በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 22፥6 ይህ አላህ እርሱ መኖሩ የተረጋገጠ፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡
ذَٰلِكَ بِأَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ وَأَنَّهُ يُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَأَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

በአንድ ወቅት የነገረ ልቦና ምሁር ሲይግመን ፍሮይድ፦ "ሁሉን የሚቆጣጠር እና የሚመግብ አምላክ ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ በሚያስፈልገው በሰው ሥነ ልቡና የተፈጠረ ነው"The God who controls and provides everything, is created by the human psyche in response to its need for love, saftey and security" በማለት ኢ-አማኝነቱን ገልጿል። ይህ የኢልሓድ እሳቤ ነው፥ በፈጣሪ እሳቦት ውስጥ ኢማን፣ ኩፍር እና ኢልሓድ ተጠቃሽ ናቸው።
"ኢልሓድ" إِلْحَاد የሚለው ቃል "አልሐደ" أَلْحَدَ‎ ማለትም "ኢ-አመነ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን በአምላክ መኖር "ኢ-አማኒነት"atheism" ማለት ነው፥ በነጠላ "ሙልሒድ" مُلْحِد ማለት "ኢ-አማኝ"atheist" ማለት ሲሆን "ሙልሒዱን" مُلْحِدُون‎ ደግሞ የሙልሒድ ብዙ ቁጥር ነው። ሙልሒድ የኢልሓድ እሳቤ የሚያራምዱ ናቸው፦

ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 87 ሐዲስ 21
ኢብኑ ዐባሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም፦ “ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “አሏህ ዘንድ የተጠሉ ሦስት ሰዎች አሉ፦ “በሐረም ውስጥ ያለ ሙልሒድ፣ የጃሂሊያህን ሡናህ ኢሥላም ውስጥ ለማስቀረት የሚፈልግ እና ያለ ሕግ የአንድ ሰው ደም ማፍሰስ የሚፈልግ ናቸው"።
عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ، أَنَّ النَّبِيَّ صلى الله عليه وسلم قَالَ أَبْغَضُ النَّاسِ إِلَى اللَّهِ ثَلاَثَةٌ مُلْحِدٌ فِي الْحَرَمِ، وَمُبْتَغٍ فِي الإِسْلاَمِ سُنَّةَ الْجَاهِلِيَّةِ، وَمُطَّلِبُ دَمِ امْرِئٍ بِغَيْرِ حَقٍّ لِيُهَرِيقَ دَمَهُ. ‏

"ዉጁድ" وُجُود የሚለው ቃል "ወጀደ" وَجَدَ ማለትም "አለወ" "ኖረ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መኖር" ሃልዎት" "ህልውና" ማለት ነው፥ "ዉጁዱል ሏህ" وُجُود الله ማለት "የአሏህ ህልውና"the existence of Allah" ማለት ነው። የአሏህ መኖር የተረጋገጠ ነው፦

ቁርኣን 22፥6 ይህ አላህ እርሱ "መኖሩ የተረጋገጠ"፣ እርሱም ሙታንን ሕያው የሚያደርግ፣ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ በመሆኑ ነው፡፡
ذَٰلِكَ بِأَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ وَأَنَّهُ يُحْيِي الْمَوْتَىٰ وَأَنَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ
ቁርኣን 24፥25 በዚያ ቀን አላህ እውነተኛ ዋጋቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ አላህም እርሱ "መኖሩ የተረጋገጠ" ሁሉን ነገር ገላጭ መኾኑን ያውቃሉ፡፡
يَوْمَئِذٍ يُوَفِّيهِمُ اللَّهُ دِينَهُمُ الْحَقَّ وَيَعْلَمُونَ أَنَّ اللَّهَ هُوَ الْحَقُّ الْمُبِينُ

"አል ሐቅ" الْحَقّ ማለት "መኖሩ ተረጋገጠ" ማለትም ሲሆን አንድ ሰው የአሏህን መኖር የሚረጋገጠው እንደ ሲይግመን ፍሮይድ ማየት፣ መስማት፣ ማሽተት፣ መቅመስ እና መዳደስ በሚባሉት አምስት የስሜት ሕዋሳት ሳይሆን በመኽሉቅ፣ በፊጥራህ፣ በዐቅል፣ በነቅል፣ በአደብ ነው። እነዚህ ማረጋገጫዎች እንመልከት፦

፨ "መኽሉቅ" مَخْلُق ማለት "ፍጥረት" ማለት ሲሆን ፍጥረት ውጤት ከሆነ ፈጣሪ መንስኤ ነው፥ አሏህ ስለመኖሩ ጉልኅ ማረጋገጫ የፍጥረት ሙግት"cosmological argument" ነው፦

ቁርኣን 56፥58 በማኅፀኖች የምታፈሱትን አያችሁን? أَفَرَأَيْتُم مَّا تُمْنُونَ
ቁርኣን 56፥59 እናንተ ትፈጥሩታላችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹን ነን? أَأَنتُمْ تَخْلُقُونَهُ أَمْ نَحْنُ الْخَالِقُونَ

በተራክቦ ጊዜ በሴት ብልት ውስጥ የሚፈሰውን የወንድ ሕዋስ"sperm cell" ሰው አርገን መፍጠር አለመቻላችን በራሱ የተፈረጠውን የሚፈጥር ፈጣሪ እንዳለ አመላካች ነው፥ በመንስኤ እና በውጤት ሕግ ያለ ሠሪ ተሠሪ እንደሌለ ሁሉ ያለ ፈጣሪ ተፈጣሪ የለም። የፍጥረት ሙግት በመቀጠል ሰው እራሱን እራሱ አለመፍጠሩ የፈጠረውን ፈጣሪ እንዳለ በቂ ማሳያ ነው፦

ቁርኣን 52፥35 ወይስ ያለ አንዳች "ነገር" ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?
أَمْ خُلِقُوا مِنْ غَيْرِ شَيْءٍ أَمْ هُمُ الْخَالِقُونَ
ቁርኣን 52፥36 ወይስ ሰማያትን እና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም፡፡
أَمْ خَلَقُوا السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ ۚ بَل لَّا يُوقِنُونَ

ፍጥረት ያለምንም ፈጣሪ እንዳልተፈጠረ እሙን እና ቅቡል ነው፥ ፍጥረትን ፍጡር አልፈጠረም። ሰማያትን እና ምድርን ሰው አለመፍጠሩ በራሱ ፈጣሪ መኖሩን ማረጋገጫ ነው። ይህንን ሙግት በምንጨታዊ፣ በስሙር፣ በርቱዕ ሙግት ስናዋቅረው፦

  1. ማንኛውም ነገር መነሾ አለው፣
  2. መነሾ ያለው ነገር መንስኤ"cause" አለው፣
  3. ስለዚህ ፍጥረትን ያስገኘው መንስኤ ፈጣሪ ነው፦
ቁርኣን 46፥3 በሰማያት እና በምድር ውስጥ ለምእምናን ሁሉ እርግጠኛ ምልክቶች አሉ፡፡
إِنَّ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ لَآيَاتٍ لِّلْمُؤْمِنِينَ
ቁርኣን 7፥54 ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ የፈጠረ አላህ ነው፡፡
إِنَّ رَبَّكُمُ اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ

፨ "ፊጥራህ" فِطْرَة ማለት "ተፈጥሮ ማለት ሲሆን አሏህ ስለመኖሩ ማረጋገጫ የሥነ ኑባሬ ሙግት"ontological argument" ነው፦

ቁርኣን 30፥30 ወደ እውነት ተዘንባይ ኾነህም ፊትህን ለሃይማኖት ቀጥ አድርግ፡፡ የአላህን ፍጥረት ያችን አላህ ሰዎችን በእርስዋ ላይ የፈጠረባትን ሃይማኖት ያዟት፡፡
فَأَقِمْ وَجْهَكَ لِلدِّينِ حَنِيفًا ۚ فِطْرَتَ اللَّهِ الَّتِي فَطَرَ النَّاسَ عَلَيْهَا
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 46, ሐዲስ 38
አቢ ሙዓዊያህ እንደተረከው፦ ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ "ማንም የሚወለድ ሰው በአንደበቱ እስከሚል ድረስ በአል-ፊጥራህ ላይ ሆኖ እንጂ አይወለድም።
عَنْ أَبِي مُعَاوِيَةَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ إِلاَّ عَلَى هَذِهِ الْمِلَّةِ حَتَّى يُبَيِّنَ عَنْهُ لِسَانُهُ ‏"‏ ‏.

አሏህ በፊጥራህ ጊዜ ከአደም ልጆች ከጀርቦቻቸው ዘሮቻቸውን በማውጣት፦ "ጌታችሁ አይደለሁምን" ብሎ አስመስክሯል፦

ቁርኣን 7፥172 "ጌታህም ከአደም ልጆች ከጀርቦቻቸው ዘሮቻቸውን ባወጣና፦ «ጌታችሁ አይደለሁምን?» ሲል በራሳቸው ላይ ባስመሰከራቸው ጊዜ የኾነውን አስታውስ፡፡ «ጌታችን ነህ መሰከርን» አሉ፡፡ «በትንሣኤ ቀን ከዚህ ኪዳን ዘንጊዎች ነበርን እንዳትሉ፡፡»
وَإِذْ أَخَذَ رَبُّكَ مِن بَنِي آدَمَ مِن ظُهُورِهِمْ ذُرِّيَّتَهُمْ وَأَشْهَدَهُمْ عَلَىٰ أَنفُسِهِمْ أَلَسْتُ بِرَبِّكُمْ ۖ قَالُوا بَلَىٰ ۛشَهِدْنَا ۛ أَن تَقُولُوا يَوْمَ الْقِيَامَةِ إِنَّا كُنَّا عَنْ هَـٰذَا غَافِلِينَ
ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 42, 121
ሐማድ ኢብኑ ሠለማህ፦ "ሁሉም መውሉድ በፊጥራህ ይወለዳል" የሚለውን ንግግር ይዞ እንዲህ አለ፦ "ይህ በእኛ ምልከታ ከአባቶቻቸው ጀርባ ሲወጡ አሏህ፦ "እኔ ጌታችሁ አይደለሁምን? ሲል "አዎ" በማለት ኪዳን በያዘ ጊዜ ነው።
قَالَ سَمِعْتُ حَمَّادَ بْنَ سَلَمَةَ، يُفَسِّرُ حَدِيثَ ‏"‏ كُلُّ مَوْلُودٍ يُولَدُ عَلَى الْفِطْرَةِ ‏"‏ ‏.‏ قَالَ هَذَا عِنْدَنَا حَيْثُ أَخَذَ اللَّهُ عَلَيْهِمُ الْعَهْدَ فِي أَصْلاَبِ آبَائِهِمْ حَيْثُ قَالَ ‏{‏ أَلَسْتُ بِرَبِّكُمْ قَالُوا بَلَى ‏}‏ ‏.‏

ሰው በተፈጥሮው የአምልኮ ፍላጎት እና ዝንባሌ ያለው ፍጡር የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፥ ሰው በፊጥራህ ጊዜ "ጌታችን ነህ መሰከርን" ማለታቸው በታኅታይ ሕሊና"subconscious" የተቀመጠ ሲሆን በትንሳኤ ቀን ይህ ውስጣችን ያለው ምሥጢር ይገለጻል፦

ቁርኣን 100፥10 "በልቦች ውስጥ ያለውም ሁሉ በተገለጸ ጊዜ እንዴት እንደሚኾን፡፡ وَحُصِّلَ مَا فِي الصُّدُورِ
ቁርኣን 86፥9 "ምሥጢሮች በሚገለጡበት ቀን"፡፡
يَوْمَ تُبْلَى السَّرَائِرُ

፨ "ዐቅል" عَقْل ማለት "አእምሮ" ማለት ሲሆን አሏህ ስለመኖሩ ማረጋገጫ የሥነ አመክንዮ ሙግት"logical argument" ነው፦

ቁርኣን 51፥21 በነፍሶቻችሁም ውስጥ ምልክቶች አሉ፤ ታዲያ አትመለከቱምን?
وَفِي أَنفُسِكُمْ ۚ أَفَلَا تُبْصِرُونَ

የሰው ውሳጣዊ ተፈጥሮ በሥነ አመክንዮ ፈጣሪ እንዳለ ምስክርነት ነው፥ በነፍሶቻችን ውስጥ ያሉት የአስተሳሰብ ቅኝት"mindset" ተአምራት ሲሆኑ ከተመለከትን የአሏህን መኖር ፍትንው አርገው ያረጋግጣሉ፦

ቁርኣን 91፥8 አመጽዋን እና ፍርሃትዋንም ባሳወቃት፡፡
فَأَلْهَمَهَا فُجُورَهَا وَتَقْوَاهَا

እዚህ አንቀጽ ላይ "ባሳወቀ" ለሚለው የገባው ቃል "አልሀመ" أَلْهَمَ መሆኑን ልብ በል! "ኢልሃም" إِلْهَام የሚለው ቃል እራሱ "አልሀመ" أَلْهَمَ ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ውሳጣዊ ግንዛቤ ወይም ዕውቀ-ልቦና”intuition” ማለት ነው፥ ለነፍስ በመልካም መታዘዝ እና በክፉን ማመጽ በውስጧ ያሳወቃት መኖሩ በራሱ የአሏህ መኖር የሕሊና ምስክርነት ነው።

፨ "ነቅል" نَقْل ማለት "ግልጠተ መለኮት" ማለት ሲሆን በነቢያቱ በኩል የመጣ ማረጋገጫ ነው፥ "ላ ኢላሀ ኢለል ሏህ" لَا إِلَـٰهَ إِلَّا اللَّه የሚለው መርሕ የሁሉም ነቢያት መርሕ ነው፦

21፥25 ከአንተ በፊትም እነሆ፦ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልእክተኛ አንድንም አላክንም፡፡
وَمَا أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِي إِلَيْهِ أَنَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدُونِ
ቁርኣን 20፥14 እኔ አላህ እኔ ነኝ ያለ እኔ አምላክ የለምና አምልከኝ፡፡ ሶላትንም በእርሷ እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡
إِنَّنِي أَنَا اللَّهُ لَا إِلَـٰهَ إِلَّا أَنَا فَاعْبُدْنِي وَأَقِمِ الصَّلَاةَ لِذِكْرِي

በነቢያቱ በኩል ወሕይ በማውረድ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" እያለ የሚናገር ነባቢ መለኮት መኖሩ፣ ሰዎች የሚመሩበትን ሙሐከማት መስጠቱ እና "ሰማያትን እና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን" ማለቱ በራሱ የሥነ መለኮት ሙግት"theological argument" ነው፦

ቁርኣን 50፥38 ሰማያትን እና ምድርን በመካከላቸው ያለውንም ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ድካምም ምንም አልነካንም፡፡
وَلَقَدْ خَلَقْنَا السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ وَمَا بَيْنَهُمَا فِي سِتَّةِ أَيَّامٍ وَمَا مَسَّنَا مِن لُّغُوبٍ

፨ "አደብ" اَدَب‎ ማለት "ግብረገብ" ማለት ሲሆን ሰው ግን ነጻ ፈቃድ ስላለው በሚሠራው መልካም ሥራ ስለሚነዳ እና በሚሠራው ክፉ ሥራ ስለሚቀጣ ልቅ ሆኖ አልተተወም፦

ቁርኣን 75፥36 ሰው ልቅ ኾኖ መተውን ያስባልን?
أَيَحْسَبُ الْإِنسَانُ أَن يُتْرَكَ سُدًى

ይህ ግብረገባዊ ሙግት"moral argument" ነው፥ "መሥኡሉል አደብ” مَسْؤُول الاَدَب‎ ማለት “ግብረገባዊ ተጠያቂነት”moral accountability” ማለት ሲሆን ሰው በተሰጠው ጸጋ ለሚሠራው ሥራ ተጠያቂ መሆኑ በራሱ ጠያቂ ፈጣሪ መኖሩ ማረጋገጫ ነው፦

ቁርኣን 21፥23 ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ ግን ይጠየቃሉ፡፡
لَا يُسْأَلُ عَمَّا يَفْعَلُ وَهُمْ يُسْأَلُونَ
ቁርኣን 16፥93 ትሠሩት ከነበራችሁትም ሁሉ በእርግጥ ትጠየቃላችሁ፡፡
وَلَتُسْأَلُنَّ عَمَّا كُنتُمْ تَعْمَلُون
ቁርኣን 102፥8 ከዚያም ከጸጋችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ።
ثُمَّ لَتُسْأَلُنَّ يَوْمَئِذٍ عَنِ النَّعِيمِ

አምላካችን አሏህ ከሙልሒድ ኢልሓድ ይጠብቀን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም