በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
ቁርኣን 42፥11 የሚመስለው ምንም "ነገር" የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡
لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
አምላካችን አሏህ ከፍጡራኑ ጋር የማይመሳሰል የራሱ ባሕርያት አሉት፥ እርሱን የሚመስል ምንም ነገር የለም፦
ቁርኣን 42፥11 የሚመስለው ምንም "ነገር" የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡
لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ሚስል" مِثْل በሚለው ቃል ላይ መነሻ ቅጥያ ሆኖ የገባው "ከ" كَ የሚል መስተዋድድ "በጭራሽ" ማለት ነው፥ "ነገር" በሚለው ቃል ውስጥ ሁሉም ፍጡራን የሚካተቱ ሲሆኑ ከፍጡራን መካከል እርሱን የሚመስል ብጤ እና ምክሼ በጭራሽ የለም፦
ቁርኣን 112፥4 «ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም፡፡» وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ
ቁርኣን 19፥65 እርሱ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነው እና አምልከው! እርሱን በአምልኮ ላይ ታገስ! ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን?።
رَّبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ ۚ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا
እዚህ አንቀጽ ላይ "ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን" ሲል አሏህን የሚተካከው ብጤ እና ሞክሼ እንደሌለው በቂ ማሳያ ነው።
ይህንን ከተረዳን ዘንዳ ኢየሱስ በአምላክ ኃይል በሕይወት ይኖራል፦
2 ቆሮንቶስ 13፥4 ነገር ግን "በ"-አምላክ ኃይል በሕይወት ይኖራል።
ἀλλὰ ζῇ ἐκ δυνάμεως Θεοῦ.
"በ" የሚለው መስተዋድድ መነሻ ላይ ያለው "የአምላክ ኃይል" እና ክርስቶስ ሁለት ለየቅል የሆኑ ነገሮች ናቸው፥ በተመሳሳይ "ኃይል" የሚለው "መልክ" በሚል ተዋዋጭ ቃል መጥቷል፦
ፊልጵስዩስ 2፥6 እርሱ "በ-"አምላክ መልክ" ሲኖር ሳለ ከአምላክ ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም።
ὃς ἐν μορφῇ Θεοῦ ὑπάρχων οὐχ ἁρπαγμὸν ἡγήσατο τὸ εἶναι ἴσα Θεῷ,
"በ" የሚለው መስተዋድድ መነሻ ላይ ያለው "የአምላክ መልክ" እና ክርስቶስ ሁለት ለየቅል የሆኑ ነገሮች ናቸው፥ "ሲኖር"being" ለሚለው የገባው የግሥ መደብ "ሃይፓርኮን" ὑπάρχων ሲሆን ቀጣይነት ያለው የአሁኑ ግሥ ስለሚያመለክት ከመወለዱ በፊት ያለውን ቅድመ ህልውና በጭራሽ አያሳያም፥ ለዚያን ነው በእንግሊዝኛ በአላፊ ግሥ "Who, was in the form of God" ሳይሆን Who, being in the form of God" ብለው ቀጣይነት ባለው አሁኗዊ ግሥ"present participle" ያስቀመጡት። አየሱስ እራሱ ከአምላክ ጋር በስምምነት ያስተካከለው በአገልግሎት ዘመኑ እንደሆነ ቅቡል ነው፦
ዮሐንስ 5፥18 ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከአምላክ ጋር አስተካክሎ፦ "አምላክ አባቴ ነው" ስላለ፥
ἀλλὰ καὶ Πατέρα ἴδιον ἔλεγεν τὸν Θεόν, ἴσον ἑαυτὸν ποιῶν τῷ Θεῷ.
"ሳለ" የሚለው ጊዜን ለማመልከት የመጣ ሲሆን በአምላክ ኃይል በሚኖርበት ጊዜ ራሱን ከአምላክ ጋር አስተካክሎ፦ "አምላክ አባቴ ነው" ብሎ ተናገረ። "መተካከል" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ኢሱስ" ἴσος ሲሆን "መስማማት"agreement" ማለት ነው፦
ማርቆስ 14፥56 ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን "አልተሰማማም"።
πολλοὶ γὰρ ἐψευδομαρτύρουν κατ’ αὐτοῦ, καὶ ἴσαι αἱ μαρτυρίαι οὐκ ἦσαν.
እዚህ አንቀጽ ላይ ያለ አፍራሽ ስናስቀምጥ "መስማማት" ለሚለው የግሥ መደብ የተጠቀመበት በተመሳሳይ "ኢሱስ" ἴσος ነው፥ አምላክ አንድ ከሆነ እና ኢየሱስ ከአንድ አምላክ ጋር መስማማትን እንደ መቀማት አልቆጠረም። "ኢሱስ" ἴσος ገላጭ ቅጽል በተውሳከ ግሥ "ኡስ" ως ሲሆን "ልክ እንደ"as" ማለት ነው፦
ዘካሪያስ 12፥8 የዳዊትም ቤት በፊታቸው "እንደ" አምላክ እንደ ጌታ መልአክ ይሆናል።
ὁ δὲ οἶκος Δαυὶδ ὡς οἶκος Θεοῦ, ὡς ἄγγελος Κυρίου ἐνώπιον αὐτῶν.
የዳዊት ቤት(ቤተሰብ) እንደ አምላክ እና እንደ የጌታ መልአክ ይሆናል ሲባል በባሕርይ ይስተካከላል ማለት ነውን? አምላክ፣ መልአክ እና የዳዊት ቤተሰብ በምንነት እንደሚለያዩ ሁሉ ክርስቶስ እና አምላክ በምንነት ይለያያሉ። ኢየሱስን የላከው አብ ከማንም ጋር በባሕርይ አይስተካከልም፦
ኢሳይያስ 46፥5 በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? τίνι με ὡμοιώσατε; ἴδετε, τεχνάσασθε, οἱ πλανώμενοι.
ይህ አንድ ነጠላ ማንነት "ከምን ጋር" ሳይሆን "ከማን ጋር" ማለቱ አብን በምንነት የሚስተካከል ማንነት እንደሌለ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። "ሜጋስ" μέγας ማለት "ታላቅ" ማለት ሲሆን ገላጭ ቅጽል"Adjective" ነው፥ የሜጋስ አንጻራዊ ገላጭ ቅጽል "ሜይዞን" μεῖζόν ሲሆን ይህም አንጻራዊ ገላጭ ቅጽል የባሕርይ መበላለጥን ለማመልከት አገልግሎት ላይ ውሏል፦
ማቴዎስ 12፥6 ነገር ግን እላችኋለሁ ከመቅደስ "የሚበልጥ" ከዚህ አለ።
λέγω δὲ ὑμῖν ὅτι τοῦ ἱεροῦ μεῖζόν ἐστιν ὧδε.
እዚህ አንቀጽ ላይ "የሚበልጥ" ለሚለው የገባው ቃል "ሜይዞን" μεῖζόν ሲሆን በላጩ ኢየሱስ ሰው ሲሆን ተበላጩ መቅደስ ደግሞ ድንጋይ በድንጋይ ላይ የተነባበረ ግዑዝ ነገር ነው፥ ይህ የባሕርይ መበላለጥን ያሳያል። ሰው፣ እንስሳ፣ እጽዋት፣ ማዕድናት በባሕርይ የተለያዩ ናቸው፥ የሰው ኑባሬ"being" ሰው ብቻ ነው። እዚህ ድረስ ከተግባባን ከሁሉ በላይ ሁሉን የፈጠረ አንድ አምላክ አብ ከሁሉ ይበልጣል፦
ዮሐንስ 10፥29 የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል። ὁ Πατήρ μου ὃ δέδωκέν μοι πάντων μεῖζόν ἐστιν
እዚህ አንቀጽ ላይ "ይበልጣል" ለሚለው የገባው ቃል "ሜይዞን" μεῖζόν ሲሆን በላጩ አብ ሲሆን ተበላጩ ደግሞ ሁሉም ነው፥ ኢየሱስ አብ ስላልሆነ "ሁሉ" በሚል ቃላት ውስጥ ኢየሱስ ስለሚካተት አብ ኢየሱስን በባሕርይ ይበልጠዋል። ኢየሱስ፦ "ከ"እኔ" አብ ይበልጣል" ብሏል፦
ዮሐንስ 14፥28 "ከ"እኔ" አብ ይበልጣልና።
ὁ Πατὴρ μείζων μού ἐστιν.
እዚህ አንቀጽ ላይ "ይበልጣል" ለሚለው የገባው ቃል "ሜይዞን" μείζων ሲሆን በላጩ አብ ሲሆን ተበላጩ ደግሞ ኢየሱስ ነው፥ "ከ" የሚለው መስተዋድድ መነሻ ቅጥያ የሆነለት "እኔ" የሚለው ተሳቢ ተውላጠ ስም የኢየሱስ ሙሉ "እኔነትን" ቁልጭ አርጎ ያሳያል፦
ዕብራውያን 2፥7 ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው።
ἠλάττωσας αὐτὸν βραχύ τι παρ’ ἀγγέλους,
"ኤላሶን" ἐλάσσων ማለት "ማነስ" ማለት ሲሆን "ሜይዞን" μείζων ለሚለው ተቃራኒ ነው፥ ኢየሱስ ከመላእክት ያነሰው በባሕርይ ከሆነ ይልቁኑ ከአብ በባሕርይ ምንኛ ያንስ ይሆን?
"ኬኖሲስ" κένωσις የሚለው የግሪክ ኮይኔ ቃል "ኬኖ" κενόω ማለትም "ባዶ አደረገ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ከንቱነት" "ባዶነት"emptiness" ማለት ነው፦
ፊልጵስዩስ 2፥7 ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን "ባዶ አደረገ"። ἀλλὰ ἑαυτὸν ἐκένωσεν μορφὴν δούλου λαβών, ἐν ὁμοιώματι ἀνθρώπων γενόμενος· καὶ σχήματι εὑρεθεὶς ὡς ἄνθρωπος
እዚህ አንቀጽ ላይ "ባዶ አደረገ" ለሚለው የገባው የግሥ መደብ "ኤኬኖሴን" ἐκένωσεν ሲሆን ሥርወ-ቃሉ "ኬኖ" κενόω ነው፥ "ባዶ አደረገ" የሚለውን አንዳንድ የፕሮቴስታንት አንጃ እና ጎጥ፦ "አምላክነቱን ትቶ መጣ" በሚል ይረዱታል። አምላክነት የሆነ ቦታ አስቀምጠህ የምትመጣበት ጃኬት አይደለም፥ መጨመር እና መጉደል የፍጡር እንጂ የመለኮት ባሕርይ አይደለም። ነገር ግን እንደ ጳውሎስ ትምህርት ኢየሱስ ሕይወቱን በመስጠት ለሰው ልጆች ሲል ድሀ ሆነ ይለናል፦
2 ቆሮንቶስ 8፥9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።
"ቸር ስጦታ" የተባለው ሕይወቱን መስጠቱን እንደሆነ ብዙ ቦታ ተናግሯል፦ ገላትያ 1፥4 ቲቶ 2፥14 ተመልከት! "ራሱን ባዶ አደረገ" ማለት "ራሱን አሳልፎ ሰጠ" ማለት ነው፥ ሕይወትን አሳልፎ ከሰጠ ትልቁ ድህነት(ባዶነት) ነው።
"የባሪያ መልክ" ማለት "ባርነት" ማለት ነው፥ ለምሳሌ "የአምልኮ መልክ" ማለት "አምልኮት" ማለት ነው፦
2 ጢሞቴዎስ 3፥5 የአምልኮት "መልክ" አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።
ἔχοντες μόρφωσιν εὐσεβείας τὴν δὲ δύναμιν αὐτῆς ἠρνημένοι· καὶ τούτους ἀποτρέπου.
"ሞርፎሲስ" μόρφωσις ወይም "ሞርፌ" μορφή የሚሉት ቃላት "ሞርፎ" μορφόω ከሚል ግሥ መደብ የመጣ ሲሆን "መልክ"form" ማለት ነው፥ ኢየሱስ ባርነት ይዞ እራሱን አዋረደ፦
ፊልጵስዩስ 2፥8 በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ።
ἐταπείνωσεν ἑαυτὸν γενόμενος ὑπήκοος
ኢየሱስ፦ "ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል" ብሎ ባስተማረው መሠረት ራሱን በትህትና በማዋረዱ አምላክ ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፦
ማቴዎስ 23፥12 ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።
καὶ ὅστις ταπεινώσει ἑαυτὸν ὑψωθήσεται.
ፊልጵስዩስ 2፥9 በዚህ ምክንያት ደግሞ አምላክ ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው።
διὸ καὶ ὁ Θεὸς αὐτὸν ὑπερύψωσεν,
ከመላእክት ያሳነሰው እና እራሱን በማዋረዱ ከፍ ከፍ ያደረገው አንዱ አምላክ ከሆነ አንዱ አምላክ እና ኢየሱስ ሁለት ለየቅል ማንነት እና ምንነት ይሆናሉ፥ በምንነት ከተለያዩ ኢየሱስ ከአምላኩ ጋር በባሕርይ ሊስተካከል አይችልም። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም