በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 24፥31 ምእመናን ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ በንስሓ ተመለሱ።
وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ
"ንስሓ" የሚለው የግዕዝ ቃል "ነስሐ" ማለትም "ተመለሰ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መመለስ" ማለት ነው፥ በተመሳሳይ "ተውባህ" تَوْبَة የሚለው ቃል "ታበ" تَابَ ማለትም "ተመለሰ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መመለስ” ማለት ነው፦
ቁርኣን 4፥18 ጸጸትንም መቀበል ለእነዚያ ኀጢአቶችን ለሚሠሩ አንዳቸውንም ሞት በመጣበት ጊዜ «እኔ አሁን ተጸጸትኩ» ለሚል እና ለነዚያም እነርሱ ከሓዲዎች ኾነው ለሚሞቱ አይደለችም፡፡ እነዚያ ለእነርሱ አሳማሚን ቅጣት አዘጋጅተናል፡፡
وَلَيْسَتِ التَّوْبَةُ لِلَّذِينَ يَعْمَلُونَ السَّيِّئَاتِ حَتَّىٰ إِذَا حَضَرَ أَحَدَهُمُ الْمَوْتُ قَالَ إِنِّي تُبْتُ الْآنَ وَلَا الَّذِينَ يَمُوتُونَ وَهُمْ كُفَّارٌ ۚ أُولَـٰئِكَ أَعْتَدْنَا لَهُمْ عَذَابًا أَلِيمًا
"ጸጸት" ለሚለው የገባው ቃል "ተውባህ" تَوْبَة ሲሆን "ንስሓ" ማለት ነው፥ ንስሓ መቅቡል የሚሆነው በዱንያህ ላይ በሕይወት እያለን እንጂ የሞት አፋፍ ገርገራ ላይ ወይም ከሞት በኃላ መጸጸት መርዱድ ነው። ንስሓ ለማይገቡ አሳማሚ ቅጣት ተዘጋጅቷል፥ ከዚህ የእሳት ቅጣት ለመዳን ወደ አሏህ በንስሓ መመለስ ፈርድ ነው፦
ቁርኣን 24፥31 ምእመናን ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ በንስሓ ተመለሱ።
وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ተመለሱ" ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል "ቱቡ" تُوبُوا ሲሆን የስመ መደቡ "ተውባህ" تَوْبَة ነው፥ ከእሳት ለመዳን በንስሓ የአሏህን ይቅርታ እና ምሕረት መቀበል ያስፈልጋል፦
15፥49 ባሮቼን እኔ ይቅርባዩ መሓሪው እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡
نَبِّئْ عِبَادِي أَنِّي أَنَا الْغَفُورُ الرَّحِيمُ
2፥199 አላህን ይቅርታ ጠይቁ! አላህ እጅግ ይቅርባይ መሓሪ ነውና፡፡
وَاسْتَغْفِرُوا اللَّهَ ۚ إِنَّ اللَّهَ غَفُورٌ رَّحِيمٌ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 52, ሐዲስ 67
አቢ ሁረይራህ እንደተረከው፦ "ነቢዩም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ከእናንተ መካከል ሥራው ብቻ የሚያድነው ማንም የለም፥ ሶሓባዎችም፦ "የአሏህ መልእክተኛ ሆይ! እርሶም ቢሆኑ? አሉ። እርሳቸውም፦ "እኔም ብሆን፥ ነገር ግን አሏህ ከእርሱ በይቅርታው እና በምሕረቱ ሸፍኖኛል"።
عَنْ أَبِي، هُرَيْرَةَ قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم " لَيْسَ أَحَدٌ مِنْكُمْ يُنْجِيهِ عَمَلُهُ " . قَالُوا وَلاَ أَنْتَ يَا رَسُولَ اللَّهِ قَالَ " وَلاَ أَنَا إِلاَّ أَنْ يَتَغَمَّدَنِيَ اللَّهُ مِنْهُ بِمَغْفِرَةٍ وَرَحْمَةٍ "
ሳይቶብቱ መልካም ሥራ ከእሳት ቅጣት ለመዳን ዋስትና አይሆንም፥ በፍርድ ቀን ቅጣቱ ከመምጣቱ በፊት ንስሓ መግባት ይወጅብብናል፦
ቁርኣን 39፥54 ቅጣቱም ወደ እናንተ ከመምጣቱ እና ከዚያም የማትረዱ ከመኾናችሁ በፊት ወደ ጌታችሁ በመጸጸት ተመለሱ፡፡ ለእርሱም ታዘዙ፡፡
وَأَنِيبُوا إِلَىٰ رَبِّكُمْ وَأَسْلِمُوا لَهُ مِن قَبْلِ أَن يَأْتِيَكُمُ الْعَذَابُ ثُمَّ لَا تُنصَرُونَ
"ተመለሱ" ለሚለው የገባው ትእዛዛዊ ግሥ "አኒቡ" أَنِيبُوا ነው፥ የሥም መደቡ ደግሞ "ሙኒብ" مُّنِيب ሲሆን "ተመላሽ" ማለት ነው፦
ቁርኣን 11፥75 ኢብራሂም በእርግጥ ታጋሽ፣ አልቃሻ፣ "ተመላሽ" ነውና፡፡
إِنَّ إِبْرَاهِيمَ لَحَلِيمٌ أَوَّاهٌ مُّنِيبٌ
ቁርኣን 30፥31 ወደ እርሱ "ተመላሾች" ሆናችሁ የአላህን ሃይማኖት ያዙ፡፡ ፍሩትም፡፡ ሶላትንም አስተካክላችሁ ስገዱ፡፡ ከአጋሪዎቹም አትሁኑ፡፡
مُنِيبِينَ إِلَيْهِ وَاتَّقُوهُ وَأَقِيمُوا الصَّلَاةَ وَلَا تَكُونُوا مِنَ الْمُشْرِكِينَ
የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ "ሙኒብ" مُّنِيب በነጠላ በሁለተኛው አንቀጽ "ሙኒቢን" مُنِيبِين በብዜት መምጣቱን ልብ አድርግ! ጀነት ደግሞ አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራ እና በንስሓ "ተመላሽ" ልብ ሆኖ ለመጣ ትቀረባለች፦
ቁርኣን 50፥33 አልረሕማንን በሩቁ ኾኖ ለፈራ እና "በ-ንጹሕ ልብ" ለመጣ ትቀረባለች፡፡
مَّنْ خَشِيَ الرَّحْمَـٰنَ بِالْغَيْبِ وَجَاءَ بِقَلْبٍ مُّنِيبٍ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ንጹሕ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሙኒብ" مُّنِيب ሲሆን "ተመላሽ" ማለት ነው፥ ጀነት ወደ አሏህ በንጹሕ ልብ ለመጣ ትቀረባለች፦
ቁርኣን 37፥84 ወደ ጌታው "በ-ንጹሕ ልብ” በመጣ ጊዜ የኾነውን አስታውስ፡፡፡
إِذْ جَاءَ رَبَّهُ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ
ቁርኣን 26፥89 ወደ አላህ "በ-ንጹሕ ልብ" የመጣ ሰው ቢኾን እንጂ፡፡
إِلَّا مَنْ أَتَى اللَّهَ بِقَلْبٍ سَلِيمٍ
ሁለቱም አናቅጽ ላይ "ንጹሕ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ሠሊም" سَلِيم ነው፥ አንድ የአሏህ ባሪያ ወደ አሏህ በንስሓ ሲመለስ ልቡ ውስጥ "ሠላም" سَلَام ስላለ ልቡ ሠሊም ስትሆን እርሱ ደግሞ "ሣሊም" سَالِم ይሆናል። በእርግጥ "ንጹሕ" የኾነችን ጸጸት በመጸጸት ወደ አሏህ መመለስ የልብ ሰላም ይሰጣል፦
ቁርኣን 66፥8 እናንተ ያመናችሁ ሆይ! "ንጹሕ" የኾነችን ጸጸት በመጸጸት ወደ አላህ "ተመለሱ"፡፡
يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا تُوبُوا إِلَى اللَّهِ تَوْبَةً نَّصُوحًا
እዚህ አንቀጽ ላይ "ተመለሱ" ለሚለው የገባው ትእዛዛዊ ግሥ "ቱቡ" تُوبُوا እንደሆነ ልብ አድርግ! በእርግጥ አሏህ የባሪያውን ንስሓ እስከ ገርገራው ድረስ ይቀበላል፦
ጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 48, ሐዲስ 168
ኢብኑ ዑመር እንደተረከው፦ "ነቢዩ"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "በእርግጥ አሏህ የባሪያውን ንስሓ ገርገራው ከመድረስ በፊት ይቀበላል"።
عَنِ ابْنِ عُمَرَ، عَنِ النَّبِيِّ صلى الله عليه وسلم قَالَ " إِنَّ اللَّهَ يَقْبَلُ تَوْبَةَ الْعَبْدِ مَا لَمْ يُغَرْغِرْ " .
"ገርጊር" غِرْغِر የሚለው ቃል "ገርገረ" غَرْغَرَ ማለትም "ሞት ጉሮሮ ላይ ደረሰ" ማለት ሲሆን "ጣር" "ገርገራ" ማለት ነው። አምላካችን አሏህ በንጹሕ ልብ ንጹሕ ንስሓ የምንገባ ያድርገን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም