በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 3፥103 በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ፥ ከእርስዋም አዳናችሁ፡፡ እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል፡፡
وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

በቋንቋ ሊሒቃን ዘንድ "ድህነት" የሚለው ቃል በሃሌታው "ሀ" ሲጻፍ "ማጣት"poverty" የሚለውን ቃል የሚያሳይ ሲሆን "ድኅነት" ተብሎ በብዙኃኑ "ኀ" ሲጻፍ ደግሞ "መዳን"salvation" የሚለውን ቃል ያሳያል፥ በግሪክ ኮይኔ ደኅንነት "ሶቴሪያ" σωτηρία ይባላል። ነገረ ድኅነት"soteriology" በኢሥላም "ነጃህ" ወይም "ፈላሕ" ይባላል፥ "ነጃህ" نَّجَاة የሚለው ቃል "ነጀሐ" نَجَحَ ማለትም "ዳነ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መዳን" "ደኅነት" ማለት ነው፦

ቁርኣን 40፥41 ወገኖቼም ሆይ! ወደ "መዳን" የምጠራችሁ ስኾን ወደ እሳት የምትጠሩኝ ስትኾኑ ለእኔ ምን አለኝ?
وَيَا قَوْمِ مَا لِي أَدْعُوكُمْ إِلَى النَّجَاةِ وَتَدْعُونَنِي إِلَى النَّارِ

እዚህ አንቀጽ ላይ "መዳን" ለሚለው የገባው ቃል "ነጃህ" نَّجَاة እንደሆነ ልብ አድርግ! ሰው የሚድነው ከእሳት ሲሆን የአሏህን ጠሪ በመቀበል አምላካችን አሏህ ከእሳት ቅጣት ያድነናል፦

ቁርኣን 46፥31 ወገኖቻችን ሆይ! የአላህን ጠሪ ተቀበሉ፡፡ በእርሱም እመኑ፡፡ አላህ ከኀጢአቶቻችሁ ለእናንተ ይምራልና፡፡ ከአሳማሚ ቅጣትም ያድናችኋልና፡፡
يَا قَوْمَنَا أَجِيبُوا دَاعِيَ اللَّهِ وَآمِنُوا بِهِ يَغْفِرْ لَكُم مِّن ذُنُوبِكُمْ وَيُجِرْكُم مِّنْ عَذَابٍ أَلِيمٍ

"ፈላሕ" فَلَاح የሚለው ቃል "ፈለሐ" فَلَحَ ማለትም "ዳነ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "መዳን" "ደኅነት" ማለት ነው፦

ቁርኣን 24፥31 ምእመናን ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ በንስሓ ተመለሱ።
وَتُوبُوا إِلَى اللَّهِ جَمِيعًا أَيُّهَ الْمُؤْمِنُونَ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ትድኑ" ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል "ቱፍሊሑን" تُفْلِحُون ሲሆን የሥም መደቡ "ፈላሕ" فَلَاح ነው፥ ሰው ከእሳት ቅጣት የሚድነው ወደ አሏህን ንስሐ በመግባት ነው። "ተጸጸቱ" ለሚለው የገባው ቃል "ቱቡ" تُوبُوا ነው፥ "ተውባህ" تَوْبَة የሚለው ቃል "ታበ" تَابَ ማለትም "ተመለሰ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ከነበሩበት ስህተት በንስሐ ወደ አሏህ መመለስ” ማለት ነው። “ላ ኢላሀ ኢለል ሏህ” لَا إِلٰهَ إِلَّا اللّٰه የሚለው ገመድ ምእመናንን በጸጋ ወንድማማቾች የሚያደርግ የአሏህ ገመድ ነው፦

ቁርኣን 3፥103 የአላህን ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም፡፡ ጠበኞችም በነበራችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ የዋለውን የአላህን ጸጋ አስታውሱ! በልቦቻችሁም መካከል አስማማ፡፡ በጸጋውም ወንድማማቾች ኾናችሁ፡፡
وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِ اللَّهِ جَمِيعًا وَلَا تَفَرَّقُوا ۚ وَاذْكُرُوا نِعْمَتَ اللَّهِ عَلَيْكُمْ إِذْ كُنتُمْ أَعْدَاءً فَأَلَّفَ بَيْنَ قُلُوبِكُمْ فَأَصْبَحْتُم بِنِعْمَتِهِ إِخْوَانًا

ጥርት ያለው “ላ ኢላሀ ኢለል ሏህ” لَا إِلٰهَ إِلَّا اللّٰه የሚለው የአሏህ ገመድ ሰዎችን በልቦቻቸው የሚያስተሳስር ነው፥ ኩፍር እና ሺርክ በእሳቱ ጉድጓድ አፋፍ ላይ ለእሳት የሚዳርጉ ሲሆኑ የአሏህ ገመድ ግን ከዚህ ከእሳት ጉድጓድ አፋፍ ተንጠልጥለን የምንድንበት ገመድ ነው፦

ቁርኣን 3፥103 በእሳት ጉድጓድ አፋፍም ላይ ነበራችሁ፥ ከእርስዋም አዳናችሁ፡፡ እንደዚሁ ትመሩ ዘንድ አላህ ለእናንተ አንቀጾቹን ያብራራል፡፡
وَكُنتُمْ عَلَىٰ شَفَا حُفْرَةٍ مِّنَ النَّارِ فَأَنقَذَكُم مِّنْهَا ۗ كَذَٰلِكَ يُبَيِّنُ اللَّهُ لَكُمْ آيَاتِهِ لَعَلَّكُمْ تَهْتَدُونَ

አንድ ሙሥሊም ይህንን ገመድ ከያዘ ከእሳት ጉድጓድ አፋፍ ተንጠልጥሎ ድኗል፥ በእርግጥ ምእመናን በዚህ ገመድ ዳኑ፦

ቁርኣን 23፥1 ምእምናን በእርግጥም "ዳኑ"።
قَدْ أَفْلَحَ الْمُؤْمِنُونَ

እዚህ አንቀጽ ላይ "ዳኑ" ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል "አፍለሐ" أَفْلَحَ ሲሆን ሥርወ-ቃሉ "ፈለሐ" فَلَحَ ነው፥ ንቁ! የአላህ ሕዝቦች እነርሱ “የሚድኑት” ናቸው፦

ቁርኣን 58፥22 ንቁ! የአላህ ሕዝቦች እነርሱ “የሚድኑት” ናቸው፡፡
أَلَا إِنَّ حِزْبَ اللَّهِ هُمُ الْمُفْلِحُونَ
ቁርኣን 7፥8 ትክክለኛውም ሚዛን የዚያን ቀን ነው፡፡ ሚዛኖቻቸው የከበዱላቸው ሰዎችም እነዚያ እነርሱ “የሚድኑት” ናቸው፡፡
وَالْوَزْنُ يَوْمَئِذٍ الْحَقُّ ۚ فَمَن ثَقُلَتْ مَوَازِينُهُ فَأُولَـٰئِكَ هُمُ الْمُفْلِحُونَ

"የሚድኑት" ለሚለው የገባው ቃል "ሙፍሊሑን" مُفْلِحُون ሲሆን ሙፍሊሑን መልካም ሥራዎቻቸው የሚመዘንላቸው በጀነት ውስጥ ያለውን የተለያየ ደረጃ ሊመነዱ ነው፥ በተቃራኒው ኩፋሮች የሚሠሩት መልካም ሥራ ያለ ኢማን ስለሆነ ሥራዎቻቸው የሚመዘንበት ሚዛን አይቆምላቸውም፥ እነርሱም ከእሳት አይድኑም፦

ቁርኣን 18፥105 እነዚያ እነርሱ በጌታቸው ማስረጃዎችና በመገናኘቱ የካዱት ናቸው፡፡ ሥራዎቻቸውም ተበላሹ፡፡ ለእነርሱ በትንሣኤ ቀን ሚዛንን አናቆምላቸውም፡፡
أُولَـٰئِكَ الَّذِينَ كَفَرُوا بِآيَاتِ رَبِّهِمْ وَلِقَائِهِ فَحَبِطَتْ أَعْمَالُهُمْ فَلَا نُقِيمُ لَهُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ وَزْنًا
ቁርኣን 6፥135 እነሆ በደለኞች አይድኑም፡፡
إِنَّهُ لَا يُفْلِحُ الظَّالِمُونَ

በኢሥላም ሥነ-መለኮት ለመዳን የሰውዬው ነጻ ፈቃድና ምርጫ፣ እምነት፣ ንስሐ፣ መልካም ሥራ፣ ጽናት እና እንዲሁ የአሏህ ይቅርታ፣ ምሕረት፣ ሉዓላዊነት ስለሚያስፈልግ ደኅንነቱ የመተባበር ድኅነት"synergistic salvation" ነው፥ አንድ ሙሥሊም የአሏህን ገመድ እስከመጨረሻው በጽናት መያዝ ሲኖርበት ከለቀቀው ድኅነቱን ሊያጣ ስለሚችል ድኅነቱ ሁኔታዊ ደኅንነት"conditional salvation" ነው። “ኢሥቲቃማህ” اِسْتِقَامَة የሚለው ቃል “ኢሥቲቃመ اِسْتَقَامَ ማለትም “ቆመ” ወይም “ጸና” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ጽናት"perseverance" ማለት ነው፦

ቁርኣን 41፥30 እነዚያ «ጌታችን አላህ ነው» ያሉ ከዚያም "ቀጥ ያሉ" «አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ» በማለት በእነርሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ፡፡
إِنَّ الَّذِينَ قَالُوا رَبُّنَا اللَّهُ ثُمَّ اسْتَقَامُوا تَتَنَزَّلُ عَلَيْهِمُ الْمَلَائِكَةُ أَلَّا تَخَافُوا وَلَا تَحْزَنُوا وَأَبْشِرُوا بِالْجَنَّةِ الَّتِي كُنتُمْ تُوعَدُون

እነዚህ አናቅጽ ላይ “ቀጥ ያሉ” ለሚለው ቃል የገባው “ኢሥተቃሙ” اسْتَقَامُوا ሲሆን "የጸኑ" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ ጀነትን በተስፋ ዋስትና የሰጠው በዲኑል ኢሥላም ለሚጸኑ አማንያን ነው። አምላካችን አላህ ስለ ፈላሕ ተረድተው ሙፍሊሑን ከሚላቸው ባሮቹ ያድርገን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም