በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 37፥102 ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡
فَلَمَّا بَلَغَ مَعَهُ ٱلسَّعْىَ قَالَ يَٰبُنَىَّ إِنِّىٓ أَرَىٰ فِى ٱلْمَنَامِ أَنِّىٓ أَذْبَحُكَ فَٱنظُرْ مَاذَا تَرَىٰ ۚ قَالَ يَٰٓأَبَتِ ٱفْعَلْ مَا تُؤْمَرُ ۖ سَتَجِدُنِىٓ إِن شَآءَ ٱللَّهُ مِنَ ٱلصَّٰبِرِينَ

"ኢሽማኤል" יִשְׁמָעֵאל‎ የሚለው ቃል የሁለት ዕብራይስጥ ቃላት ውቅር ነው፥ "ኢሽማ" שָׁמַע ማለት "ይሰማል" ማለት ሲሆን "ኤል" אֵל ማለት "አምላክ" ማለት ነው። በጥቅሉ "ኢሽማኤል" יִשְׁמָעֵאל‎ ማለት "አምላክ ጸሎቴን ሰማኝ" ማለት ነው፥ ይህ ስም የወጣበት ምክንያት አብርሃም፦ "አቤቱ ያህዌህ ሆይ! ምንን ትሰጠኛለህ? ያለ ልጅ እሄዳለሁ” ብሎ ለለመነው ልመና መልስ ፈጣሪም፦ "ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል" በማለት ይመልስለታል፦

ዘፍጥረት 15፥2 አብራምም፦ አቤቱ አቤቱ ያህዌህ ሆይ! ምንን ትሰጠኛለህ? ያለ ልጅ እሄዳለሁ።
ዘፍጥረት 15፥4 እነሆም የያህዌህ ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፦ ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል።

ፈጣሪም ከአብርሃም ጉልበት ስለወጣው የአብራኩ ክፋይ ሲናገር፦ "ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ" በማለት ጸሎቱን ሰምቶታል፥ አብርሃምም አምላክ ጸሎቱን ስለሰማው የልጁን ስም "እስማኤል" ብሎ ጠራው፦

ዘፍጥረት 17፥20 ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ "ባርኬዋለሁ"።
ዘፍጥረት16፥15 አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው።

"ልጁን" የሚለው ይሰመርበት! አንዳንድ ዐላዋቂ የክርስትና መምህራን እስማኤል የአብርሃም ልጅ እንዳልሆነ እና እንዳልተባረከ ሲናገሩ ስንስማ ምን ያክል ባይብልን እንዳማያነቡ ያሳብቅብባቸዋል። አጋር የሳራ ባሪያ ብትሆንም ለአብርሃም ሚስቱ ነእንደነበረች እሙን እና ቅቡል ነው፥ ስለዚህ ልጇ ለኢብራሂም ሕጋዊ ልጅ ነው፦

ዘፍጥረት 16፥3 የአብራም ሚስት ሦራ ግብፃዊት ባሪያዋን አጋርን ወስዳ ለባልዋ ለአብራም ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠችው።

አጋር የሳራ ባሪያ የነበረች መሆኗ በእስማኤል ልጅነት ላይ የሚፈይደው አሉላዊ ቁብ የለውም። ለምሳሌ ባላን የራሔል ባሪያ ስትሆን ለያዕቆብ ግን ሚስት ነበረች፥ ከእርሷም የተወለዱት ዳን እና ንፍታሌም ሕጋዊ ልጆች ናቸው፦

ዘፍጥረት 30፥4 ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት።

በተጨማሪም ዘለፋ የልያ ባሪያ ስትሆን ለያዕቆብ ግን ሚስት ነበረች፥ ከእርሷም የተወለዱት ጋድ እና አሴር ሕጋዊ ልጆች ናቸው፦

ዘፍጥረት 30፥9 ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው።

ያዕቆብ አሥራ ሁለት ሕጋዊ ልጆች ያሉት ከባላን እና ከዘለፋ የወለዳቸውን ልጆች ጨምሮ እንደሆነ ሁሉ አብርሃምም ከሳራ ባሪያ ከሚስቱ ከአጋር የወለደው የበኲር ልጁም ሕጋዊ ልጁ ነው፦

ዘፍጥረት 17፥26 በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ እንዲሁ ልጁ እስማኤልም።
ዘፍጥረት 25፥9 ልጆቹ ይስሐቅ እና እስማኤል.....ቀበሩት።
ዘፍጥረት 16፥15 አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው።

ይህ የበኲር ልጅ እስማኤል ሁለተኛው ልጅ ይስሐቅ እስኪወለድ ድረስ የአብርሃም ብቸኛ ልጅ ነው፦

ዘፍጥረት 22፥16 እንዲህም አለው፦ ያህዌህ፦ በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ ብቸኛ ልጅህንም አልከለከልህምና። וַיֹּ֕אמֶר בִּ֥י נִשְׁבַּ֖עְתִּי נְאֻם־יְהוָ֑ה כִּ֗י יַ֚עַן אֲשֶׁ֤ר עָשִׂ֙יתָ֙ אֶת־הַדָּבָ֣ר הַזֶּ֔ה וְלֹ֥א חָשַׂ֖כְתָּ אֶת־בִּנְךָ֥ אֶת־יְחִידֶֽךָ׃

"ያኺድ" יָחִיד ማለት "ብቸኛ" ማለት ነው፥ እዚህ አንቀጽ ላይ የተቀመጠው ወሳኝ ቃል "ያኺድከ" יְחִידֶֽךָ ማለት "ብቸኛክ" ማለት ሲሆን የበኲር ልጅ ሌላ ልጅ እስኪወለድ ድረስ ለወላጅ ብቸኛ ልጅ ነው፦

ዘካርያስ 12፥10 ሰውም ለብቸኛ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል። אֲשֶׁר־דָּקָ֑רוּ וְסָפְד֣וּ עָלָ֗יו כְּמִסְפֵּד֙ עַל־הַיָּחִ֔יד וְהָמֵ֥ר עָלָ֖יו כְּהָמֵ֥ר עַֽל־הַבְּכֹֽור׃

እዚህ አንቀጽ ላይ የመጀመሪያ ልጅ ብቸኛ ልጅ መባሉን ልብ በል! ስለዚህ አብርሃም ሊሰዋ የነበረው የዕርዱ ልጅ የመጀመሪያ ልጁን ነው። ሲጀመር የዕርዱ ልጅ ይስሐቅ ቢሆን ኖሮ "ብቸኛ ልጅህን" የሚለው ትርጉም ይሰጣልን? ሲቀጥል ይስሐቅ ከመወለዱ በፊት አድጎ ዘር እንደሚኖረው ለአብርሃም ተነግሮታልም ያውቃልም፦

ዘፍጥረት 17፥19 ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ።

ታዲያ አብርሐም ልጁ ይስሐቅ ሳይወለድ ዘሩ እንደሚቀጥል እያወቀ ፈተና ነው ማለት ትርጉም ይኖረዋልን? ምክንያቱም ልጅህን ዕረድልኝ ፈተና ነው፥ ፈተና ትርጉም የሚኖረው ተፈታኙ የሚፈተነውን የማያውቅ ሲሆን ብቻ እና ብቻ ነው፦

ዘፍጥረት 22፥1 ከእነዚህም ነገሮች በኋላ ያህዌህ አብርሃምን "ፈተነው"።

በሙሴ ሕግ አስቀድሞ የተወለደው የበኲር ልጅ ለያህዌህ ይሆናል፥ የበኵር ልጅ በእርሱ ፋንታ እንስሳ ይታረዳል። ይህንን ሕግ አብርሃም ፈጽሞታል፦

ዘጸአት 13፥2 በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ የእኔ ነው።
ዘፍጥረት 26፥5 አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፥ ፍርዴን ትእዛዜን ሥርዓቴን "ሕጌንም ጠብቆአልና"።

አብርሃም ሕጉ ከጠበቀ የበኵር ልጁ ሊሰዋ ነበር ማለት ነው። አምላካችን አሏህ ሁሉንም ነገር ዐዋቂ ነው፥ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው ይህ አንዱ አምላክ ቁርኣንን ወደ ነቢያችን"ﷺ" አውርዷል፦

ቁርኣን 33፥54 አላህ ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ ነው።
فَإِنَّ اللَّهَ كَانَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا
ቁርኣን 25፥6 «ያ በሰማያትና በምድር ውስጥ ያለን ምስጢር የሚያውቀው አወረደው፡፡ እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና» በላቸው፡፡
قُلْ أَنزَلَهُ الَّذِي يَعْلَمُ السِّرَّ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ ۚ إِنَّهُ كَانَ غَفُورًا رَّحِيمًا

"ነበእ" نَبَأ የሚለው ቃል "ነበአ" نَبَّأَ ማለትም "አወራ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ነቢብ" "የሩቅ ወሬ" ማለት ነው፥ ከአሏህ ዘንድ የሩቅ ወሬ የሚወርድለት ሰው "ነቢይ" نَبِيّ ሲባል "ነባቢ" "የሩቅ ወሬ አውሪ" ማለት ነው። ከአሏህ ዘንድ ወደ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ከወረደው የሩቅ ወሬ አንዱ ስለ ኢብራሂም እና ስለ ቤተሰቡ ነው፦

ቁርኣን 26፥69 በእነርሱም ላይ የኢብራሂምን "ወሬ" አንብብላቸው፡፡
وَاتْلُ عَلَيْهِمْ نَبَأَ إِبْرَاهِيمَ
ቁርኣን 37፥102 ከእርሱ ጋርም ለሥራ በደረሰ ጊዜ «ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ?» አለው፡፡ «አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ሥራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ» አለ፡፡
فَلَمَّا بَلَغَ مَعَهُ ٱلسَّعْىَ قَالَ يَٰبُنَىَّ إِنِّىٓ أَرَىٰ فِى ٱلْمَنَامِ أَنِّىٓ أَذْبَحُكَ فَٱنظُرْ مَاذَا تَرَىٰ ۚ قَالَ يَٰٓأَبَتِ ٱفْعَلْ مَا تُؤْمَرُ ۖ سَتَجِدُنِىٓ إِن شَآءَ ٱللَّهُ مِنَ ٱلصَّٰبِرِينَ

ኢብራሂም ሊሰዋው የነበረው ልጅ ኢስማኤል እንደሆነ ከቁርኣን ብቻ ሳይሆን ከባይብልም መለኮታዊ ቅሪት ከላይ እንዳብራራነው እናገኛለን። አሏህ ሂዳያህ ይስጣቸው! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም