በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 51፥56 ጂኒን እና ሰውን ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ
ጂን እና ሰው የተፈጠሩበት ዓላማ ሁሉንም የፈጠረውን አንዱን አምላክ አሏህን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው። ወደ ባይብሉ ከመጣን ግን ኃጢአተኛ የተፈጠረው ለገሃነም ነው፦
ምሳሌ 16፥4 ያህዌህ ሁሉን ለእርሱ ለራሱ እንዲሁ ኅጥኣንን ደግሞ ”ለክፉ ቀን ፈጠረ። כֹּ֤ל פָּעַ֣ל יְ֭הוָה לַֽמַּעֲנֵ֑הוּ וְגַם־רָ֝שָׁ֗ע לְיֹ֣ום רָעָֽה׃
"ክፉ ቀን" ለሚለው የገባው ቃል "ዩውም ራህ" יֹ֣ום רָעָֽה ሲሆን "ዩውም" י֣וֹם በሚለው መነሻ ቅጥያ ላይ "ለ" לְ የሚል መስተዋድድ መግባቱ በራሱ ኃጥአን የተፈጠረው ለክፉ ቀን"doomsday" እንደሆነ ያሳያል፥ ይህ ክፉ ቀን የጥፋት ቀን ሲሆን ፈጣሪ ኅጥኣንን በገሃነም የሚያጠፋበት ክፉ ቀን ነው፦
ኤርምያስ 17፥18 "ክፉንም ቀን" አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት "አጥፋቸው"።
ማቴዎስ 10፥28 ይልቁንስ ነፍስን እና አካልን በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።
φοβεῖσθε δὲ μᾶλλον τὸν δυνάμενον καὶ ψυχὴν καὶ σῶμα ἀπολέσαι ἐν γεέννῃ.
"ኅጥኣን" ማለት "ኃጢአተኛ" ማለት ነው፥ የፍርዱ ቀን ለጻድቃን መልካም ቀን ሲሆን ለኃጥአን ክፉ ቀን ነው። የሚያፈርስን ኃጢአተኛ እንዲያጠፋ የፈጠረው እራሱ ያህዌህ ነው፥ ይህንን ያደረገው ገና እናታቸው ማኅፀን ውስጥ ሲፈጥራቸው ነው፦
ኢሳይያስ 54፥16 የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ። וְאָנֹכִ֛י בָּרָ֥אתִי מַשְׁחִ֖ית לְחַבֵּֽל
መዝሙር 58፥3 ኅጥኣን ከማኅፀን ጀምረው ተለዩ፤ ከሆድም ጀምረው ሳቱ፥ ሐሰትንም ተናገሩ።
ኅጥኣን እናታቸው ማኅፀን ውስጥ ምን አንደበት ኖሯቸው ነው ሐሰትን የተናገሩት? ያኔስ ማን አሳስታቸው ነው የሳቱት? መልሳቸው ወሒድ ሆይ! ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ "ለ"ክብር አንዱንም "ለ"ውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? የሚል ነው፦
ሮሜ 9፥21 ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ "ለ"ክብር አንዱንም "ለ"ውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን?
ስለዚህ አምላክ ሰውን ከጭቃ ሢሠራ አንዱን ለክብር ሌላውን ለውርደት ሊሠራ ሥልጣን ካለው በምን ሒሳብ ይሆን የአሏህን ንግግር ለመተቸት ሞራሉ ያላችሁ? የክርስትና አንጃ"sect" ፕሮቴስታንት ሲሆን ከፕሮቴስታንት ጎጥ"denomination" ደግሞ የካልቪኒዝም ጎጥ ለሕዱስ ሥነ-መለኮት"reformed theology" ፈር ቀዳጅ እና ፋና ወጊ ነው፥ የካልቪኒዝም መሥራች ዮሐንስ ካልቪን እንደ ጎርጎርዮሳውያን አቆጣጠር በ 1539 ድኅረ ልደት "የክርስትና ሃይማኖት ተቋማት" በሚል በጻፈው መጽሐፉ፦ "ሰዎች አንዳንዶቹ ለመዳን ሌሎች ደግሞ ለጥፋት አስቀድሞ መወሰን ተገብቷቸዋል" ብሏል፦
"ሰዎች አንዳንዶቹ ለመዳን ሌሎች ደግሞ ለጥፋት አስቀድሞ መወሰን ተገብቷቸዋል" Mankind some should be predestined to salvation and others to destruction.
The institutes of the christian religion Book 3 Chapter 21 Page 766
ግርድፍ እና ሽርክት ትርጉም ስለሆነብኝ እንግሊዝኛውን እዩት! "የሚድኑት እና የሚጠፉትን አስቀድ ወስኗል" የሚለው የካልቪን እሳቤ "ድርብ ቅድመ ውሳኔ"double predestination " ይባላል። ከካልቪን በፊት የሂፓ አውግስጢኖስ በድርብ ቅድመ ውሳኔ ያምናል፦
"ለምን እንግዲህ በምህረት ከሚያስተምረው በቀር ሁሉንም ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ አብ ሁሉንም አላስተማረም? በዚያው ልክ የማያስተምራቸውን በፍርድ አያስተምራቸውም? "እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም ደንዳና ያደርገዋል" ሮሜ 9፥18። ነገር ግን መልካም ነገር በመስጠት ይምራል፥ ምን ያህን እንደሚገባ በሚክስ ጊዜ ያደነድናል።
On the Predestination of the Saints (Augustine) Book 1 Chapter 14
ካልቪን ሆነ አውግስጢኖስ ይህንን እሳቤ ያገኙት ከጳውሎስ ትምህርት ነው። ባይብል ላይ በመደረግ ሊጠፉ የተወሰኑ ሰዎች እንዳሉ እና እነዚህ ሰዎች "ከብዙ ጊዜ በፊት" ማለትም "ምንም ነገር ሳይፈጠር" ለፍርድ እንደተጻፉ ይናገራል፦
ቆላስይስ 2፥22 እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና።
ይሁዳ 1፥4 ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ "የተጻፉ" አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና።
መዝሙር 139፥16 ለእኔ የተወሰኑልኝ ዘመናት ገና አንዳቸውም ወደ መኖር ሳይመጡ በመጽሐፍህ ተመዘገቡ። (አዲሱ መደበኛ ትርጉም) גלמי ראו עיניך ועל ספרך כלם יכתבו ימים יצרו ולא אחד בהם׃
እዚህ አንቀጽ ላይ የአዲሱ መደበኛ ትርጉም ላይ "መጽሐፍ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል በዕብራይስጡ "ሰፈር" סֵפֶר ሲሆን ይህም መጽሐፍ ሰው ወደ መኖር ከመምጣቱ በፊት ተወስኖ የተጻፈበት መጽሐፍ ነው፥ ይህንን የአዲሱ መደበኛ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ፦ "የሰው የሕይወት ዘመን በእግዚአብሔር የተወሰነ ነው፥ "በመጽሐፍህ" የእግዚአብሔር ውሳኔዎች ሁሉ የተጻፉበት የሰማይ መዝገብ ነው" በማለት ያትታል። የ 1954 እትም ደግሞ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ ሳይፈጠሩ በመጽሐፍ እንደተጻፉ ይናገራል፦
መዝሙር 139፥16 የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ
አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።
καὶ ἐπὶ τὸ βιβλίον σου πάντες γραφήσονται· ἡμέρας πλασθήσονται καὶ οὐθεὶς ἐν αὐτοῖς.
እዚህ አንቀጽ ላይ በግሪክ ሰፕቱአጀንት ላይ "መጽሐፍ" ተብሎ የተቀመጠው ቃል "ቢብሊዮን" βιβλίον ነው፥ "አንድ ስንኳ ሳይኖር" ማለት "ምንም ነገር ሳይኖር" ማለት ሲሆን ምንም ነገር ሳይፈጠር የሰዎች ሁኔታ በአምላክ መጽሐፍ ተጽፏል። ይህንን ኤጲፋንዮስ በቅዳሴ ላይ፦ "ሁሉ በመጽሐፉ የተጻፈ ነው" በማለት ይናገራል፦
የኤጲፋንዮስ ቅዳሴ 14፥15 "ከእርሱ የሚሰወር የለም፣ ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተገለጠ ነው፣ በዓይኖቹ ፊት ሁሉ የተዘረጋ ነው፣ ሁሉ በመጽሐፉ የተጻፈ ነው"።
ስለዚህ ሰዎች ለመካድ ሾልከው የገቡት ምንም ነገር ሳይፈጠር በፊት ለፍርድ የተጻፉ ስለሆኑ ነው። ክርስቲያኖች ሆይ! ውልፍጥ ዝልፍጥ ወለም ዘለም ሳትሉ ሰጥ እረጥ ለጥ ብላችሁ አንዱን አምላክ አሏህን እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም