በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ

ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ከጥንት ነቢያት ሲጠቅስ ስለሚሳሳት የሚጽፈው በመንፈስ ቅዱስ በጭራሽ አይደለም፦

1ኛ ቆሮንቶስ 2፥9 ነገር ግን፦ "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጀው" ተብሎ እንድተጻፈ፥ እንዲህ እንናገራለን።

በብሉይ ኪዳን "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው" ተብሎ የተጻፈበትን ከ 39 የቀኖና መጻሕፍት በባትሪ ብትፈልጉ አታገኙም፥ ጥቅሱን የወሰደበት ቦታ አምላክ ስላዘጋጀው ነገር ሳይሆን አሐዳውያን ባዕድ አምላክን መስማት፣ መቀበል እና ማየት እንዳልፈለጉ የሚያስጨብጥ ነው፦

ኢሳይያስ 64፥4 ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም።

ጳውሎስ ሲኮርጅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ቢሆን ኖሮ በትክክል ማስቀመጥ ያቅተዋልን? ይህንን ስል አንዱ ወጠጤ አሳብን ከመሞገት ይልቅ እንደ ወጠጤ የሰው ስብዕና ላይ እንጠጥ እንጠጥ በማለት እንደ ውርጋጥ መራገጥ በለመደበት አፉ ጳውሎስ "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው" የሚለው ከየት እንዳገኘው ለመመለስ ቢሞክርም ምንም ምንጭ ሳያስቀምጥ ጭራሽ መልስ ላይሆነው ነገር ስለ ራዕየ ኤልያስ ሲዳክር እና ሲነፍር ታይቷል። ጳውሎስ "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው" ብሎ ዐውዱ ላይ የሚናገረው ስለ ክርስቶስ እንጂ ስለ ጀነት በፍጹም አይደለም፦

1ኛ ቆሮንቶስ 2፥7 ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን።

ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ እና ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ ያላወቁት ክርስቶስ ሲሆን ክርስቶስ የተዘጋጀ ሰው ነው፦

ሉቃስ 2፥30 ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት "ያዘጋጀኸውን" ማዳንህን አይተዋልና።
የሐዋርያት ሥራ 17፥31 ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን "ባዘጋጀው ሰው" እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው።

ይህ ሆኖ ሳለ በመቀጠል ነቢያችን"ﷺ" ከ 1ኛ ቆሮንቶስ 2፥9 ላይ እንዶኮረጁ ለማስመሰል ሲቃጣው ይህንን ሐዲስ ይጠቅሳል፦

ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 302
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “የላቀው አሏህም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለደጋግ ባሮቼ ዓይን ዓይቶት የማያውቅ፣ ጆሮ ሰምቶት የማያውቅ እና በሰው ልብ ውልብ ብሎ የማያውቅ ጸጋን አዘጋጅቻለው”። ከዚያም እርሳቸው፦ “ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ ዐታውቅም” የሚለውን አንቀጽ አነበቡ"። عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم ‏”‏ يَقُولُ اللَّهُ تَعَالَى أَعْدَدْتُ لِعِبَادِي الصَّالِحِينَ مَا لاَ عَيْنٌ رَأَتْ، وَلاَ أُذُنٌ سَمِعَتْ، وَلاَ خَطَرَ عَلَى قَلْبِ بَشَرٍ، ذُخْرًا، بَلْهَ مَا أُطْلِعْتُمْ عَلَيْهِ ‏”‌‏.‏ ثُمَّ قَرَأَ ‏{‏فَلاَ تَعْلَمُ نَفْسٌ مَا أُخْفِيَ لَهُمْ مِنْ قُرَّةِ أَعْيُنٍ جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ‏}‏

፨ ሲጀመር እዚህ ሐዲስ ላይ እንደ ጳውሎስ "ተብሎ እንድተጻፈ" የሚል የለም፣
፨ሲቀጥል ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ሐዲሱ ላይ ያሉን፦ "ጳውሎስ አለ" ብለው ሳይሆን "አሏህ አለ" ብለው ነው፥ አሏህን ደግሞ የግልጠት ባለቤት ስለሆነ ከማንም ወሰደ አይባልም።
፨ሢሰልስ ሐዲሱ ላይ አሏህ፦ "እኔ ለደጋግ ባሮቼ ዓይን ዓይቶት የማያውቅ፣ ጆሮ ሰምቶት የማያውቅ እና በሰው ልብ ውልብ ብሎ የማያውቅ ጸጋን አዘጋጅቻለው" ያለው ስለ ጀነት ነው፦

ቁርኣን 32፥17 ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን ጸጋ ማንኛይቱም ነፍስ ዐታውቅም፡፡
فَلَا تَعْلَمُ نَفْسٌ مَّا أُخْفِيَ لَهُم مِّن قُرَّةِ أَعْيُنٍ جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

ይኸው ቀጣፊ አሏህ እንደኮረጀ ለማስመሰል ሲዋትር አምላካችን አሏህ ጥንት በተውራት፦ "ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል" የሚል ሕግ ተናግሮ የነበረው ይጠቅሳል፦

ቁርኣን 5፥45 በእነርሱም ላይ በውስጧ፦ “ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል፤ ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው” ማለትን "ጻፍን"፡፡
وَكَتَبْنَا عَلَيْهِمْ فِيهَا أَنَّ النَّفْسَ بِالنَّفْسِ وَالْعَيْنَ بِالْعَيْنِ وَالْأَنفَ بِالْأَنفِ وَالْأُذُنَ بِالْأُذُنِ وَالسِّنَّ بِالسِّنِّ وَالْجُرُوحَ قِصَاصٌ

“ከተበ” كَتَبَ ደግሞ “ቃለ” قَالَ ማለትም “አለ” ወይም “ከለመ” كَلَّمَ ማለትም “ተናገረ” በሚል ስለሚመጣ "ከተብና" َكَتَبْنَا የሚለው ቃል "ቁልና" قُلْنَا ወይም "አውሐይና" َأَوْحَيْنَا በሚል የመጣ ነው። ያ ሆኖ ሳለ በ 9ኛው ክፍለ ዘመን ከቁርኣን 200 ዓመት በኃላ ከተዘጋጀው ከማሶሬት ቅጂ ተጠቅሶ "በትክክል አልተቀመጠም" ማለት እንጥል መቧጠጥ ነው፦

ዘጸአት 21፥24-25 ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥ እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።

ማሶሬት የቶራህ ቀዳማይ ሥረ መሠረት"orginal autography" አይደለም፥ ቅሉ ግን አሏህ ተናግሮት የነበረው አሳቡ በመለኮታዊ ቅሪት እንዳለ ጉልኅ ማሳያ ነው። ቁርኣን ላይ አሏህ የተናገረው "ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ ይያዛል" የሚለው ቃል በቃል ዘጸአት 21፥24-25 መቀመጥ ነበረበት ብሎ መሞገት በባዶ ሜዳ አቧራ ከማስነሳት የዘለለ ነገር የለውም።
በመጨረሻም የምለው ነገር ጳውሎስ "ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው" ተብሎ የተጻፈበት ጽሑፍ በብሉይ ኪዳን 39 መጻሕፍት ውስጥ በባትሪ ብትፈልጉት አታገኙትም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ኮረጀ ከተባለ ከ 46 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቀኖና መካከል ከሚገኘው ከመቃቢያን ሊሆን ከቻለ ነው፦

1ኛ መቃቢያን 14፥20 በወዲያኛው ዓለም ለደጋግ ሰዎች የተዘጋጀች ደስ የምታሰኝ ገነትን "ዓይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰው ልቡና ያልታሰበውን እግዚአብሔር በሕይወት ሳሉ ደስ ላሰኙት ለሚወዱት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ ያዘጋጀውን" ይሰጣቸው ዘንድ በሥራቸው ደስ እንዳሰኙት ለምእንደ አብርሃም፣ እንደ ይስሐቅ፣ እንደ ያዕቆብ አደሉም።

ጳውሎስ "ያዘጋጀውን" የሚለው ክርስቶስን ሲሆን የመቃብያን ተናጋሪ እና ጸሐፊ ደግሞ "ያዘጋጀውን" የሚለው ገነትን ነው። ስለዚህ ጳውሎስ "ተብሎ እንደተጻፈ" ብሎ የጻፈውን ከታሪክ መጽሐፍ ከመቃቢያን ከሆነ "ከአምላክ ነው" ብሎ ማለትም "ወዮላቸው" የሚያስብል ወንጀል ነው፦

ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ

አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
[9/22/2023, 4:17 PM] Wahid Omer Whatsapp: