በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 6፥164 በላቸው «እርሱ አላህ የሁሉ ነገር ጌታ ሲሆን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡
قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

አምላካችን አሏህ ስለ ራሱ በሦስተኛ መደብ "የሁሉ ነገር ጌታ" እንደሆነ ይናገራል፦

ቁርኣን 6፥164 በላቸው «እርሱ አላህ የሁሉ ነገር ጌታ ሲሆን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ ክፉን አትሠራም፡፡
قُلْ أَغَيْرَ ٱللَّهِ أَبْغِى رَبًّۭا وَهُوَ رَبُّ كُلِّ شَىْءٍۢ ۚ وَلَا تَكْسِبُ كُلُّ نَفْسٍ إِلَّا عَلَيْهَا

ሚሽነሪዎች ይህንን አንቀጽ ይዘው "በባይብል ኢየሱስ "የሁሉ ጌታ" ተብሏልና የእርሱ ጌትነት የባሕርይ ነው" በማለት ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፦

የሐዋርያት ሥራ 10፥36: "የሁሉ ጌታ በሚሆን" በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።
Tὸν λόγον ὃν ἀπέστειλεν τοῖς υἱοῖς Ἰσραήλ, εὐαγγελιζόμενος εἰρήνην διὰ Ἰησοῦ χριστοῦ― οὗτός ἐστιν πάντων κύριος―

ሲጀመር "የሁሉ ጌታ በሚሆን"he is Lord of all" የሚለው ኃይለ-ቃል በ 400 ድኅረ ልደት በተዘጋጀው ኮድ በፊደል D በቁጥር 05 በሆነው ኮዴክስ ቤዛይ ላይ በቅንፍ የተቀመጠ ነው፦
― οὗτός ἐστιν πάντων κύριος―

ለማመሳከሪያ ኦርጅናሉ ስለሌለ የተለያዩ ቨርዥኖች "he is Lord of all" የሚለውን በቅንፍ አስቀምጠውታል፥ ለምሳሌ፦

  1. English Standard Version
  2. King James Bible
  3. New American Standard Bible
  4. American Standard Version
  5. Literal Standard Version
  6. Young's Literal Translation
    ተጠቃሾ ናቸው።
ልክ ሉቃስ 3፥23 "እንደመሰላቸው"as was supposed" የሚለው ኮዴክስ ቤዛይ ላይ በቅንፍ እንደተቀመጠው ማለት ነው፦

ሉቃስ 3፥23 ― ὡς ἐνομίζετο―

ሲቀጥል ጥቅሱ ላይ "የሁሉ" የሚለው ገላጭ ቅጽል "ፓንቶን" πάντων አይሁድ እና አሕዛብ ለማሳየት የገባ አንጻራዊ እንጂ ፍጹማዊ አይደለም። ለምሳሌ፦ "ፓንቶን" የሚለው ቃል በአንጻራዊ ደረጃ ይመጣል፦

1 ቆሮንቶስ 4፥13 እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ "የሁሉም" ጉድፍ ሆነናል።
δυσφημούμενοι παρακαλοῦμεν· ὡς περικαθάρματα τοῦ κόσμου ἐγενήθημεν, πάντων περίψημα ἕως ἄρτι.

ጳውሎስ "የሁሉም" ሰው ጉድፍ ሆነናል" ሲል በአንጻራዊ እንጂ ጳውሎስ የማያውቁት ሁሉንም ያጠቃልላል ማለት አይደለም። በተመሳሳይም ኢየሱስ "የሁሉ ጌታ" የተባለው በአንጻራዊ ደረጃ ነው፥ ምክንያቱም አንደኛ ጌትነቱ መነሻ አለው፣ ሁለተኛ ከእርሱ በላይ ያለውን ጌታውን "ጌታዬ" እያለ ተናግሯል፣ ሦስተኛ የእርሱ ጌታ አብ እርሱን "ባሪያዬ" ብሎታል፣ አራተኛ ከበላዩ ራስ አለው።
ሢሠልስ አማኞች "የሁሉ ጌታ" ተብለዋል፦

ገላትያ 4፥1 ነገር ግን እላለሁ ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ ምንም "የሁሉ ጌታ" ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም።
Λέγω δέ, ἐφ’ ὅσον χρόνον ὁ κληρονόμος νήπιός ἐστιν, οὐδὲν διαφέρει δούλου κύριος πάντων ὤν,

"ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ ምንም "የሁሉ ጌታ" ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም" የተባለው ሕፃን አማንያንን እንደሆነ ዐውደ ንባቡ"contextual passage" ይናገራል፦

ገላትያ 4፥2-3 ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው። እንዲሁ እኛ ደግሞ ሕፃናት ሆነን ሳለን ከዓለም መጀመሪያ ትምህርት በታች ተገዝተን ባሪያዎች ነበርን።
ገላትያ 4፥7 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ።

ዮሴፍ በአንጻራዊ ደረጃ በግሪክ ሰፕቱአጀንት "የሁሉ ጌታ" ተብሏል፦

ዘፍጥረት 45፥9 "አምላክ" በግብፅ ምድር ላይ "የሁሉ ጌታ" አደረገኝ። τάδε λέγει ὁ υἱός σου ᾿Ιωσήφ· ἐποίησέ με ὁ Θεὸς κύριον πάσης γῆς Αἰγύπτου·

ዮሴፍ በመደረግ "የሁሉ ጌታ" ከተባለ ኢየሱስም በመደረግ "የሁሉ ጌታ" ቢባል ያንስበታልን? ወይስ ይበዛበታል? ፈጣሪ አምላክ ዮሴፍን ጌታ ስላረገው ዮሴፍ፦ "አምላክ" በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ "ጌታ" አደረገኝ" ብሎአል፦

ዘፍጥረት 45፥9 "አምላክ" በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ "ጌታ" አደረገኝ። שָׂמַ֧נִי אֱלֹהִ֛ים לְאָדֹ֖ון לְכָל־מִצְרָ֑יִם

"ጌታ አደረገኝ" ሲል የዓለማቱ ጌታ ሆነ ማለት ሳይሆን በጸጋ እና በስጦታ ያገኘው እንጂ የባሕርይ ጌትነት በፍጹም አይደለም። በተመሳሳይም የኢየሱስ ጌትነት በመደረግ ላይ የተመሠረተ መነሾ ያለው ስለሆነ የባሕርይ ጌትነት በፍጹም አይደለም፦

የሐዋርያት ሥራ 2፥36 ኢየሱስን አምላክ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ። ἀσφαλῶς οὖν γινωσκέτω πᾶς οἶκος Ἰσραὴλ ὅτι καὶ Κύριον αὐτὸν καὶ Χριστὸν ἐποίησεν ὁ Θεός, τοῦτον τὸν Ἰησοῦν.

እዚህ አንቀጽ ላይ "አምላክ" ባለቤት ሲሆን "ኢየሱስ" ተሳቢ ነው፥ በባለቤት እና በተሳቢ መካከል "እንዳደረገው" የሚል ተሻጋሪ ግሥ አለ። ጌታ አድራጊ አንዱ አምላክ ሲሆን ጌታ ተደራጊ ኢየሱስ ነው፥ አምላክ ኢየሱስን ጌታ ካረደገው የኢየሱስ ጌትነት መነሾ ያለው ስለሆነ ጌታ ከመደረጉ በፊት በባዶነት ስለሚቀደም ጌትነቱ ሥልጣን እና ሹመት ወይም እልቅና እና ማዕረግን ብቻ ያሳያል እንጂ የባሕርይ ገንዘቡ መሆኑን በፍጹም አያሳይም።
ስለዚህ ኢየሱስ "የሁሉ ጌታ" የተባለው ልክ አማኞች እና ዮሴፍ በተባሉበት ሒሣብ አንጻራዊ ነው፥ የኢየሱስ ጌታ አሏህ ግን በጌትነቱ ባርነት የሌለበት የሁሉም አንድ ጌታ አምላክ ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም