በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ ”እኔንም ብቻ አምልኩኝ”፡፡
يَٰعِبَادِىَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ إِنَّ أَرْضِى وَٰسِعَةٌۭ فَإِيَّٰىَ فَٱعْبُدُونِ

አምላካችን አሏህ መለኮት ነው፥ “መለኮት” ማለት ሁሉን ነገር የሚሰማ፣ ሁሉን ነገር የሚመለከት፣ ሁሉን ነገር የሚያውቅ፣ ሁሉን ነገር የፈጠረ፣ በሁሉን ነገር ላይ ቻይ ማለት ነው። እርሱ በእኔነት የሚናገር ነባቢና ሕያው መለኮት ነው፥ ብዙ አንቀጾች ላይ “አምልኩኝ” እያለ በመጀመሪያ መደብ ይናገራል፦

ቁርኣን 29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ ”እኔንም ብቻ አምልኩኝ”፡፡
يَٰعِبَادِىَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ إِنَّ أَرْضِى وَٰسِعَةٌۭ فَإِيَّٰىَ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 21፥92 ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፤ ”እኔም ጌታችሁ ነኝና አምልኩኝ”፡፡
إِنَّ هَٰذِهِۦٓ أُمَّتُكُمْ أُمَّةًۭ وَٰحِدَةًۭ وَأَنَا۠ رَبُّكُمْ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 21፥25 ከአንተ በፊትም እነሆ ”ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ” በማለት ወደ እርሱ ”የምናወርድለት” ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡
وَمَآ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِىٓ إِلَيْهِ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّآ أَنَا۠ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 51፥56 ጂኒን እና ሰውንም ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ

እኛ ሙሥሊም አሏህ ስናመልከው እርሱን እንዴት ማምለክ እንዳለብን በቅዱስ ቃሉ በቁርኣን ውስጥ እና በእርሱ ነቢይ ሐዲስ ውስጥ በተቀመጠልን መስፈርት ብቻ ነው። ይህንን ካወቅን ስለ ዋቄፈና ደግሞ በግርድፉና በሌጣው እንይ።

“ዋቄፈና” የሚለው ቃል “ዋቃ” ማለትም “አምላክ” ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን የእምነቱ ስም ነው፥ ይህንን እምነት የሚከተል ሰው ደግሞ “ዋቄፈታ” ይባላል። “ኢሬቻ” ማለት “ምስጋና” ወይም “አምልኮ” ማለት ሲሆን “ገልማ” ማለትም “ቤተ-አምልኮ” ውስጥ በጭፈራዎቹና በፌሽታዎች የሚከበር በዓል ነው፥ ኢሬቻን የምትለዋ ቃል የምትወክለው እርጥብ ሣር ወይም አበባ በማቅረብ “መሬሆ” ማለትም “መዝሙር” መዘመሩን ነው። ይህንን አምልኮ የሚፈጽሙ ምዕመናኑ “ሚሤንሣ” ሲባሉ እምነቱን የሚመሩት ካህናቱ “ቃሉ” ይባላሉ፥ ፓለቲካውን “ሲርነ ገዳ” ሲባል ፓለቲካውን የሚመሩት መሪዎች ደግሞ “አባ ገዳ” ይባላሉ።

ይህ እምነት አምልኮውን የሚፈጽመው በተራራ እና በሐይቅ ወዘተ ነው፥ “ቱሉ” ማለት “ተራራ” ማለት ሲሆን “ቱሉ ጩቋላ(የዝቋላ ተራራ) እና “ቱሉ ፊሪ” “ቱሉ ኤረር” እየተባለ ወደ ስምንት ተራሮች ላይ አምልኮ ይፈጸማል። “ሆረ” ማለት “ሃይቅ” ማለት ሲሆን፦ “ሆረ አርሰዴ” “ሆረ ፊንፊኔ” “ሆረ ኪሎሌ” እየተባሉ ሰባቱ የዋቃ ሃይቆች ላይ አምልኮ ይፈጸማል፥ ይህ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል።

ይህ እምነት ታሪካዊ ዳራው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3000 ቅድመ-ልደት እንደተጀመረ እና ጅምሩ የአንድ አምላክ አስተምህሮት እንደነበር ይገመታል ይነገራል። እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ 2007 ድህረ-ልደት በተደረገው የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ከኦሮሞ ሕዝብ ወደ 3.3 በመቶ የሚደርሰው ሕዝብ የዚህ እምነት ተከታይ ነበር፥ በአሁኑ ጊዜ ይሄ ቁጥር ወደ 3 በመቶ ዝቅ እንዳለ ይነገራል። አንዳንዶች ደግሞ፦ “አብዛኛው ዋቄፈናን ከእሥልምና ጋር ወይንም ከክርስትና ጋር ቀይጦ ነው የሚያመልከው” ይላሉ፥ ይህ ስህተት ነው። ምክንያቱም የሚያመልኩት ዋቃ አንድም ቀን እንዴት መመለክ እንዳለበት አልነገራቸውም፥ ደግሞም “አይናገርምም” ይላሉ። እነርሱም ባወጡት ሰው ሠራሽ አምልኮ ያመልኩታል፥ ይህ ደግሞ ቢድዓህ ነው። እዚህ አምልኮ ውስጥ ለወንዙ፣ ለተራራው፣ ለሃይቁ የሚደረገው የሁሉ አምላክነት”Pantheism” እሳቤ ሺርክ ነው፥ በዚህ አምልኮ ውስጥ ልመና፣ ምስጋና፣ ስለት፣ ስግደት የመሳሰሉት ይካሄዳሉ። ዛፍ ቅቤ በመቀባት መለማመን፣ ማመስገን፣ መሳል፣ መስገድ ባዕድ አምልኮ ካልሆነ ምንድን ነው? እንደውም “ቃሊቻ” የሚለው ቃል የተገኘው “ቃሉ” ከሚለው እንደሆነም ይነገራል፥ “ቃሉ” የተባሉት መሪዎች ከአጋንንት ጋር እየተነጋገሩ ሺርክ እንደሚያደርጉ የዚህ ባዕድ አምልኮ ነጻ የወጡ ሰዎች ይናገራሉ።

ስለዚህ እዚህ እምነት ውስጥ ያላችሁ ዋቄፈታዎች የነቢያት አምላክ የሆነውን አንዱን አምላክ አሏህን ብቻ በብቸኝነት እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው፥ ሙሥሊሞች ሆናችሁ ይህንን በዓል ባለማወቅ የምታከብሩምና የምታመልኩ ካላችሁ በንስሐ ወደ አሏህ ተመለሱ! አሏህ ወደ እርሱ በመጸጸት ለሚመለሱት ይቅር ባይና አዛኝ ነው፦

ቁርኣን 2፥160 እነዚያ ከመደበቅ የተጸጸቱና ሥራቸውን ያሳመሩም የደበቁትን የገለጹም ብቻ ሲቀሩ፡፡ እነዚህም በእነርሱ ላይ ጸጸታቸውን እቀበላለሁ፤ እኔም ጸጸትን በጣም ተቀባይ አዛኙ ነኝ፡፡
إِلَّا الَّذِينَ تَابُوا وَأَصْلَحُوا وَبَيَّنُوا فَأُولَـٰئِكَ أَتُوبُ عَلَيْهِمْ ۚ وَأَنَا التَّوَّابُ الرَّحِيمُ

ስለ ዋቄፈና ዋቢ መጽሐፍት፦

  1. Mulugeta Jaleta Gobenooromo; Indiginious Religion: Anthroplogical Understanding of Waaqeffanna-Nature Link, With Highlight on Livelihood in Guji Zone, Adola Redde and Girja Districts, A thesis submitted to the department of Social Anthropology, College of Social Science Addis Ababa University, June 2017,
  2. Census (PDF), Ethiopia, 2007,
  3. Workinesh Kelbessa, Traditional Oromo Attitudes towards the Environment, Social Science Research Report Series.

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም