በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 81፥21 በዚያ ስፍራ ትእዛዙ ተሰሚ፤ ታማኝ የኾነ መልእክተኛ ቃል ነው፡፡
مُّطَاعٍ ثَمَّ أَمِينٍ
ሚሽነሪዎች ጋንጩር እንዳለበት ክልው ክልው የሚያረጋቸው ነገር አለ፥ ካለማወቅ ይሁን በማወቅ መላ ቅጡ እና ቅጥ አንባሩ ጠፍቶባቸዋል። "አሏህ እያለ እንዴት መላእክት ለጂብሪል ይታዘዛሉ" የሚል መናኛ ሙግት ይሟገታሉ፥ መጠየቁ አግባብ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ ዐዋቂ ሙግት አደራጅቶ መሰንዘር ግን አግባብ አይደለም።
እንደሚታወቀው ወደ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" በታማኝነት መልእክት ከአሏህ ዘንድ የሚያስተላልፍ መልአኩ ጂብሪል "ሙጧዕ" مُّطَاع ማለትም "አዛዥ" ወይም "ትእዛዙ ተሰሚ" ተብሏል፦
ቁርኣን 81፥21 በዚያ ስፍራ "ትእዛዙ ተሰሚ" እንዲሁ ታማኝ የኾነ መልእክተኛ ቃል ነው፡፡
مُّطَاعٍ ثَمَّ أَمِينٍ
ተፍሢሩል ጀላለይን 81፥21 "ትእዛዙ ተሰሚ" ማለት "በሰማይ እና በምድር መላእክት ይታዘዙለታል፥ "ታማኝ" ማለት "ታማኝነቱ በወሕይ ላይ ነው።
{ مُّطَاعٍ ثَمَّ } أي تطيعه الملائكة في السموات والأَرض { أَمِينٍ } على الوحي.
እዚህ አንቀጽ ላይ ጂብሪል "አዛዥ" ወይም "ትእዛዙ ተሰሚ" መባሉ እኮ ጂብሪል "የመላእክት አለቃ" መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ይህንን ለማስረዳት በሰፈራችሁት ቁና ሰፍረን እናሳያችሁ! "ሊቅ" ማለት "ምሁር" ማለት ብቻ ሳይሆን "አለቃ" ማለትም ጭምር ነው፥ ለምሳሌ፦ "ሊቀ ጳጳሳት" ማለት "የጳጳሳት አለቃ" ማለት ሲሆን "ሊቃነ ጳጳሳት" ማለት "የጳጳሳት አለቆች" ማለት ነው። ስለዚህ "ሊቃውንት" ማለት "ምሁራን" ማለት ብቻ ሳይሆን "አለቆች" ማለትም ጭምር ነው፦
ጦቢት 12፥15 "ከከበሩ ሰባት አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ" አላቸው።
ዳንኤል 10፥13 ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።
וְהִנֵּ֣ה מִֽיכָאֵ֗ל אַחַ֛ד הַשָּׂרִ֥ים הָרִאשֹׁנִ֖ים בָּ֣א לְעָזְרֵ֑נִי
እዚህ አንቀጽ ላይ "አለቃ" ለሚለው የገባው ቃል የዕብራይስጡ ማሶሬት ላይ "ሳር" שַׂר ሲሆን የግሪክ ሰፑአጀንቱ ላይ ደግሞ "አርኾስ" ἀρχός ነው፥ ይህም "መሪ" "ገዢ" "አዛዥ" ማለት ነው። "አዛዥ" መባል በራሱ አንደኛው መልአክ ሌላውን መልአክ እንደሚመራው፣ እንደሚገዛው፣ እንደሚያዘው ጉልኅ ማሳያል ነው፥ ጦቢት ላይ ሊቃነ መላእክት"archangels" ሰባት መሆናቸው ሲገለጽ ዳንኤል ላይ ደግሞ ሚካኤል ከሊቃነ መላእክት አንዱ ሊቀ መላእክት መሆኑን ያሳያል። ሚካኤል "የመላእክት አለቃ" መባሉ በራሱ አንድ ሊቀ መላእክት መልአክ ሆኖ ሌሎችን መላእክት ማዘዙን እና ለራሱ የሥራ ድርሻ የሚላላኩለት መላእክት እንዳሉት ቁልጭ አርጎ ያሳያል፦
ይሁዳ 1፥9 "የመላእክት አለቃ ሚካኤል" ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር፦ ጌታ ይገሥጽህ፥ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
ራእይ 22፥7 በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤል እና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ።
Καὶ ἐγένετο πόλεμος ἐν τῷ οὐρανῷ, ὁ Μιχαὴλ καὶ οἱ ἄγγελοι αὐτοῦ τοῦ πολεμῆσαι μετὰ τοῦ δράκοντος.
"መላእክቱ" የሚለው ቃል "አንጌሎኢ አውቶዩ" ἄγγελοι αὐτοῦ ሲሆን "የእርሱ መላእክት"his angels" ማለት ሲሆን "የ" አጋናዛቢ ዘርፍ የተገናዘበለት "እርሱ" የሚለው ተውላጠ ስም "ሚካኤል" የሚለው ስም ተክቶ እና ለውጦ የመጣ ነው።
ሰባቱ የመላእክት ሊቃውንት(አለቆች) ደግሞ በትውፊት ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል፣ ራጉኤል፣ ዑራኤል፣ ፋኑኤል፣ ሳቁኤል ናቸው፥ እነዚህ ሰባቱ መላእክት በዙፋኑ ፊት የሚቆሙ ሰባቱ መላእክት፣ ሰባት የእሳት መብራቶች፣ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት(መንፈሶች)፣ የእግዚአብሔር ዓይኖች ተብለዋል፦
ራእይ 8፥2 በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን "ሰባቱን መላእክት" አየሁ፥
ራእይ 4፥5 በዙፋኑም ፊት "ሰባት የእሳት መብራቶች" ይበሩ ነበር፥ እነርሱም "ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት" ናቸው።
ዘካርያስ 4፥2 "ሰባትም መብራቶች" ነበሩበት፤
ዘካርያስ 4፥10 "እነዚህ ሰባቱ" ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ "እነዚህም" በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ "የእግዚአብሔር ዓይኖች" ናቸው።
የሚገርመው አንዱ መልአክ ሌላውን መልአክ በትእዛዛዊ ግሥ "ስደድ" "ቍረጥ" "ሩጥ" "በለው" በማለት ያዘዋል፦
ራእይ 14፥17 ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው። በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን፦ ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን "ስደድ" እና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች "ቍረጥ" ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ።
ዘካርያስ 2፥3-4 እነሆም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጣ፥ ሌላም መልአክ ሊገናኘው ወጣ፥ እንዲህም አለው፦ "ሩጥ" ይህንም ጕልማሳ እንዲህ "በለው"፦ ኢየሩሳሌም በውስጥዋ ካሉት ሰዎችና እንስሶች ብዛት የተነሣ ቅጥር እንደሌላቸው መንደሮች ሆና ትኖራለች።
በመላእክት መካከል ያለው መተታዘዝ የግብር መተታዘዝ"functional obedience" እንጂ የባሕርይ መተዛዘዝ"ontological obedience" ስላልሆነ ከላይ ያለውን መላእክት ለጂብሪል መታዘዛቸውን በዚህ ስሌት እና ሒሣብ መረዳት ትችላላችሁ።
እንግዲህ ዐቃቢያነ እሥልምና የኢሥላም ዘቦች፣ አበጋዞች እና አርበኞች ብቻ ሳይሆኑ ስንዱ ከበርቴዎች እና ለመጪው ትውልድ ማኅቶት እና ማዕዶት መሆናቸውን ተረድታችሁ እርማት እንደምትወስዱ ኢንሻሏህ ተስፋ አለን።
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም