በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 16፥102 እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት እና ሙሥሊሞቹን ለመምራት እና ለማብሰር ቁርኣንን ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው" በላቸው፡፡
قُلْ نَزَّلَهُ رُوحُ الْقُدُسِ مِن رَّبِّكَ بِالْحَقِّ لِيُثَبِّتَ الَّذِينَ آمَنُوا وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُسْلِمِينَ

"ቅዱሳን" የሚለው ቃል "ቅዱስ" ለሚለው ቃል ብዜት ሲሆን መላእክት "ቅዱሳን" ተብለዋል፦

ዘዳግም 33፥2 ከአእላፋትም "ቅዱሳኑ" መጣ፤
በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።
וְאָתָ֖ה מֵרִבְבֹ֣ת קֹ֑דֶשׁ מִֽימִינֹ֕ו [אֵשְׁדָּת כ] (אֵ֥שׁ ק) (דָּ֖ת ק) לָֽמֹו׃

"በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው" የሚለው ይሰመርበት! ሕግ የተነገረው እና የተሰጠው በመላእክት ሥርዓት ነው፥ እነዚህ ጥቅስን፦ የሐዋርያት ሥራ 7፥53 ዕብራውያን 2፥2 ተመልከት!
መላእክት ብዙ ቦታ "ቅዱሳን" ተብለዋል፦

ኢዮብ 15፥15 እነሆ "በቅዱሳኑ" ስንኳ አይታመንም፤ ሰማያትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።
ዳንኤል 8፥13: ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ፦
ዳንኤል 4፥13 "አንድ ቅዱስ ጠባቂ" ከሰማይ ወረደ።
ዳንኤል 4፥17 ይህ ነገር "የጠባቂዎች ትእዛዝ"፥ ይህም ፍርድ "የቅዱሳን ቃል" ነው።

"መንፈስ" "ረቂቅ" "ምጡቅ" ማለት ሲሆን የመንፈስ ብዙ ቁጥር ደግሞ "መናፍስት" ነው፥ መላእክት "መናፍስት" ተብለዋል፦

ዕብራውያን 1፥14 ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ "የሚላኩ" እና የሚያገለግሉ "መናፍስት" አይደሉምን?

እዚህ አንቀጽ ላይ "መናፍስት" የተባሉት መላእክት እንደሆኑ እሙን እና ቅቡል ነው። "ቄስ" ተብሎ ብዜቱ "ቀሳውስት" እንደሆነ፣ "ቅዱስ" ተብሎ ብዜቱ "ቅዱሳን" እንደሆነ፣ "አምላክ" ተብሎ ብዜቱ "አማልክት" እንደሆነ ሁሉ "መንፈስ" ተብሎ ብዜቱ "መናፍስት" ነው። ነገር ግን "መንፈሶች" "ቄሶች" "ቅዱሶች" "አምላኮች" ጸያፍ ርቢ ናቸው፥ መላእክት "ቅዱሳን መናፍስት" ከሆኑ አንድ ነጠላ መልአክ "ቅዱስ መንፈስ" ሊባል ይችላል። ስለዚህ በቁርኣን ጂብሪል "ቅዱስ መንፈስ" መባሉ ስትሰሙ የሚያውረገርጋችሁ ማላመጫው እና ማዳመጫው ከተቀላቀለበት የሚመጣ ክፉኛ መረዳት ነው፦

ቁርኣን 16፥102 እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት እና ሙሥሊሞቹን ለመምራት እና ለማብሰር ቁርኣንን ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲኾን ከጌታህ አወረደው በላቸው፡፡
قُلْ نَزَّلَهُ رُوحُ الْقُدُسِ مِن رَّبِّكَ بِالْحَقِّ لِيُثَبِّتَ الَّذِينَ آمَنُوا وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُسْلِمِينَ

"ከጌታህ አወረደው" የሚለው ይሰመርበት! ጂብሪል ቁርኣንን ከአሏህ ማውረዱ ስሙር እና እሙር ነው፦

ቁርኣን 2፥97 "ለጂብሪል ጠላት የኾነ ሰው በቁጭት ይሙት በላቸው"፡፡ እርሱ ቁርኣኑን ከበፊቱ ለነበሩት አረጋጋጭ ለምእመናን መሪ እና ብስራት ሲኾን "በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና"፡፡
قُلْ مَن كَانَ عَدُوًّا لِّجِبْرِيلَ فَإِنَّهُ نَزَّلَهُ عَلَىٰ قَلْبِكَ بِإِذْنِ اللَّهِ مُصَدِّقًا لِّمَا بَيْنَ يَدَيْهِ وَهُدًى وَبُشْرَىٰ لِلْمُؤْمِنِينَ

አምላካችን አሏህ ለጂብሪል እልቅና በመስጠት ወደራሱ በማስጠጋት "መንፈሳችን" በማለት ይናገራል፦

ቁርኣን 19፥7 ከእነሱም መጋረጃን አደረገች፡፡ መንፈሳችንም (ጂብሪልን) ወደ እርሷ ላክን፡፡ ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት፡፡
فَاتَّخَذَتْ مِن دُونِهِمْ حِجَابًا فَأَرْسَلْنَا إِلَيْهَا رُوحَنَا فَتَمَثَّلَ لَهَا بَشَرًا سَوِيًّا

ይህ እኮ አያስገርምም። ባይብል ላይ ሰባቱ የመላእክት ሊቃውንት የእግዚአብሔር መናፍስት ተብለዋል፥ "ሊቅ" ማለት "አለቃ" ማለት ሲሆን "ሊቃውንት" ደግሞ "አለቆች" ማለት ነው፦

ዳንኤል 10፥13 ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።
וְהִנֵּ֣ה מִֽיכָאֵ֗ל אַחַ֛ד הַשָּׂרִ֥ים הָרִאשֹׁנִ֖ים בָּ֣א לְעָזְרֵ֑נִי
ራእይ 5፥6 እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ "የእግዚአብሔር መናፍስት" ናቸው።

መላእክት "የእግዚአብሔር መናፍስት" መባላቸው ስትሰሙ ፍግም እና ክልትው ከማለት ይልቅ ከአፉ እስከ ገደፉ ጢቅ አርጎ ማንበብ ይበጃል። እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ "የእግዚአብሔር መናፍስት" ሰባቱ የመላእክት አለቆች ሲሆኑ በትውፊት ሚካኤል፣ ገብርኤል፣ ሩፋኤል፣ ራጉኤል፣ ዑራኤል፣ ፋኑኤል፣ ሳቁኤል ናቸው፥ እነዚህ ሰባቱ መላእክት በዙፋኑ ፊት የሚቆሙ ሰባቱ መላእክት፣ ሰባት የእሳት መብራቶች፣ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት፣ የእግዚአብሔር ዓይኖች ተብለዋል፦

ራእይ 8፥2 በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን "ሰባቱን መላእክት" አየሁ፥
ራእይ 4፥5 በዙፋኑም ፊት "ሰባት የእሳት መብራቶች" ይበሩ ነበር፥ እነርሱም "ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት" ናቸው።
ዘካርያስ 4፥2 "ሰባትም መብራቶች" ነበሩበት፤
ዘካርያስ 4፥10 "እነዚህ ሰባቱ" ደስ ብሎአቸው በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ያያሉ፤ "እነዚህም" በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ "የእግዚአብሔር ዓይኖች" ናቸው።

ስለዚህ መላእክት "ቅዱሳን መናፍስት" እና "የእግዚአብሔር መናፍስት" ሲባሉ ጎብለል፣ ዘንጎል፣ ደንጎል እያላችሁ በእምነት ከተቀበላችሁ እንግዲያውስ ከመላእክት አንዱ ገብርኤል በነጠላ "ቅዱስ መንፈስ" እና "መንፈሳችን" ሲባል ክች እና ምንክች አትበሉ። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም