በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 33፥45 አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ፣ አብሳሪ እና አስጠንቃቂም አድርገን ላክንህ፡፡
يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ إِنَّا أَرْسَلْنَاكَ شَاهِدًا وَمُبَشِّرًا وَنَذِيرًا
"ነቢይ" نَبِيّ የሚለው ቃል "ነበአ" نَبَّأَ ማለትም "የሩቅ ወሬን አወራ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "የሩቅ ወሬ አውሪ" "ባለ ራእይ" "ነባይ" "ነባቢ" ማለት ነው፥ የሚወርድለት "የሩቅ ወሬ" ደግሞ "ነበእ" نَبَأ ይባላል። ይህንን የሩቅ ወሬ ለአንድ ነቢይ ከሦስት መንገድ በአንዱ ይወርድለታል፦
ቁርኣን 42፥51 ለሰው አላህ “በራእይ”፣ ወይም “ከግርዶ ወዲያ”፣ ወይም “መልክተኛን መልአክን” የሚልክ እና በፈቃዱ የሚሻውን “የሚያወርድለት” ቢሆን እንጅ በገሃድ “ሊያናግረው” ተገቢው አይደለም"፥ እርሱ የበላይ ጥበበኛ ነውና።
وَمَا كَانَ لِبَشَرٍ أَن يُكَلِّمَهُ ٱللَّهُ إِلَّا وَحْيًا أَوْ مِن وَرَآئِ حِجَابٍ أَوْ يُرْسِلَ رَسُولًۭا فَيُوحِىَ بِإِذْنِهِۦ مَا يَشَآءُ ۚ إِنَّهُۥ عَلِىٌّ حَكِيمٌۭ
እዚህ አንቀጽ ላይ እንደተጠቀሰው አምላካችን አሏህ አንድን ነቢይ የሚያናግረው አንደኛው መንገድ በራእይ የሚያናግረው ነው፥ "ራዕይ" ያ ነቢይ በሰመመን ወይም በተመስጦ ውስጥ ሆኖ አሏህ የሚያናግርበት መንገድ ነው። ሁለተኛው መንገድ አሏህ በቀጥታ የሚያናግረው ነው፥ ይህም ያለ ራዕይ ወይም ያለ መልአክ ሳይታይ ከግርዶ ወዲያ ሆኖ የሚያናግርበት መንገድ ነው።
ሦስተኛው መንገድ አላህ በመልአክ የሚያናግረው ነው። ይህንን ከተረዳን ዘንዳ አሏህ ይህንን የሩቅ ወሬ ለአንድ ሰው ሲያሳውቀው ያ ሰው ነቢይ ይባላል፥ አምላካችን አሏህ ነቢያችንን"ﷺ" በሦስተኛ መንገድ በመልአኩ ጂብሪል አናግሯቸዋል። አሏህ ወደ እርሳቸው ያወረደላቸው ቁርኣን ደግሞ "ነበእ" ነው፦
ቁርኣን 38፥67 በላቸው «እርሱ ቁርኣን ታላቅ ነበእ ነው፡፡
قُلْ هُوَ نَبَأٌ عَظِيمٌ
አምላካችን አሏህ በሦስተኛው መንገድ ለነቢያችንን"ﷺ"፦ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" ብሏል፦
ቁርኣን 29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ "እኔንም ብቻ አምልኩኝ"፡፡
يَٰعِبَادِىَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ إِنَّ أَرْضِى وَٰسِعَةٌۭ فَإِيَّٰىَ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 21፥92 ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፤ "እኔም ጌታችሁ ነኝና አምልኩኝ"፡፡
إِنَّ هَٰذِهِۦٓ أُمَّتُكُمْ أُمَّةًۭ وَٰحِدَةًۭ وَأَنَا۠ رَبُّكُمْ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 21፥25 ከአንተ በፊትም እነሆ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" በማለት ወደ እርሱ የምናወርድለት ቢኾን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም፡፡
وَمَآ أَرْسَلْنَا مِن قَبْلِكَ مِن رَّسُولٍ إِلَّا نُوحِىٓ إِلَيْهِ أَنَّهُۥ لَآ إِلَٰهَ إِلَّآ أَنَا۠ فَٱعْبُدُونِ
አምላካችን አሏህ ነቢያችንን"ﷺ" በሁለተኛ መደብ፦ "አንተ ነቢዩ ሆይ" በማለት እራሱ እንደላከ ለማመልከት "ላክንህ" በማለት "ለሰዎች ሁሉ" እንደተላኩ ይናገራል፦
ቁርኣን 33፥45 አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ፣ አብሳሪ እና አስጠንቃቂም አድርገን ላክንህ፡፡ يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ إِنَّا أَرْسَلْنَاكَ شَاهِدًا وَمُبَشِّرًا وَنَذِيرًا
ወደ ባይብል ስንመጣ ፈጣሪ በተለያየ መንገድ ለአንድ ነቢይ ይናገራል፥ በሕልም፣ በሌሊት ራእይ ወዘተ ማለት ነው፦
ኢዮብ 33፥14-15 አምላክ በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም። በሕልም፣ በሌሊት ራእይ፣ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ።
ፈጣሪ በራእይ የሚያናግረው ሰው ባለ ራእይ ይባል ነበር፥ ሰው አምላክን ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ሲሄድ፦ "ኑ! ወደ ባለ ራእይ እንሂድ" ይል ነበር፦
1 ሳሙኤል 8፥9 ዛሬ ነቢይ የሚባለው ቀድሞ ባለ ራእይ ይባል ነበርና አስቀድሞ በእስራኤል ዘንድ ሰው አምላክን ለመጠየቅ ሲሄድ፦ "ኑ! ወደ ባለ ራእይ እንሂድ" ይል ነበር።
አምላክ ነቢያትን ማለትም አብርሃምን፣ ያዕቆብን፣ ኢሳይያስን፣ ዳንኤልን፣ ሙሴን በራእይ አራግሯል፦
ዘፍጥረት 15፥1 ከዚህ ነገር በኋላም የያህዌህ ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ።
ዘፍጥረት 46፥2 አምላክም በሌሊት ራእይ፦ "ያዕቆብ ያዕቆብ" ብሎ ለእስራኤል ተናገረው።
ኢሳይያስ 1፥1 የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ።
ዳንኤል 2፥19 የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት።
ዘጸአት 3፥3 ሙሴም፦ ልሂድና ቍጥቋጦው ስለ ምን አልተቃጠለም ይህን ታላቅ "ራእይ" ልይ አለ።
ሙሴ "ታላቅ ራእይ ልይ" ያለው መልአክ ተልኮ በመልአኩ ፈጣሪ፦ "እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ" በማለት የተነገረውን ነው፦
ዘጸአት 3፥2 የያህዌህም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው።
ዘጸአት 3፥6 ደግሞም፦ እኔ የአባትህ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ" አለው።
የሐዋርያት ሥራ 7፥35 ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ አምላክ ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
ስለዚህ "ፈጣሪ ከራእይ ወይም ከመልአክ ውጪ በቀጥታ ያለ ራእይ እና ያለ መልአክ አንድን ነቢይ ካላናገረ" ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ፣ አሸሼ ገዳዬ፣ እንቧ ከረዮ፣ እሪ ከረዮ ማለት አያዋጣም፥ ፈጣሪ አብዛኛው ነቢያት በራእይ ዕውቀት ይገልጥላቸዋል ወይም በሕልም ያናግራቸዋል እንጂ ቀጥታ አያናግራቸውም፦
ዘኍልቍ 12፥6 እርሱም፦ ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ ያህዌህ በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።
ሙሴን ቢሆን በነቢይነቱ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን መሃል ላይ ቀጥታ ያለ ራእይ እና ያለ መልአክ ቢያናግረውም ግልጠተ መለኮት የመጣለት ግን በመልአክ ነው፦
ዘኍልቍ 12፥7-8 ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ።
ስለዚህ ቁርኣን የአሏህ ንግግር ነው፥ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" እያለ የሚናገረው አሏህ ነው፥ የአምልኮ ሐቅ የሚገባውም ብቻውን የፈጠረ ብቻ እንደሆነ እራሱ አሏህ በመጀመሪያ መደብ "ጂንን እና ሰውን ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም" በማለት ተናግሯል፦
ቁርኣን 51፥56 ጂንን እና ሰውን ሊያመልኩኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም