በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
20፥115 ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡
وَلَقَدْ عَهِدْنَآ إِلَىٰٓ ءَادَمَ مِن قَبْلُ
“ነቢይ” نَبِيّ የሚለው ቃል “ነበአ” نَبَّأَ ማለትም “አወራ” ወይም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ ቃል ሲሆን “አውሪ” ወይም “ተናጋሪ” ማለት ነው፥ “ነበእ” نَبَأ ማለት “የሩቅ ወሬ” ወይም “የሩቅ ንግግር” ሲሆን አንድ ሰው ከአሏህ ነበእ ሲወርድለት ነቢይ ይሰኛል። አምላካችን አሏህ ወደ አደም ኪዳንን አውርዷል፦
20፥115 ወደ አደምም ከዚህ በፊት ኪዳንን በእርግጥ አወረድን፡፡
وَلَقَدْ عَهِدْنَآ إِلَىٰٓ ءَادَمَ مِن قَبْلُ
"ከዚህ በፊት" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! "ከዚህ በፊት" ለሚለው የገባው ቃል "ሚን ቀብሉ” مِنْ قَبْلُ ሲሆን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ ነው፥ "ከዚህ በፊት" አሏህ በአደም ጊዜ "ሙሥሊሞች" ብሎ ሰየመ፦
22፥78 "እርሱ "ከዚህ በፊት" ሙሥሊሞች ብሎ ሰይሟችኋል፡፡
هُوَ سَمَّاكُمُ الْمُسْلِمِينَ مِن قَبْلُ
"ከዚህ በፊት" ለሚለው የገባው ቃል "ሚን ቀብሉ” مِنْ قَبْلُ ሲሆን የአደምን ጊዜ ያስታውሰናል። "እርሱ" የተባለው "አሏህ" የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ተውላጠ ስም ነው፥ አሏህ "ሙሥሊሞች" ብሎ የጠራን ሲሆን "ሙሥሊም" مُسْلِم ማለት አንዱን አምላክ "ተገዥ" "አምላኪ" "ታዛዥ" ማለት ነው። አደም በምድር ላይ የመጀመሪያው ነቢይ ነው፦
ኢማም አሕመድ መጽሐፍ 5, ሐዲስ 1781
አቡ ዘር እንደተረከው፦ "የአሏህ ነቢይ ሆይ! የመጀመሪያው ነቢይ ማን ነው? ብሎ አለ። እርሳቸውም፦ "አደም ነው" አሉ። እርሱም፦ "የአሏህ ነቢይ ሆይ!እርሱ ነቢይ ነበርን? ብሎ አለ። እርሳቸውም፦ "አዎ" አሉ"።
عَن أَبُو ذَرٍّ قُلْتُ : يَا نَبِيَّ اللَّهِ، فَأَيُّ الْأَنْبِيَاءِ كَانَ أَوَّلَ. قَالَ : " آدَمُ ". قَالَ : قُلْتُ : يَا نَبِيَّ اللَّهِ، أَوَنَبِيٌّ كَانَ آدَمُ ؟ قَالَ : " نَعَمْ،
“ረሡል” رَسُول የሚለው ቃል “አርሠለ” أَرْسَلَ ማለትም “ላከ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “መልእክተኛ” ማለት ነው፥ “ሪሣላህ” رِسَالَة ማለት “መልእክት” ማለት ሲሆን አንድ ነቢይ ሪሣላህ ሲወርድለት “ረሡል” ይሰኛል፦
22፥52 ከመልእክተኛ እና ከነቢይ ከአንተ በፊት አንድንም አልላክንም፥ ባነበበና ዝም ባለ ጊዜ ሰይጣን በንባቡ ላይ ማጥመሚያን ቃል የሚጥል ቢሆን እንጂ።
وَمَا أَرْسَلْنَا مِنْ قَبْلِكَ مِنْ رَسُولٍ وَلَا نَبِيٍّ إِلَّا إِذَا تَمَنَّىٰ أَلْقَى الشَّيْطَانُ فِي أُمْنِيَّتِهِ
እዚህ አንቀጽ ላይ “ነቢይ” نَبِيّ እና “ረሡል” رَسُول በሚሉት የማዕረግ ስሞች መካከል “ወ” وَ ማለትም “እና” የሚል መስተጻምር አለ፥ ይህም ነቢይ እና ረሡል ሁለት የተለያየ ደረጃ መሆኑን ቁልጭ እና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ይህንን ከተረዳን ዘንዳ ኑሕ ደግሞ የመጀመሪያው ረሡል ነው፦
ኢማም ቡኻሪይ መጽሐፍ 65, ሐዲስ 4476
አነሥ እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” አሉ፦ *”……(አደምም)፦ “ኑህ ጋር ሂዱ! እርሱ በምድር ላይ የተላከ የመጀመሪያው መልእክተኛ ነው፥ ወደ ምድር ባለቤቶች አሏህ ልኮታል” ይላቸዋል”።
ائْتُوا نُوحًا فَإِنَّهُ أَوَّلُ رَسُولٍ بَعَثَهُ اللَّهُ إِلَى أَهْلِ الأَرْضِ.
"ነባይ" የሚለው የግዕዝ ቃል “ነበየ” ማለትም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “ነባቢ” “ተናጋሪ” "ነቢይ" ማለት ነው፥ "ነቢብ" ማለት "ንግግር" ማለት ሲሆን አንድ ሰው ከፈጣሪ ነቢብ ሲመጣለት ነቢይ ይሆናል። አዳም ነቢብ መቶለት ነበር፦
ቀሌምንጦስ 1፥37 አዳም ጥበብን፣ ነቢብን እና ዕውቀትን ሁሉ እንዲቀበል ነው።
ቀሌምንጦስ 1፥40 በዚህ ጊዜ ንጉሥነትን እና ነቢይነትን ሠጠው በክብር መንበር ላይም አስቀመጠው።
አዳም "ነቢይነት" ሲቀበል ነቢይ ሆኗል፥ ፈጣሪ "አዳም ሆይ! እነሆ ንጉሥ፣ ካህን እና "ነቢይ" መስፍን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ስላንተ በፈጠርሁት ሁሉ እንድትሆን አደረግሁ" ሲል መላእክት ሰምተዋል፦
ቀሌምንጦስ 1፥43 በዚህ ጊዜ መላእክት የእግዚአብሔር ቃል፦ "አዳም ሆይ! እነሆ ንጉሥ፣ ካህን እና "ነቢይ" መስፍን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ስላንተ በፈጠርሁት ሁሉ እንድትሆን አደረግሁ...ሲል ሰሙ።
ከ 451 እስከ 521 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረ ያዕቆብ ዘሥሩግ "Jacob of Serugh" በእንተ ወላዲተ አምላክ በሚል መጽሐፉ ላይ አዳም ነቢይ እንደነበረ ተናግሯል፦
"አዳም ድንግል ሔዋንን አስገኝቷል፥ "የሕይወት እናት" ብሎ ጠርቷታል። እርሱ ነቢይ ነበረ"።
On the Mother of God (Jacob of Serugh) Homily (I)1 Number 634
በአበው ትምህርት "አዳም ነቢይ አልነበረም" የሚል አሉታዊ ዕይታ አልበረም፥ "አዳም ነቢይ ከነበረ ለእነማን ነበረ" ብላችሁ የምትጠይቁን ጥያቄውን ገልብጣችሁ እራሳችሁን ጠይቁ! አዳም የፈለገውን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ተሰቶት ነበር፦
ቀሌምንጦስ 1፥44 "የፈለግኸውን ታደርግ ዘንድ ይህንን ሥልጣን ሠጠሁህ" ሲል ሰሙ።
ሥልጣን ስለተሰጠው አዳም ከነቢይነትም አልፎ "አምላክ" ተብሎ እንደሚጠራ ቴዎፍሎስ ዘአንጾኪያ"Theophilus of Antioch" ተናግሯል፦
"ሁሉን ቻይ አምላክም አዳምን ከተፈጠረባት ምድር ወደ ገነት አዛወረው፥ እንደገናም እንዲበስል፣ ፍጹም እንዲሆን፣ "አምላክ" ተብሎ እንዲጠራ እና የኢ-መዋቲነትን ርስት ይዞ ወደ ሰማይ እንዲወጣ የእድገት ዘዴዎችን ተሰጠው"።To Autolycus (Theophilus of Antioch) Book II(2) Chapter 24
በእርግጥ አንድ ሰው ፈጣሪ ካናገረው እና ንግግር ከእርሱ ከተቀበለ ነቢይ ስለሚሆን የግድ መላክ እና "ለእነማ ተላከ" የሚል አጠይቆት ላያስፈልገው ይችላል፥ "አጠይቆቱ አግባብ እና አገባብ አለው" ከተባለ እንግዲያውስ አዳም ቤተሰብ እስካለው ድረስ ለቤተሰቡ ነቢይ መሆን ይችላል።
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም