በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

ቁርኣን 2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ

"ሡጁድ" سُّجُود የሚለው ቃል "ሠጀደ" سَجَدَ ማለትም "ሰገደ" "ታዘዘ" "ተገዛ" ከሚለው ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ስግደት" "መታዘዝ" "መገዛት" ማለት ነው፥ ሡጁድ ደግሞ "ሡጁዱል ዒባዳህ" እና "ሡጁዱ አ-ተሒያህ" ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ።
1ኛ. “ዒባዳህ” عِبَادَة የሚለው ቃል “ዓበደ" عَبَدَ ማለትም “አመለከ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “አምልኮ” ማለት ነው፥ ይህ የአምልኮ ስግደት “ሡጁዱል ዒባዳህ” سُّجُود العِبَادَة ሲባል ለአሏህ ብቻ የሚቀርብ እና የሚሰጥ ነው።
2ኛ. “ተሒያህ” تَحِيَّة የሚለው ቃል “ሐያ” حَيَّا ማለትም “አከበረ” “እጅ ነሳ” “ሰላምታ ሰጠ” ከሚለው ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “አክብሮት” “እጅ መንሳት” “ሰላምታ” ማለት ነው፥ ይህ የአክብሮት ስግደት "ሡጁዱ አ-ተሒያህ" سُّجُود التَحِيَّة ሲባል ለምሳሌ የዩሡፍ ቤተሰብ ለዩሡፍ የሰገዱት ስግደት "ሡጁዱ አ-ተሒያህ" ነው፦

ቁርኣን 12፥4 ዩሱፍ ለአባቱ፡- «አባቴ ሆይ! እኔ አሥራ አንድ ከዋክብትን፣ ፀሐይን እና ጨረቃን በሕልሜ አየሁ፡፡ "ለእኔ ሰጋጆች" ሆነው አየኋቸው» ባለ ጊዜ አስታውስ፡፡
إِذْ قَالَ يُوسُفُ لِأَبِيهِ يَا أَبَتِ إِنِّي رَأَيْتُ أَحَدَ عَشَرَ كَوْكَبًا وَالشَّمْسَ وَالْقَمَرَ رَأَيْتُهُمْ لِي سَاجِدِينَ
ቁርኣን 12፥100 ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፡፡ “ለእርሱም ሰጋጆች ኾነው” ወረዱለት፡፡ እርሱም፦ «አባቴም ሆይ! ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፡፡ ጌታ በእርግጥ እውነት አደረጋት» አለ፡፡
وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ وَخَرُّوا لَهُ سُجَّدًا ۖ وَقَالَ يَا أَبَتِ هَـٰذَا تَأْوِيلُ رُؤْيَايَ مِن قَبْلُ قَدْ جَعَلَهَا رَبِّي حَقًّا

አምላካችን አሏህ ለመላእክትም፦ "ለአደም ስገዱ" ብሎ ያዘዛቸው በተመሳሳይ ሡጁዱ አ-ተሒያህ ነበር፦

ቁርኣን 2፥34 ለመላእክትም «ለአደም ስገዱ» ባልን ጊዜ አስታውስ፡፡
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ

ይህ ስግደት የአክብሮት ስግደት ሲሆን በክሌመንት መጽሐፍ ላይ ደግሞ "እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ለአዳም ሰገዱ" ይለናል፥ በተጨማሪም ኢየሱስ ዳግም ሲመጣ የሰይጣን ማኅበር ለፊልድልፍያ ኤጲስ ቆጶስ እንዲሰግዱለት እንደሚያደርግ ተናግሯል፦

ቀሌምንጦስ 1፥41 አራዊት፣ እንስሳት፣ ወፎች እና እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ወደ አዳም ተሰበሰበ ከፊቱም ቁመው ራሳቸውን አዘነበሉ ለአዳም ሰገዱ።
ራእይ 3፥9 እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት "ይሰግዱ" ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።

ይህ ስግደት የአክብሮት ስግደት እንደሆነ እሙን እና ቅቡል ነው። በቁርኣን ውስጥ መላእክት ለአደም እንደ ሰገዱለት እና ኢብሊሥ የአሏህን ትእዛዝ በማመጽ እንቢ እንዳለ ይናገራል፦

ቁርኣን 2፥34 ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፥ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፤ ኮራም ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ أَبَىٰ وَاسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ

ሰይጣን ለአዳም ከፈጣሪ የተሠጠውን ሀብተ ጸጋ ባየ ጊዜ ከዚች ሰዓት ጀምሮ ቅንአት አደረበት፥ ሁሉም ፍጥረት ሲሰግዱ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ግን "አልሰግድም" በማለቱ ተዋርዷል፦

ቀሌምንጦስ 1፥46 ሰይጣን ለአዳም ከእግዚአብሔር የተሠጠውን ሀብተ ጸጋ ባየ ጊዜ ከዚች ሰዓት ጀምሮ ቅንአት አደረበት ።
ቀሌምንጦስ 1፥47 በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በሰይጣን ላይ የነበረውን የምሥጋና ልብስና የግርማ ልዕልና አስወገደ።
2ኛ መቃብያን 9፥3 ክሣደ ልቡናውን በማጽናት እና ራሱን በማኩራት ፈጣሪው ለፈጠረው ለአዳም መስገድን እምቢ እንዳለ አንተም መምህር ዲያብሎስ እንዳደረገ ለፈጣሪህ ለእግዚአብሔር መስገድ እምቢ ብለሃልና።
3ኛ መቃብያን 1፥6 "ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው ስለ አዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና።

ይህ የአክብሮት ስግደት ከአምልኮ ስግደት የሚለየው በኒያህ ነው፥ “ኒያህ” نِيَّة የሚለው ቃል “ነዋ” نَوَى ማለትም “ወጠነ” ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን “ውጥን”intention” ማለት ነው። ነገር ግን ይህ የአክብሮት ስግደት አቅጣጫውን ቀይሮ አምልኮ እየሆነ ስላለ፥ በነቢያችን”ﷺ” ጊዜ ቁርኣን ሲወርድ ተከለከለ፦

ቁርኣን 41፥37 ሌሊትና ቀንም ፀሐይና ጨረቃም ከምልክቶቹ ናቸው፡፡ ለፀሐይና ለጨረቃ አትስገዱ፡፡ ለእዚያም ለፈጠራቸው አላህ ስገዱ፡፡ እርሱን ብቻ የምታመልኩ እንደ ኾናችሁ "ለሌላ አትስገዱ"፡፡
وَمِنْ آيَاتِهِ اللَّيْلُ وَالنَّهَارُ وَالشَّمْسُ وَالْقَمَرُ ۚ لَا تَسْجُدُوا لِلشَّمْسِ وَلَا لِلْقَمَرِ وَاسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي خَلَقَهُنَّ إِن كُنتُمْ إِيَّاهُ تَعْبُدُون
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 9, ሐዲስ 1926:
ዐብደላህ ኢብኑ አቢ ዐውፋ እንደተረከው፦ ”ሙዓዝ ኢብኑ ጀበል ከሻም ምድር በተመለሰ ጊዜ ለነቢዩ”ﷺ” ሰገደ፥ እሳቸውም፦ “ሙዓዝ ሆይ! ይህ ምንድነው እሱ? አሉት። እርሱም፦ “ሻም ምድር ሄጄ ነበር፥ ለኤጲስ ቆጶሳቶቻቸው እና ለጳጳሳቶቻቸው ሲሰግዱ ተመለከትኩ። ይህንን ለእርሶ ልንሠራው ተመኘሁ” አለ። የአሏህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “ይህንን በፍጹም እንዳትሠሩ!”።
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ أَبِي أَوْفَى، قَالَ لَمَّا قَدِمَ مُعَاذٌ مِنَ الشَّامِ سَجَدَ لِلنَّبِيِّ ـ صلى الله عليه وسلم ـ قَالَ ‏”‏ مَا هَذَا يَا مُعَاذُ ‏”‏ ‏.‏ قَالَ أَتَيْتُ الشَّامَ فَوَافَقْتُهُمْ يَسْجُدُونَ لأَسَاقِفَتِهِمْ وَبَطَارِقَتِهِمْ فَوَدِدْتُ فِي نَفْسِي أَنْ نَفْعَلَ ذَلِكَ بِكَ ‏.‏ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ ‏”‏ فَلاَ تَفْعَلُوا

ስለዚህ አሏህ ለአደም "ስገዱ" ማለቱ "አምልኩ" ማለቱ ሳይሆን "አክብሩ" ማለቱ እንደሆነ ተረድታችሁ የወጠጤ እና የውርጋጥ ስድባችሁን ብታቆሙ መልካም ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ ወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም