃቂ" ማለት ሲሆን የተወዳጁ ነቢያችንን"ﷺ" ማስጠንቀቂያ ሰምቶ ያስተባበለ የአይሁድ ሆነ የክርስቲያን ሕዝብ የእሳት ጓድ እንጂ ሌላ አይሆንም፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 1, ሐዲስ 292
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንዳስተላለፈው የአሏህ መልክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነችው እምላለው፥ የአይሁድ ሆነ የክርስቲያን ሕዝብ የእኔን መላክ ሰምቶ ሳያምን ቢሞት የእሳት ጓድ እንጂ ሌላ አይሆንም"።
حَدَّثَهُ عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، عَنْ رَسُولِ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم أَنَّهُ قَالَ ‏ “‏ وَالَّذِي نَفْسُ مُحَمَّدٍ بِيَدِهِ لاَ يَسْمَعُ بِي أَحَدٌ مِنْ هَذِهِ الأُمَّةِ يَهُودِيٌّ وَلاَ نَصْرَانِيٌّ ثُمَّ يَمُوتُ وَلَمْ يُؤْمِنْ بِالَّذِي أُرْسِلْتُ بِهِ إِلاَّ كَانَ مِنْ أَصْحَابِ النَّارِ ‏”

"መካህ" مَكَّة የጥንት ስሟ "በካህ" بَكَّة ነው፥ መካህ ውስጥ በይቱል ሐረም ስላለ መካህ ለዓለማት ሁሉ ማእከል ናት፦

ቁርኣን 3፥96 ለሰዎች መጀመሪያ የተኖረው ቤት ቡሩክ እና ለዓለማት ሁሉ መመሪያ ሲኾን ያ በበካህ ያለው ነው፡፡
إِنَّ أَوَّلَ بَيْتٍ وُضِعَ لِلنَّاسِ لَلَّذِي بِبَكَّةَ مُبَارَكًا وَهُدًى لِّلْعَالَمِينَ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 15, ሐዲስ 521
ጃቢር እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “ኢብራሂም መካን ቀድሷል፥ እኔም መዲናን ቀድሻለው”።
عَنْ جَابِرٍ، قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ إِنَّ إِبْرَاهِيمَ حَرَّمَ مَكَّةَ وَإِنِّي حَرَّمْتُ الْمَدِينَةَ

"ሐረመ” حَرَّمَ ማለት “ቀደሰ” ወይም “አከበረ” ማለት ሲሆን በመካህ የሚገኘው ቤት “በይቱል ሐረም” بَيْت الْحَرَام ማለትም "የተቀደሰ ቤት" "የተከበረ ቤት" ይባላል፥ መካን በምድር ላይ ካሉት ከተሞች በደረጃ ስለምትልቅ "ኡሙል ቁራ" أُمَّ الْقُرَىٰ ማለትም "የከተሞች እናት" ተብላለች፦

ቁርኣን 6፥92 የከተሞችን እናት እና በዙሪያዋ ያሉትን ሰዎች ልታስጠነቅቅበት አወረድነው፡፡ وَلِتُنذِرَ أُمَّ الْقُرَىٰ وَمَنْ حَوْلَهَا
ቁርኣን 42፥7 እንደዚሁም የከተሞችን እናት እና በዙሪያዋ ያሉትን ሰዎች ልታስጠነቅቅ እና የመሰብሰቢያውን ቀን በእርሱ ጥርጣሬ የሌለበት ሲኾን ልታስጠነቅቅ ዐረብኛ የኾነን ቁርኣን ወደ አንተ አወረድን፡፡
وَكَذَٰلِكَ أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ قُرْآنًا عَرَبِيًّا لِّتُنذِرَ أُمَّ الْقُرَىٰ وَمَنْ حَوْلَهَا وَتُنذِرَ يَوْمَ الْجَمْعِ لَا رَيْبَ فِيهِ

"መን ሐውለ-ሃ" مَنْ حَوْلَهَا ማለት "በዙሪያዋ ያሉት ሰዎች" ማለት ሲሆን ቁርኣን ማስጠንቀቂያ ሆኖ የወረደው የከተሞችን እናት የሆነችውን መካን ብቻ ሳይሆን በዙሪያ ያሉትን መላው ሰዎችን ሁሉ ነው፦

ቁርኣን 6፥19 እንዲህ በላቸው፦ «በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው? «አላህ ነው» በል፡፡ በእኔ እና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ "ይህም ቁርኣን እናንተን እና የደረሰውን ሰው ሁሉ በእርሱ ላስጠነቅቅበት ወደ እኔ ተወረደ"፡፡
قُلْ أَيُّ شَيْءٍ أَكْبَرُ شَهَادَةً ۖ قُلِ اللَّهُ ۖ شَهِيدٌ بَيْنِي وَبَيْنَكُمْ ۚ وَأُوحِيَ إِلَيَّ هَـٰذَا الْقُرْآنُ لِأُنذِرَكُم بِهِ وَمَن بَلَغَ

ምን ትፈልጋለህ? "እናንተ" ሲል ዐረቦችን ሲሆን "የደረሰውን ሰው ሁሉ" ሲል መላው ሰዎችን ሁሉ ያመለክታል፥ ነቢያችን"ﷺ" ለሰዎች ሁሉ የተላኩ የአሏህ መልእክተኛ ስለሆኑ አሏህ እራሱ፦ "ለሰዎችም ሁሉ" መልእክተኛ ኾነህ ላክንህ" በማለት ለሁሉም የሰው ልጆች መላካቸውን አስረግጦ ተናግሯል። መስካሪም በአሏህ በቃ፦

ቁርኣን 4፥79 "ለሰዎችም ሁሉ" መልእክተኛ ኾነህ ላክንህ፡፡ መስካሪም በአላህ በቃ፡፡
وَأَرْسَلْنَاكَ لِلنَّاسِ رَسُولًا ۚ وَكَفَىٰ بِاللَّهِ شَهِيدًا
ሡነን ነሣኢይ መጽሐፍ 4, ሐዲስ 37
ጃቢር ኢብኑ ዐብደሏህ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "እኔ ወደ ሰዎች ሁሉ ተልኬአለሁ፥ ከእኔ በፊት የነበሩት ነቢያት ግን ለገዛ ሕዝቦቻቸው ተልከዋል"።
عَنْ جَابِرِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ بُعِثْتُ إِلَى النَّاسِ كَافَّةً وَكَانَ النَّبِيُّ يُبْعَثُ إِلَى قَوْمِهِ خَاصَّةً ‏"‏ ‏.‏

አምላካችን አሏህ በሁለተኛ መደብ፦ "እናንተ ሰዎች ሆይ" እያለ የሚያናግረው መላውን የሰው ዘር ነው፥ ለመላው የሰው ዘር ነቢያችን"ﷺ"፦ "እኔ ወደ እናንተ "ወደ ሁላችሁም" የአላህ መልእክተኛ ነኝ" እንዲሉ አሏህ "በላቸው" በማለት አዟቸዋል፦

ቁርኣን 7፥158 በላቸው፡- «እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ወደ እናንተ "ወደ ሁላችሁም" የአላህ መልእክተኛ ነኝ»፡፡
قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ إِنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ جَمِيعًا
ቁርኣን 34፥28 አንተንም "ለሰዎች ሁሉ በሙሉ" አብሳሪ እና አስጠንቃቂ አድርገን ቢሆን እንጂ አላክንህም፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡
وَمَا أَرْسَلْنَاكَ إِلَّا كَافَّةً لِّلنَّاسِ بَشِيرًا وَنَذِيرًا وَلَـٰكِنَّ أَكْثَرَ النَّاسِ لَا يَعْلَمُونَ

"ለሰዎች ሁሉ በሙሉ" የሚለው ኃይለ-ቃል ይሰመርበት! አይበቃችሁም? ቁርኣንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስጠንቃቂ ይኾን ዘንድ ያወረደው አምላካችን አሏህ ክብርና ጥራት ተገባው፦

ቁርኣን 25፥1 ያ ፉርቃንን በባሪያው ላይ ለዓለማት አስጠንቃቂ ይኾን ዘንድ ያወረደው አምላክ ክብርና ጥራት ተገባው፡፡
تَبَارَكَ الَّذِي نَزَّلَ الْفُرْقَانَ عَلَىٰ عَبْدِهِ لِيَكُونَ لِلْعَالَمِينَ نَذِيرًا

አሏህ ለእናንተ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም