በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 33፥56 አላህ እና መላእክቱ በነቢዩ ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ፡፡
إِنَّ اللَّهَ وَمَلَائِكَتَهُ يُصَلُّونَ عَلَى النَّبِيِّ

አንድ ቃል ቋንቋዊ ፍቺው "መዕና ሉገዊይ" مَعْنًى لُغَوِيّ ሲባል ሸሪዓዊ ፍቺው ደግሞ "መዕና ሸርዒይ" مَعْنًى شَرْعِيّ ይባላል፥ አንድ ቃል ቋንቋዊ ፍቺው ሆነ ሸሪዓዊ ፍቺው ብዙ ትርጉም ይይዛል። ለምሳሌ፦ "በዐሰ" بَعَثَ ማለት "ላከ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 25፥41 ባዩህም ጊዜ ያ አላህ መልእክተኛ አድርጎ የላከው ይህ ነውን እያሉ መሳለቂያ እንጂ ሌላ አያደርጉህም፡፡
وَإِذَا رَأَوْكَ إِن يَتَّخِذُونَكَ إِلَّا هُزُوًا أَهَـٰذَا الَّذِي بَعَثَ اللَّهُ رَسُولًا

እዚህ አንቀጽ ላይ "ላከ" ለሚለው የገባው ቃል "በዐሰ" بَعَثَ ሲሆን "አርሠለ" أَرْسَلَ ማለት ነው፥ ነገር ግን "በዐሰ" بَعَثَ ማለት "ቀሰቀሰ" ወይም "አስነሳ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 36፥52 «ወይ ጥፋታችን! ከመኝታችን ማን ቀሰቀሰን? ይህ ያ አዛኙ ጌታ በእርሱ የቀጠረን መልክተኞቹም እውነትን የነገሩን ነው» ይላሉ፡፡
قَالُوا يَا وَيْلَنَا مَن بَعَثَنَا مِن مَّرْقَدِنَا ۜ ۗ هَـٰذَا مَا وَعَدَ الرَّحْمَـٰنُ وَصَدَقَ الْمُرْسَلُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ቀሰቀሰ" ለሚለው የገባው ቃል "በዐሰ" بَعَثَ ሲሆን "አስነሳ" ማለት ነው፥ ስለዚህ "አላህ መልእክተኛ አድርጎ የቀሰቀሰው ይህ ነው" ወይም "ወይ ጥፋታችን! ከመኝታችን ማን ላከን" ብለን ብናስቀምጠው ትርጉም አልባ ነው። ሌላ ምሳሌ፦ "ሠበሐ" سَبَّحَ ማለት "አሞገሰ" "አመሰገነ" "አጠራ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 21፥20 በሌሊት እና በቀንም "ያጠሩታል"፤ አያርፉም፡፡
يُسَبِّحُونَ اللَّيْلَ وَالنَّهَارَ لَا يَفْتُرُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ያጠሩታል" ለሚለው የገባው ቃል "ዩሠቢሑነ" يُسَبِّحُونَ ሲሆን ሥርወ-ቃሉ "ሠበሐ" سَبَّحَ ነው፥ ነገር ግን "ሠበሐ" سَبَّحَ ማለት "ዋኘ" ወይም "ተንቀሳቀሰ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 21፥33 እርሱም ሌሊትንና ቀንን፣ ፀሐይንና ጨረቃንም የፈጠረ ነው፡፡ ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ "ይዋኛሉ"፡፡
وَهُوَ الَّذِي خَلَقَ اللَّيْلَ وَالنَّهَارَ وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ ۖ كُلٌّ فِي فَلَكٍ يَسْبَحُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ይዋኛሉ" ለሚለው የገባው ቃል "የሥበሑነ" يَسْبَحُونَ ሲሆን ሥርወ-ቃሉ "ሠበሐ" سَبَّحَ ነው፥ ስለዚህ "በሌሊት እና በቀንም "ይዋኙታል" ወይም "ሁሉም በፈለካቸው ውስጥ "ያጠራሉ" ብለን ብናስቀምጠው ትርጉም አልባል ነው። አንድ ቃል ብዙ ትርጉም እንዳለው እዚህ ድረስ ከተግባባን ዘንዳ ይህ በነሕው ደርሥ "ኢሥሙል ሙሽተሪክ" ይባላል፥ "ኢሥሙል ሙሽተሪክ" اِسْم المُشْتَرِك ማለት "ተመሳሳይ ቃል ግን የተለያየ ትርጉም ያለው አሳብ"Homonym" ነው። "ሶላ" صَلَّىٰ ማለት "ሰገደ" "ጸለየ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 87፥15 የጌታውንም ስም ያወሳ እና "የሰገደ"፡፡
وَذَكَرَ اسْمَ رَبِّهِ فَصَلَّىٰ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሰገደ" ለሚለው የገባው ቃል "ሶላ" صَلَّىٰ ሲሆን የአምልኮ ክፍል የሆነውን ሶላት ያመላክታል፥ ነገር ግን "ሶላ" صَلَّىٰ ማለት "ባረከ" ማለት ነው፦

ቁርኣን 33፥56 አላህ እና መላእክቱ በነቢዩ ላይ የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ፡፡
إِنَّ اللَّهَ وَمَلَائِكَتَهُ يُصَلُّونَ عَلَى النَّبِيِّ

"የአክብሮት እዝነትን ያወርዳሉ" ለሚለው የገባው ቃል "ዩሶሉነ" يُصَلُّونَ ሲሆን "ይባርካሉ" ማለት ነው፥ ዐረቢኛ ላይ ተመሳሳይ ቃል ቢኖረው እንኳን ተመሳሳይ አሳብ እና ትርጉም አለው ማለት አይደለም። የአንድን ቃል አማራጭ ትርጉም የሚወስነው ቃሉ የሚገኝበት አረፍተ ነገር ወይም ዐውድ እንደ ሆነ ቅቡል ነው፥ መታየት ያለበት ቃሉ ብቻ ሳይሆን ቃሉ የወከለው አሳብም ጭምር ነው። አሏህ እና መላእክቱ ሶለዋትን የሚያወርዱት በነቢያችን"ﷺ" ብቻ ሳይሆን በአማኞችም ላይ ጭምር ነው፦

ቁርኣን 33፥43 እርሱ ያ “በእናንተ “ላይ” እዝነትን” የሚያወርድ ነው፡፡ መላእክቶቹም እንደዚሁ፡፡
هُوَ الَّذِي يُصَلِّي عَلَيْكُمْ وَمَلَائِكَتُهُ

"እዝነትን የሚያወርድ" ለሚለው የገባው ቃል በተመሳሳይ "ዩሶሊ" يُصَلِّي ነው፥ አንድ አማኝ በነቢያችን"ﷺ" ላይ ሶለዋት ሲያወርድ አሏህ በእርሱ ላይ አሥር ሶለዋት ያወርድለታል፦

ቁርኣን 33፥56 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በእርሱ ላይ የአክብሮት እዝነትን አውርዱ፡፡ የማክበርንም ሰላምታ ሰላም በሉ፡፡
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا صَلُّوا عَلَيْهِ وَسَلِّمُوا تَسْلِيمًا
ጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 3, ሐዲስ 33
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ ”በእኔ ላይ ሶለዋት ያወረደ አሏህ በእርሱ ላይ አሥር ሶለዋት ያወርድለታል”።
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ مَنْ صَلَّى عَلَىَّ صَلاَةً صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ بِهَا عَشْرًا ‏

እንደ ሚሽነሪዎች መጃጃል "አሏህ እና መላእክቱ ወደ ነቢዩ ይጸልያሉ ወይም ለነቢዩ ይሰግዳሉ" ካሉ አሏህ እና መላእክቱ ወደ አማኞች ሶለዋት ማውረዳቸውን ሲያውቁ "ወደ አማኞች ይጸልያሉ ወይም ለአማኞች ይሰግዳሉ" ብለው ሊረዱት ነው? "አንድ ቃልን ለሁለት የተለያዩ ነገሮችን የሚውለውን"two different things by the same word" አንድ ነገር አርጎ መውሰድ "አሻሚ ሕፀፅ"fallacy of equivocation" ነው። ለምሳሌ፦
premise 1
Since only man is rational.
premise 2
And no woman is a man.
conclusion
Therefore, no woman is rational.

ብሎ መተርጎም አሻሚ ሕፀፅ ነው፥ በ 1ኛው ነጥብ "Man" የተባለው "ሰው"human" ሲሆን በ 2ኛው "Man" የተባለው "ወንድ"male" ነው፥ ስለዚህ አንድ ቃልን ለሁለት የተለያዩ ነገሮችን ወክሎ የሚውለውን በተቃራኒው "Man" የሚለውን "ወንድ" ብቻ ብለን ተርጉመን፦ "ወንድ ብቻውን ዐቅለኛ ነው፣ ሴት ወንድ አይደለችም፣ ስለዚህ ሴት ዐቅለኛ አይደለችም" ብሎ መረዳት በሥ-አመክንዮ ሙግት አሻሚ ሕፀፅ ነው። በተመሳሳይም "ሶላ" صَلَّىٰ ማለት "ባረከ" ማለትም ሆኖ ሳለ "ሰገደ "ጸለየ" ማለት ብቻ አርጎ መረዳት ክፉኛ ተፋልሶ"fallacy" ነው፦

ሡነን አቢ ዳውድ መጽሐፍ 8, ሐዲስ 118
ጃቢር ኢብኑ ዐብደሏህ እንደተረከው፦ "አንዲት ሴት ለነቢዩ"ﷺ" እንዲህ አለች፦ "በእኔ ላይ እና በባለቤቴ ላይ ሶላዋት አውርዱ" ነቢዩም"ﷺ"፦ "አሏህ በአንቺ ላይ እና በባለቤትሽ ላይ ሶላዋት ያውርድ" አሉ።
عَنْ جَابِرِ بْنِ عَبْدِ اللَّهِ، أَنَّ امْرَأَةً، قَالَتْ لِلنَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم صَلِّ عَلَىَّ وَعَلَى زَوْجِي ‏.‏ فَقَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْكِ وَعَلَى زَوْجِكِ ‏"‏ ‏.‏

"ሶላ" صَلَّىٰ ማለት "ባረከ" ማለት ባይሆን ኖሮ ባርኩኝ ሲባሉ አሏህ ይባርክሽ ይሉ ነበር? ይህ መደበኛ ሕፀፅ"formal fallacy" ያለበት ኢ-ምንጨታዊ ሙግት"inductive argument" ነው፥ ምክንያቱም ሙግቱ ድምዳሜ ለማጽናት እክል ያጋጠመው ስለሆነ ነው። ቅሉ እና ጥቅሉ ግን በዚህ ዐውድ ላይ "ሶለዋት" صَلَوَات የሚለው ቃል "በረካት" بَرَكَات የሚለውን ቃል ተክቶ የመጣ ነው፥ አባሪ ናሙና እስቲ እንመልከት፦

ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 60, ሐዲስ 48
አቡ ሑመይድ አሥ-ሣዒዲይ”ረ.ዐ” እንደተረከው፦ "ሰዎች፦ “የአሏህ መልእክተኛ”ﷺ” ሆይ! በእርሶ ላይ እንዴት ሶለዋት እናውርድ? አሉ፥ የአሏህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “አሏህ ሆይ! ሶለዋትን በኢብራሂም ቤተሰብ ላይ እንዳወረድክ ሶለዋትን በሙሐመድ፣ በባልተቤቶቹ እና በዝርዮቹ ላይ አውርድ! በረካትን በኢብራሂም ቤተሰብ ላይ እንዳወረድክ በሙሐመድ፣ በባልተቤቶቹ እና በዝርዮቹ ላይ አውርድ! አንተ የተመሰገንክ እና የተከበርክ ነህ" በሉ።
أَخْبَرَنِي أَبُو حُمَيْدٍ السَّاعِدِيُّ ـ رضى الله عنه ـ أَنَّهُمْ قَالُوا يَا رَسُولَ اللَّهِ كَيْفَ نُصَلِّي عَلَيْكَ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ قُولُوا اللَّهُمَّ صَلِّ عَلَى مُحَمَّدٍ وَأَزْوَاجِهِ وَذُرِّيَّتِهِ، كَمَا صَلَّيْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، وَبَارِكْ عَلَى مُحَمَّدٍ وَأَزْوَاجِهِ وَذُرِّيَّتِهِ، كَمَا بَارَكْتَ عَلَى آلِ إِبْرَاهِيمَ، إِنَّكَ حَمِيدٌ مَجِيدٌ ‏”‌‏.‏

ምን ትፈልጋለህ? እዚህ ዐውድ ላይ “ሶለይተ” صَلَّيْتَ የሚለው ቃል “ባረክተ” بَارَكْتَ በሚል ተለዋዋጭ ቃል መምጣቱ በራሱ ሶለዋት በረካት መሆኑን ያሳያል፥ አሏህ ሶለዋት የሚያወርደው በነቢያችን”ﷺ” ብቻ ሳይሆን በባልተቤቶቻቸው ላይ እና በዝርያወቻቸው ላይ ጭምር መሆኑ በራሱ ሶለዋት ቡራኬን ያሳያል።
በተጨማሪም “ወደ” የሚለው መስተዋድድ “ኢላ” إِلَى ሲሆን ለቡራኬ ጥቅም ላይ አልዋለም፥ ለቡራኬ የዋለው መስተዋድድ “ዐላ” عَلَى ማለትም “ላይ” ነው። “ላይ” ደግሞ ለሰላም፣ ለእዝነት እና ለበረከት የሚውል መስተዋድድ ነው፦

ቁርኣን 11፥73 «ከአላህ ትዕዛዝ ትደነቂያለሽን የአላህ ራህመት እና በረካት በእናንተ እና በኢብራሂም ቤተሰቦች “ላይ” ይሁን! እርሱ ምስጉን ለጋስ ነውና» አሉ፡፡
قَالُوا أَتَعْجَبِينَ مِنْ أَمْرِ اللَّهِ ۖ رَحْمَتُ اللَّهِ وَبَرَكَاتُهُ عَلَيْكُمْ أَهْلَ الْبَيْتِ ۚ إِنَّهُ حَمِيدٌ مَّجِيدٌ
ቁርኣን 11፥48 «ኑሕ ሆይ! ከእኛ በሆነ ሰላም እና በረካት በአንተ “ላይ” እና አንተም ጋር ባሉት ሕዝቦች “ላይ” በሆኑ የተጎናጸፍክ ሆነህ ውረድ፡
قِيلَ يَا نُوحُ اهْبِطْ بِسَلَامٍ مِّنَّا وَبَرَكَاتٍ عَلَيْكَ وَعَلَىٰ أُمَمٍ مِّمَّن مَّعَك

ስለዚህ "በነቢዩ ላይ" የሚለውን "ወደ ነቢዩ" ወይም "ለነቢዩ" ብሎ መረዳት ጥራዝ ጠለቅ መረዳት ሳይሆን ጥራዝ ነጠቅ መረዳት ነው፦

ቁርኣን 108፥2 ስለዚህ "ለ-ጌታህ ስገድ" ሰዋም፡፡
فَصَلِّ لِرَبِّكَ وَانْحَرْ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ስገድ" ለሚለው የገባው የግሥ መደብ "ሶል" صَلِّ ሲሆን ለአሏህ የሚቀርብ የአምልኮ ክፍል የሆነውን ሶላት የሚያመለክት ነው፥ የገባውም መስተዋድድ "ሊ" لِ እንጂ "ዐላ عَلَى አይደለም። ሆን ብሎ ማጣመም ዋጋ ያስከፍላል፥ የቁያማህ ቀንም ያስጠይቃል። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

"አሏሁመ ሶሊ ዐላ ሙሐመድ ወአሊ ሙሐመድ" ٱللّٰهُمَّ صَلِّ عَلَى مُحَمَّدٍ وَآلِ مُحَمَّدٍ
"ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሠለም" صَلَّى ٱللَّٰهُ عَلَيْهِ وَسَلَّم

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
ወሠላሙ ዐለይኩም