በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 11፥2 እንዲህ በላቸው፡- «አላህን እንጂ ሌላን አታምልኩ! እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ እና አብሳሪ ነኝ» أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ ۚ إِنَّنِي لَكُم مِّنْهُ نَذِيرٌ وَبَشِيرٌ
ዘርዓ ያዕቆብ ከደረሳቸው መጻሕፍት አንዱ መስተብቁዕ ዘመስቀል ነው፥ መስተብቁዕ ዘመስቀል ላይ መስቀል እና ማርያም ከፈጣሪ ጋር ተካክለው ምስጋና እንደሚቀርብላቸው ይናገራል፦
መስተብቁዕ ዘመስቀል ቁጥር 8
"ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ"
"ለእነዚህ ሁለት ፍጥረታት የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል፥ በክብር ተካክለዋልና"
"ሁለቱ" የተባሉት "መስቀል እና ማርያም" ሲሆኑ እነዚህ ሁለት ፍጡራን ከፈጣሪ ጋር "በክብር ተካክለዋል" ይለናል፥ ኢየሱስን፦ "ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ(በባሕይርው ከአብ ጋር የሚተካከል)" ሲሉት ሲገርመን ማርያም እና መስቀልን "እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ(በክብር ተካክለዋል)" ሲሏቸው አስደመመን። ስለተስተካከሉ ለፈጣሪ የሚገባው የፈጣሪ ምስጋና "ይገባቸዋል" ብለው አረፉት፥ ይህ እልም ያለ ሺርክ ነው። ስብሐት ለሦስቱ ማለትም ለእግዚአብሔር፣ ለድንግል እና ለመስቀል እንደሚገባ የዘወትር ጸሎት ላይ ተገልጿል፦
የዘወትር ጸሎት ቁጥር 9
"ስብሐት ለእግዚአብሔር ወወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር"
ትርጉም፦ "ለእግዚአብሔር፣ ለወለደችው ለድንግል እና ለክቡር መስቀሉ ምስጋና ይገባል"
መስቀል ከመመስገንም አልፎ ይሰገድለታል፦
የዘወትር ጸሎት ቁጥር 8
“እሰግድ “ለ”መስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተቀደሰ በደሙ ክቡር”
ትርጉም፦ “በደሙ ክቡር “ለ”ተሰቀለበት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እሰግዳለው”
እንደ ትምህርታቸው ኢየሱስ የተሰቀለበት እና ደሙን ያፈሰሰበት እንጨት እኮ አንድ ነው፥ ዛሬ በእጃቸው የሚያሳልሙበት እና በጉልላት ላይ የሚሰቅሏቸው መስቀሎች የተሰቀለባቸው፣ ደም የፈሰሰባቸው እና ወዝ የተንጠፈጠፈባቸው ስላልሆኑ በምንም ሒሣብ ክቡር አይደሉም።
የሚገርመው መስከረም 17 ቀን "ዮም መስቀል ተሰብሐ" ማለትም "ዛሬ መስቀል ተመሰገነ" በማለት ካመሰገኑት በኃላ መልሰው በደመራ ያቃጥሉታል። "የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፣ አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም" እየተባለ ለማይሰማ እና ለማይለማ፥ ለማይናገር እና ለማይጋገር ለግዑዝ እንጨት የጸጋ ስግደት መስገድ አግባብ አይደለም፥ ይህ ድርጊት አሳፋሪ እንደሆነም ተገልጿል፦
ዘጸአት 20፥4 የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ! አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም።
መዝሙር 97፥7 ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ፥ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ።
"ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ" የሚለው ይሰመርበት! እኛም ሙሥሊሞች የምንለው ደግሞ "የፈጠራችሁን አሏህን ብቻ አምልኩ" ነው፦
ቁርኣን 11፥2 እንዲህ በላቸው፡- «አላህን እንጂ ሌላን አታምልኩ! እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ እና አብሳሪ ነኝ»
أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ ۚ إِنَّنِي لَكُم مِّنْهُ نَذِيرٌ وَبَشِيرٌ
የፈጠረንን አንዱን አምላክ ብቻ ማምለክ ምንኛ መታደል ነው? አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም