በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 23፥100 ከስተፊታቸውም እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ "ግርዶ" አለ፡፡
وَمِن وَرَائِهِم بَرْزَخٌ إِلَىٰ يَوْمِ يُبْعَثُونَ

በኢሥላም ስለ በርዘኽ ያለው እሳቤ ከብዙ በጥቂቱ አይተን ነበር። በባይብልም ደግሞ ስለ በርዘኽ እንዲህ ይናገራል፦

ሉቃስ 16፥26 ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛ እና በእናንተ መካከል ታላቅ "ገደል" ተደርጎአል" አለ።

የገነት ሰዎች ከሲኦል ሰዎች እንዳይተላለፉ እና እንዳይሻገሩ በመካከላቸው ያለው ገደል ምንድን ነው? ባለ ጠጋው በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ ማየቱ በራሱ ሲኦል እና ገነት ከሞት በኃላ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ ጊዜአዊ መቆያ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ገደል በርዘኽ ነው፦

ሉቃስ 16፥22 ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት።
ሉቃስ 16፥23 ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ፥ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ።

"መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት" የሚለው በራሱ ልክ እንደ አን ናዚዓት እና አን-ናሺጧት መላእክት መኖራቸውን ጉልኅ ማሳያ ነው፥ አብርሃም ያለበት ስፍራ ደግሞ ገነት ነው፦

1ኛ መቃብያን 3፥38 መላእክትም የጣሉዋቸው ሰዎች ሲያዩ ተቀብለው ነፍሳቸውን ይስሐቅ፣ አብርሃም፣ ያዕቆብ ወዳሉበት ተድላ እና ደስታ ወደሚገኝበት ወደ ገነት ወሰዷቸው።
1ኛ መቃብያን 6፥2 የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርገዋልና ይስሐቅ፣ አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ሰሎሞን፣ ዳዊት እና ሕዝቅያስ ማደሪያቸው ብርሃን የሆነች እና ያማሩ ነገሥታት ሁሉ ባሉበት በገነት ማደሪያቸውን በማይመረመር ብርሃን ያበራል ።

"በአዳም የተነሳ ሁሉም ነፍሳት ሲኦል ገብተው ኢየሱስ ከሲኦል አወጣቸው" የሚለው ትምህርት ባይብላዊ ማስረጃ የሌለው ከመሆንም ባሻገር ከመቃብያን አሳብ ጋር ይጋጫል። ድሀው ሲሞት የሄደበት የአብርሃም እቅፍ ገነት ከተባለ እና ባለ ጠጋው ሲሞት የሄደበት ሲኦል ከተባለ፣ ባለ ጠጋው በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አልዓዛርንም በእቅፉ ካየ፣ አብርሃም በገነት ባለ ጠጋው በሲኦል ሆነው የንግግር ልውጥውጥ ካደረገ እና ሁለቱ እንዳይገናኙ ገደል ካለ ለምን ይሆን ክርስቲያን ሚሽነሪዎች በኢሥላም ያለውን የበርዘኽ እሳቤ የሚሳለቁበት? ስንል ሚሽነሪዎች የራሳቸውን መጽሐፍ ጠንቅቀው አለማወቃቸውን እያሳበቀባቸው ነው። የሁሉም ሰው መንፈስ ወደ ፈጣሪ ይመለሳል፦

መክብብ 12፥7 አፈርም(ሥጋም) ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ አምላክ ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። וְיָשֹׁ֧ב הֶעָפָ֛ר עַל־הָאָ֖רֶץ כְּשֶׁהָיָ֑ה וְהָר֣וּחַ תָּשׁ֔וּב אֶל־הָאֱלֹהִ֖ים אֲשֶׁ֥ר נְתָנָֽהּ׃

ከአፈር የመጣው ሥጋ ወደ አፈር ሲመለስ መንፈስ ደግሞ ወደ አምላክ ይመለሳል። "ሩአሕ" רוּחַ ማለት "መንፈስ" ማለት ሲሆን በቁርኣን መንፈስ በእሳት ሲቀጣ "በእኛ ላይ ከውኃ አፍስሱብን" ማለታቸውን ስትሳለቁ በባይብል መንፈስ በእሳት ሲቀጣ "በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ" ማለቱን ስታውቁ ምን ይውጣችሁ ይሆን? "እሳት፣ ውኃ፣ ጣት፣ ምላስ የሩቅ ነገር ምሥጢር ናቸው" ካላችሁ እንግዲያውስ ውኃ እና እሳት የሩቅ ነገር ምሥጢር ናቸው፦

ሉቃስ 16፥24 እርሱም እየጮኸ፦ "አብርሃም አባት ሆይ! ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ" አለ።

አምላካችን አሏህ ከእሳት ቅጣት ይጠብቀን! የጀነት ያድርገን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም