በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ
ኢየሱስ ሲመጣ በሙሴ በኩል ከአምላክ የተሰጠውን ሕግ እና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ሊሽር ሳይሆን ሊፈጽም መጥቷል፦
ማቴዎስ 5፥17 እኔ ሕግን እና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።
"ልፈጽም" ሲል "ላሟላ" "ልተገብር" ማለቱ ነው፥ በሙሴ የተነገረውን ሕግ ሊተገብር እና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ፍጻፌ በማድረግ ሊያሟላ ነው። ሰማይ እና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሙሴ ሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፦
ማቴዎስ 5፥18 እውነት እላችኋለሁ ሰማይ እና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።
ነገር ግን ከእነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ "ታናሽ" ይባላል፦
ማቴዎስ 5፥19 እንግዲህ ከእነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ "ታናሽ" ይባላል።
የጳውሎስ ስሙ "ሳውል" ነው፥ ነገር ግን "ሕግ ተሽሯል" ብሎ ሲያስተምር "ጳውሎስ" ተባለ። "ፓውሎስ" Παῦλος ማለት "ታናሽ" ማለት ነው፥ የፈጣሪን ሕግ የማይረባ እና ደካማ ብሎ በመንቀፍ "ተሽራለች" ያለው ጳውሎስ ነው፦
ዕብራውያን 7፥18 ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ "ተሽራለች"።
ኤፌሶን 2፥14 በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ..።
ቆላስይስ 2፥14 በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው።
ሕጉን በአዋጅ ያስነገረው እራሱ ፈጣሪ ነው፥ በትእዛዝም ያጻፈው እራሱ ፈጣሪ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ "ተሽራል" "የዕዳ ጽሕፈት ነው" "ተደምስሷል" ይለናል፥ ይህ የጳውሎስ ስህተቱ ነው።
የጳውሎስ ሌላው ስህተቱ ፈጣሪ "ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም" ሲል ጳውሎስ በተቃራኒው "ሰው እንዲህ(ነጠላ) ሆኖ ቢኖር መልካም ነው" ይለናል፦
ዘፍጥረት 2፥18 ያህዌህ አምላክም አለ፦ "ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት ልፍጠርለት"። וַיֹּ֙אמֶר֙ יְהוָ֣ה אֱלֹהִ֔ים לֹא־טֹ֛וב הֱיֹ֥ות הָֽאָדָ֖ם לְבַדֹּ֑ו אֶֽעֱשֶׂהּ־לֹּ֥ו עֵ֖זֶר כְּנֶגְדֹּֽו׃
1ኛ ቆሮንቶስ 7፥26-27 እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ "ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው"። በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ "በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ"።
"በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ" ምን ዓይነት ምክር ነው? ስለ ደናግል በተናገረበት ዐውድ ላይ "የአሁኑ ጊዜ ችግር" የሚለው መጋባትን ነው፥ የምነና እና የብትህውና ትምህርት ጠንሳሹ አባ እንጦስ ሳይሆን ጳውሎስ ነው፦
1 ቆሮንቶስ 7፥ 8 ላላገቡ እና ለመበለቶች ግን እላለሁ፦ "እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው"።
"እንደ እኔ (ሳያገቡ) ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው" እና "ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም" እርስ በእርሱ ይጣረሳል።
ጳውሎስ የሚቃረነው ከፈጠረው ፈጣሪ ጋር ብቻ ሳይሆን እከተለዋለው ከሚለው ከኢየሱስ ጋርም ነው፥ ኢየሱስ "ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል" ሲል ጳውሎስ ደግሞ "ሚስትም ከባልዋ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር" በማለት ይቃረናል፦
ማቴዎስ 19፥9 "እኔ ግን እላችኋለሁ "ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል"፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል" አላቸው።
1ኛ ቆሮንቶስ 7፥10 ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ።
የጳውሎስ ሌላው ስህተቱ ከግሪካውያን ሥነ ተረት"mythology" ይቀዳ ነበር። በግሪካውያን “አምላክ አንድ ነው” ብለው ስለማያምኑ “እኛ የአምላክ ዘር ነን” ብለው ያምናሉ፥ ለምሳሌ፦ ከ 315-310 ቅድመ ልደት ይኖር የነበረው ባለ ቅኔው አራተስ”Aratus” እራሱ ይህንን ይናገር ነበር፦
የሐዋርያት ሥራ 17፥28 “ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ “እኛ ደግሞ ዘሩ ነንና” ብለው እንደ ተናገሩ። τινες τῶν καθ’ ὑμᾶς ποιητῶν εἰρήκασιν Τοῦ γὰρ καὶ γένος ἐσμέν.
ጳውሎስ ከባለ ቅኔዎች መጥቀሱ ያጅባል። “ጌኑስ” γένος ማለት “ዘር” “ውሉድ”offspring” ማለት ሲሆን ጳውሎስ ከአራተስ ጠቅሶ “የአምላክ ዘር ከሆንን” በማለት አጽድቆላቸዋል፦
የሐዋርያት ሥራ 17፥29 እንግዲህ የአምላክ ዘር ከሆንን..። γένος οὖν ὑπάρχοντες τοῦ Θεοῦ
ጳውሎስ እስር ቤት ሆኖ ለአሥር አጥቢያ እና ለሦስት ግለሰቦች አሥራ አራት ደብዳቤዎችን ያጽፍ እና ይጽፍ ነበር፦
ሮሜ 16፥22 "ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ" በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።
የሮሜ ደብዳቤ የጳውሎስ ብቻ ሳይሆን የተማሪው የጤርጥዮስም ጭምር ነው፥ "ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ" የሚለው በቂ ማሳያ ሲሆን ይህ የፈጣሪ ቃል ነውን? "በርኖሱን እና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ" የሚለው ጳውሎስ እንጂ ፈጣሪ አይደለም፦
2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥13 ስትመጣ በጢሮአዳ ከአክርጳ ዘንድ የተውሁትን በርኖሱን እና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ።
ስለዚህ የጳውሎስ ደብዳቤዎች በገዛ እጁ የጻፋቸው የእርሱ ሰላምታዎች እንጂ የአምላክ ቃል በፍጹም አይደሉም፦
1ኛ ቆሮንቶስ 16፥21 እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌአለሁ።
ቆላስይስ 4፥18 በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ።
2ኛ ተሰሎንቄ 3፥17 በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ።
እነዚህን ደብዳቤዎች በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «የፈጣሪ ንግግር ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፦
ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም