በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 51፥56 ጂኒን እና ሰውን ሊያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ
ጂን እና ሰው የተፈጠሩበት ዓላማ ሁሉንም የፈጠረውን አንዱን አምላክ አሏህን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው፦
ቁርኣን 51፥56 ጂኒን እና ሰውን "ሊ"ያመልኩኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡
وَمَا خَلَقْتُ الْجِنَّ وَالْإِنسَ إِلَّا لِيَعْبُدُونِ
እዚህ አንቀጽ ላይ "የዕቡዱኒ" يَعْبُدُونِ በሚለው ግሥ መነሻ ቅጥያ ላይ "ሊ" لِ የምትል መስተዋድድ አለች፥ ይህቺ "ላም" ل በነሕው ሕግ "ላሙ-አት-ታዕሊል" لَام الْتَاعْلِل ትባላለች። "ታዕሊል" تَاعْلِل ማለት "ግልጽ ዓላማ" ማለት ሲሆን አሏህ ጂንን እና ሰውን የፈጠረበት ዓላማ እርሱን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ነው፥ እያንዳንዱ ሙሐከማት ሁሉ ደግሞ ዒባዳህ ነው። "ላሙ-አት-ታዕሊል" ለመረዳት በነሕው አወቃቀር አንድ ናሙና እስቲ እንመልከት፦
ቁርኣን 28፥9 የፈርዖንም ሚስት፦ "ለ"እኔ እና "ለ"አንተ የዓይኔ መርጊያ ነው፡፡ አትግደሉት! ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና» አለች፡፡
وَقَالَتِ امْرَأَتُ فِرْعَوْنَ قُرَّتُ عَيْنٍ لِّي وَلَكَ ۖ لَا تَقْتُلُوهُ عَسَىٰ أَن يَنفَعَنَا أَوْ نَتَّخِذَهُ وَلَدًا
"እኔ" እና "አንተ" ከሚለው በፊት ያለችው "ላም" ل ላሙ-አት-ታዕሊል ስትሆን ፈርዖን እና ሚስቱ ሙሣን ያነሱበት ዓላማቸው ይጠቅመናል ብለው ሊያሳድጉት እንደሆነ ታሳያለች፥ ነገር ግን አድጎ ምን እንደሚያደርግ ፍጻሜውን ዐያውቁትም፦
ቁርኣን 28፥9 እነርሱም ፍጻሜውን የማያውቁ ሆነው አነሱት፡፡
وَقَالَتِ امْرَأَتُ فِرْعَوْنَ قُرَّتُ عَيْنٍ لِّي وَلَكَ ۖ لَا تَقْتُلُوهُ عَسَىٰ أَن يَنفَعَنَا أَوْ نَتَّخِذَهُ وَلَدًا وَهُمْ لَا يَشْعُرُونَ
አምላካችን አሏህ ሁሉን ዐዋቂ በመሆኑ ፍጻሜውን ስለሚያውቅ "ለእነርሱ ጠላት እና ሐዘን ይሆን ዘንድ አነሱት" ብሎ ነገረን፦
ቁርኣን 28፥8 የፈርዖን ቤተሰቦችም መጨረሻው "ለ"እነርሱ ጠላት እና ሐዘን "ይሆን ዘንድ" አነሱት፡፡
فَٱلْتَقَطَهُۥٓ ءَالُ فِرْعَوْنَ لِيَكُونَ لَهُمْ عَدُوًّۭا وَحَزَنًا
"የኩነ" يَكُونَ በሚለው ግሥ መነሻ ቅጥያ ላይ "ሊ" لِ የምትል መስተዋድድ አለች፥ ይህቺ "ላም" ل በነሕው ሕግ "ላሙል-ዓቂባህ" لَام الْعَاقِبَة ትባላለች። "ዓቂባህ" عَاقِبَة ማለት "ፍጻሜ" ማለት ሲሆን አሏህ ፍጻሜውን በማወቁ የነገረን ንግግር ነው። በተመሳሳይ አምላካችን አሏህ ጂን እና ሰው የፈጠረበት ዓላማ እርሱን እንዲያመልኩ ሲሆን ቅሉ ግን ጂን እና ሰው በነጻ ፈቃዳቸው አሏህን መታዘዝ ሲችሉ ጀነትን በተቃራኒው ሲያምጹ ጀሃነም ይገባሉ፥ ከጂን እና ከሰው በአሏህ ላይ ስለሚያምጹት አሏህ እንዲህ ይለናል፦
ቁርኣን 7፥179 "ከ"ጂኒ እና "ከ"ሰው ብዙዎችን "ለ"ገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡
وَلَقَدْ ذَرَأْنَا لِجَهَنَّمَ كَثِيرًا مِّنَ الْجِنِّ وَالْإِنسِ
"ጀሀነም" جَهَنَّمَ በሚለው ቃል መነሻ ላይ ያለችው "ላም" ل ላሙል-ዓቂባህ ስትሆን አሏህ ፍጻሜውን በማወቁ የነገረን ንግግር ለማመልከት የመጣች ናት። አሏህ "ሊያመልኩኝ" በሚልበት ጊዜ "ጂኒ እና ሰው" ሲል ለገሃነም በሚልበት ጊዜ ግን "ከ"ጂኒ" እና "ከ"ሰው" በማለት "ሚን" مِّن ማለትም "ከ" የሚል መስተዋድድ አስገብቷል። አንቀጹ ላይ ከጂኒ እና ከሰው ለገሃነም የዳረጋቸው ልብ እያላቸው አለማወቃቸው፣ ዓይን እያላቸው ዓለማየታቸው፣ ጆሮ እያላቸው አለመስማታቸው ነው፦
ቁርኣን 7፥179 ለእነርሱ በእርሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፣ ለእነርሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሉዋቸው፣ ለእነርሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሉዋቸው፡፡ እነዚያ እንደ እንስሳዎች ናቸው፡፡ ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው።
لَهُمْ قُلُوبٌ لَّا يَفْقَهُونَ بِهَا وَلَهُمْ أَعْيُنٌ لَّا يُبْصِرُونَ بِهَا وَلَهُمْ آذَانٌ لَّا يَسْمَعُونَ بِهَا ۚ أُولَـٰئِكَ كَالْأَنْعَامِ بَلْ هُمْ أَضَلُّ ۚ أُولَـٰئِكَ هُمُ الْغَافِلُونَ
እንስሳ ውሳጣዊ ልብ፣ ዓይን፣ ጆሮ የለውም፥ እነዚህ ግን ውሳጣዊ ማመዛዘኛ እያላቸው ባለመጠቀም እንደ እንስሳ ናቸው። ሆን ብለው በመሳሳት ዘንጊዎች ናቸው፥ ከጂኒ እና ከሰው በአሏህ ላይ ያመጹትን አሏህ በጀሀነም እንደሚቀጣ ሁሉ ከጂኒ እና ከሰው አሏህን የሚፈሩት ጀነትን ይመነዳል፦
ቁርኣን 55፥45 ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ?
فَبِأَيِّ آلَاءِ رَبِّكُمَا تُكَذِّبَانِ
ቁርኣን 55፥46 በጌታውም ፊት መቆምን ለፈራ ሁለት ገነቶች አሉት፡፡
وَلِمَنْ خَافَ مَقَامَ رَبِّهِ جَنَّتَانِ
ቁርኣን 4፥124 "ከ"ወንድ ወይም "ከ"ሴት እርሱ አማኝ ኾኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳችን የሚሠራ እነዚያ ገነትን ይገባሉ፡፡
وَمَن يَعْمَلْ مِنَ الصَّالِحَاتِ مِن ذَكَرٍ أَوْ أُنثَىٰ
ለገሃነም "ፈጠርን" የሚለው ቃል "ዘረእና" ذَرَأْنَا ሲሆን "ጀዐልና" جَعَلْنَا ማለትም "አደረግን" በሚል ይመጣል፥ ለምሳሌ፦ ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። አሏህን ግን ሞትን እንደፈጠረ ይናገራል፦
ቁርኣን 67፥2 ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መኾኑን ሊፈትናችሁ ሞትን እና ሕይወትን የፈጠረ ነው፡፡
الَّذِي خَلَقَ الْمَوْتَ وَالْحَيَاةَ لِيَبْلُوَكُمْ أَيُّكُمْ أَحْسَنُ عَمَلًا
ሰው ያልነበረበት ሁኔታ ሕይወት አልባ ሲሆን "ሙታን" ተብሏል፥ ከአለመኖር ሁኔታ ወደ መኖር መምጣትን "ሕያውን ከሙት ያወጣል" ይለዋል፦
ቁርኣን 30፥19 ሕያውን ከሙት ያወጣል፥ ሙታንም ከሕያው ያወጣል፡፡
يُخْرِجُ الْحَيَّ مِنَ الْمَيِّتِ وَيُخْرِجُ الْمَيِّتَ مِنَ الْحَيِّ
ቁርኣን 2፥28 ሙታን የነበራችሁ ስትኾኑ ሕያው ያደረጋችሁ፣ ከዚያም የሚያሞታችሁ፣ ከዚያም ሕያው የሚያደርጋችሁ ሲኾን፣ ከዚያም ወደ እርሱ የምትመለሱ ስትኾኑ በአላህ እንዴት ትክዳለችሁ?
كَيْفَ تَكْفُرُونَ بِاللَّهِ وَكُنتُمْ أَمْوَاتًا فَأَحْيَاكُمْ ۖ ثُمَّ يُمِيتُكُمْ ثُمَّ يُحْيِيكُمْ ثُمَّ إِلَيْهِ تُرْجَعُونَ
ስለዚህ አሏህ "ከ"ጂኒ እና "ከ"ሰው "ለ"ገሀነም በእርግጥ አደረግን" ቢል ለገሃነም ማድረጉ ፍትሐዊ ቅጣቱ አይደለምን? በእርግጥ ከጂን እና ከሰው ዲያብሎስን የተከተለ ጀሀነም ይገባል፦
ቁርኣን 38፥85 ከአንተ እና ከእነርሱ ውስጥ ከተከተሉህ በአንድ ላይ ገሀነምን በእርግጥ እሞላታለሁ፡፡
لَأَمْلَأَنَّ جَهَنَّمَ مِنكَ وَمِمَّن تَبِعَكَ مِنْهُمْ أَجْمَعِينَ
ቁርኣን 32፥13 ግን ገሀነምን ከጂን እና ከሰው የተሰበሰቡ ሆነው በእርግጥ እሞላለሁ ማለት ቃሉ ከእኔ ተረጋግጧል፡፡
وَلَـٰكِنْ حَقَّ الْقَوْلُ مِنِّي لَأَمْلَأَنَّ جَهَنَّمَ مِنَ الْجِنَّةِ وَالنَّاسِ أَجْمَعِينَ
አሏህ ለተፈጠርንበት ዓላማ እርሱን ብቻ ለማምለክ ይርዳን! ከጀሀነም ቅጣት ይጠብቀን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም