በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 2፥190 እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና፡፡
وَقَاتِلُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ الَّذِينَ يُقَاتِلُونَكُمْ وَلَا تَعْتَدُوا ۚ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ
“ጀናህ” جَنَّة የሚለው ቃል በነጠላ ሲሆን በብዙት ደግሞ “ጀናት” جَنَّات ነው፥ ትርጉሙ "ገነት" ማለት ሲሆን እንደየ ዐውዱ የተለያየ ትርጉም አለው። ለምሳሌ “ጀናህ” جَنَّة የሚለው ቃል “አትክልት” በሚል መጥቷል፦
ቁርኣን 13፥4 በምድርም የተጎራበቱ ቁርጥራጮች አሉ፥ ከወይኖችም “አትክልቶች” አዝርዕቶችም መንታዎችና መንታዎች ያልኾኑ ዘንባባዎችም አሉ። በአንድ ውሃ ይጠጣሉ”።
وَفِي الْأَرْضِ قِطَعٌ مُّتَجَاوِرَاتٌ وَجَنَّاتٌ مِّنْ أَعْنَابٍ وَزَرْعٌ وَنَخِيلٌ صِنْوَانٌ وَغَيْرُ صِنْوَانٍ يُسْقَىٰ بِمَاءٍ وَاحِدٍ
እዚህ አንቀጽ ላይ “አትክልቶች” ለሚለው የገባው ቃል “ጀናት” جَنَّات መሆኑን አንባቢ ልብ ይለዋል፥ “ጀናህ” جَنَّة ማለት "መልካም ነገር" በሚል ትርጉም ይመጣል፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 55, ሐዲስ 1
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ዱንያህ ለሙእሚን እስር ቤት ናት፥ ለካፊር ደግሞ ጀናህ ናት"።
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم " الدُّنْيَا سِجْنُ الْمُؤْمِنِ وَجَنَّةُ الْكَافِرِ "
"ዱንያህ ለካፊር ደግሞ ጀናህ ናት" ማለት "መልካም ነገር ናት" "ምቾት ናት" ድሎት ናት" ማለት እንጂ በትንሳኤ ቀን አሏህ ለባሮቹ ያዘጋጃት ጸጋ ናት ማለት በፍጹም አይደለም። በተቃራኒው ዱንያህ "ለሙእሚን እስር ቤት ናት" ይላል፥ "ሢጂን" سِجِّين ወይም "ሢጅን" سِجْن ማለት "እስር ቤት" ማለት ሲሆን በጀሀነም ያለው እስር ቤት በትንሳኤ ቀን አሏህ ለኩፋሮች ያዘጋጀው እስር ቤት ማለት ሳይሆን ክፉ ነገርን ለማመልከት የመጣ ቃል ነው፦
ቁርኣን 83፥7 *"በእውነት የአመጸኞቹ መጽሐፍ በእርግጥ በሲጂን ውስጥ ነው"፡፡
كَلَّا إِنَّ كِتَابَ الْفُجَّارِ لَفِي سِجِّينٍ
እዚህ አንቀጽ ላይ በትንሳኤ ቀን አሏህ ለኩፋሮች በጀሀነም ውስጥ ያዘጋጀው እስር ቤት "ሢጂን" سِجِّين መባሉን ልብ አድርግ!
"ናር" نَّار እንዲሁ "መጥፎ ነገርን" ለማመልከት መጥቷል። ለምሳሌ እሳት በዝንባሌ ዙሪያ ሲሆን ከጫማው የቆዳ ማሰሪያ ይልቅ ቅርብ ነው፥ በተቃራኒው ጀናህ ከዝንባሌ በመላቀቅ ዙሪያ ስትሆት ከጫማው የቆዳ ማሰሪያ ይልቅ ቅርብ ናት፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 81, ሐዲስ 77
ዐብደሏህ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ጀናህ ከእናንተ መካከል ከጫማው የቆዳ ማሰሪያ ይልቅ ቅርብ ናት፥ በተመሳሳይም እሳት ከጫማው የቆዳ ማሰሪያ ይልቅ ቅርብ ነው"።
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ ـ رضى الله عنه ـ قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم " الْجَنَّةُ أَقْرَبُ إِلَى أَحَدِكُمْ مِنْ شِرَاكِ نَعْلِهِ، وَالنَّارُ مِثْلُ ذَلِكَ ".
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 81, ሐዲስ 76
አቢ ሁራይራህ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "እሳት በዝንባሌዎች ዙሪያ ነው፥ ጀናህ ደግሞ በመላቀቅ ዙሪያ ናት"።
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم قَالَ " حُجِبَتِ النَّارُ بِالشَّهَوَاتِ، وَحُجِبَتِ الْجَنَّةُ بِالْمَكَارِهِ ".
መሢሑ አድ-ደጃል በመጨረሻው ዘመን ሲመጣ ከእርሱ ጋር ጀናህ እና እሳት አለ፥ ግን እሳቱ ጀናህ እንዲሁ ጀናው እሳት ነው። ያ ማለት እርሱ መልካም ነገር አድርጎ የሚያቀርበው ነገር ሁሉ መጥፎ ነገር ነው፥ እርሱ መጥፎ ነገር አድርጎ የሚያቀርበው ነገር ሁሉ መልካም ነገር ነው ማለት ነው እንጂ በትንሳኤ ቀን አሏህ ለባሮቹ ያዘጋጃት ጀናት እና ለአመጸኞች ያዘጋጀው እሳት በእጁ ነው ማለት አይደለም፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 36, ሐዲስ 146
ሑዘይፋህ እንደተረከው፦ የአሏህም መልእክተኛ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ደጃል የግራ ዓይኑ ዕውር ነው፥ የተትረፈረፈ ጸጉር አለው። ከእርሱ ጋር ጀናህ እና እሳት አለ፥ ግን እሳቱ ጀናህ እንዲሁ ጀናው እሳት ነው"።
عَنْ حُذَيْفَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ " الدَّجَّالُ أَعْوَرُ عَيْنِ الْيُسْرَى جُفَالُ الشَّعَرِ مَعَهُ جَنَّةٌ وَنَارٌ فَنَارُهُ جَنَّةٌ وَجَنَّتُهُ نَارٌ " .
የማንኛውም ሰው የመጀመሪያ ቋንቋ "እናት ቋንቋ" ይባላል፥ እናት የመጀመሪያዋ ትምህርት ቤት ናት። እናት ሥር መልካም ነገር ሁሉ ስላለ ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ"፦ "ጀናህ እናት እግር ሥር ናት" ብለውናል፦
ሡነን አን-ነሣኢይ መጽሐፍ 25, ሐዲስ 20
ሙዓዊያህ ኢብኑ ጃሂማህ አሥ-ሡለሚይ እንደተረከው፦ "ጃሂማህ ወደ "ነቢዩ"ﷺ" መጥቶ እንዲህ አለ፦ "የአሏህ መልእክተኛ ሆይ! መውጣት እና መጋደል እፈልጋለው፥ ምክርዎን ፈልጌ መጥቻለው"፥ እርሳቸውም፦ "እናት አለክን? አሉት። እርሱም፦ "አዎ" አለ፥ እርሳቸውም፦ "ከእርሷ ጋር ቆይ! ጀናህ እናት እግር ሥት ናት" አሉት።
عَنْ مُعَاوِيَةَ بْنِ جَاهِمَةَ السُّلَمِيِّ، أَنَّ جَاهِمَةَ، جَاءَ إِلَى النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم فَقَالَ يَا رَسُولَ اللَّهِ أَرَدْتُ أَنْ أَغْزُوَ وَقَدْ جِئْتُ أَسْتَشِيرُكَ . فَقَالَ " هَلْ لَكَ مِنْ أُمٍّ " . قَالَ نَعَمْ . قَالَ " فَالْزَمْهَا فَإِنَّ الْجَنَّةَ تَحْتَ رِجْلَيْهَا " .
እዚህ ድረስ ከተግባባ ዘንዳ እነዚያንም ወሰን አልፈው የሚጋደሉትን በአሏህ መንገድ መጋደል ሰላም እና መልካም ነገር ያመጣል፥ ለእነዚያ ለሚገደሉት ምእመናን እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው መጋደል የተፈቀደው ይህንን መልካም ነገር ስለሚያመጣ ነው፦
ቁርኣን 2፥190 እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን በአላህ መንገድ ተጋደሉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና፡፡
وَقَاتِلُوا فِي سَبِيلِ اللَّهِ الَّذِينَ يُقَاتِلُونَكُمْ وَلَا تَعْتَدُوا ۚ إِنَّ اللَّهَ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ
ቁርኣን 22፥39 ”ለእነዚያ ለሚገደሉት ምእመናን እነርሱ የተበደሉ በመኾናቸው መጋደል ተፈቀደላቸው፡፡ አላህም እነርሱን በመርዳት ላይ በእርግጥ ቻይ ነው”፡፡
أُذِنَ لِلَّذِينَ يُقَاتَلُونَ بِأَنَّهُمْ ظُلِمُوا ۚ وَإِنَّ اللَّهَ عَلَىٰ نَصْرِهِمْ لَقَدِيرٌ
ቁርኣን 22፥40 "አላህ ሰዎችን ከፊላቸውን በከፊሉ መገፍተሩ ባልነበረ ኖሮ ገዳማት፣ ቤተክርስቲያናት፣ ምኩራቦች እና በውስጣቸው የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጊዶችም በተፈረሱ ነበር"፡፡
وَلَوْلَا دَفْعُ اللَّهِ النَّاسَ بَعْضَهُم بِبَعْضٍ لَّهُدِّمَتْ صَوَامِعُ وَبِيَعٌ وَصَلَوَاتٌ وَمَسَاجِدُ يُذْكَرُ فِيهَا اسْمُ اللَّهِ كَثِيرًا
ወሰን በሚያልፉት ሰዎች ላይ ወሰን ማለፍ ከሌለ ወሰን አላፊዎች ገዳማትን፣ ቤተክርስቲያትን፣ ምኩራቦችን እና በውስጣቸው የአሏህ ስም በብዛት የሚወሳባቸው መስጊዶችን አፍርሰው ይጨርሱ ነበር፥ ለዚያ ነው ተወጃጁ ነቢያችን"ﷺ"፦ "ሰዎች ሆይ! ጠላትን በጦርነት መግጠምን አትመኙ! ሰላምን እንዲሰጣችሁ አሏህን ጠይቁት! የግድ ሆኖ ጠላትን በገጠማችኋቸው ጊዜ ግን ታገሱ!" ያሉት፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 32, ሐዲስ 23
አቢ ነድር እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ሰዎች ሆይ! ጠላትን በጦርነት መግጠምን አትመኙ! ሰላምን እንዲሰጣችሁ አሏህን ጠይቁት! የግድ ሆኖ ጠላትን በገጠማችኋቸው ጊዜ ግን ታገሱ! ጀናህ በሰይፍ ጥላ ሥር መሆኗን ዕወቁ!"።
عَنْ أَبِي النَّضْرِ، فَقَالَ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم " يَا أَيُّهَا النَّاسُ لاَ تَتَمَنَّوْا لِقَاءَ الْعَدُوِّ وَاسْأَلُوا اللَّهَ الْعَافِيَةَ فَإِذَا لَقِيتُمُوهُمْ فَاصْبِرُوا وَاعْلَمُوا أَنَّ الْجَنَّةَ تَحْتَ ظِلاَلِ السُّيُوفِ "
"ሰይፍ" መጋደልን እና ጦርነትን ያመለክታል፥ ጦርነትን መመኘት እንደሌለብን እና መታገስ እንዳለብን ከተነገረን በኃላ የመጨረሻው አማራጭ የኃይል አሰላለፍ ከሆነ ወደ ጦርነቱ ይገባል። በአሏህ መንገድ መጋደል ሥር መልካም ነገር የሆነው ፍትሕ፣ ሰላም፣ ጸጥታ ስላለ ተወጃጁ ነቢያችን"ﷺ"፦ "ጀናህ በሰይፍ ጥላ ሥር መሆኗን ዕወቁ!" አሉን። "ጀናህ በሰይፍ ጥላ ሥር ናት" የተባለው "ጀናህ እናት እግር ሥር ናት" በተባለበት ስሌት እና ቀመር ነው። አጽራረ ኢሥላም የሐዲሱን ሙሉ መልእክት ከመረዳት ይልቅ ከፊት እና ከኃላ ቀርጠው አረፍተ ነገሩን ከዐውዱ ለማፋታት ይዳዳሉ። አሏህ በእርሱ መንገድ ፍትሕ ለማስከበር ከሚታገሉት እና ከሚጋደሉት ባሮቹ ያድርገን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም