በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ

በባይብልም አምላክ ለኢየሱስ የሰጠውን ቃል ወንጌል ይለዋል፥ ይህንን የአምላክ ወንጌል ኢየሱስ ሲሰብከው ነበረ፦

ዮሐንስ 17፥8 "የሰጠኸኝን ቃል" ሰጥቻቸዋለሁና።
ዮሐንስ 17፥14 እኔ "ቃልህን" ሰጥቻቸዋለሁ።
ሉቃስ 4፥18 ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና።
ማርቆስ 1፥14 ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የአምላክን ወንጌል እየሰበከ ወደ ገሊላ መጣ።
Καὶ μετὰ τὸ παραδοθῆναι τὸν Ἰωάνην ἦλθεν ὁ Ἰησοῦς εἰς τὴν Γαλιλαίαν κηρύσσων τὸ εὐαγγέλιον τοῦ Θεοῦ

ኢየሱስ አምላኩ የሰጠውን የአምላክ ወንጌል ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሰጥቶ እነርሱም ይህን ወንጌልን ሰበኩ፥ ይህ ወንጌል ለእስራኤል ቤት እንጂ ለአሕዛብ እና ለሳምራውያን አልመጣም፦

ሉቃስ 9፥6 ወጥተውም "ወንጌልን እየሰበኩ" እና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።
ማቴዎስ 10፥5-6 እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ፦ "በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፥ ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ"።

"መሢሕ ይመጣል" ብለው የሚጠብቁት አይሁዳውያን እንጂ አሕዛብ ስላልሆነ የመሢሑ ወንጌል ትርጉም ያለው ለእስራኤል ቤት ብቻ ነው፥ ኢየሱስ ከአብ የተላከው ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ሲሆን በተመሳሳይ ኢየሱስ ሐዋርያትን የላከው የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነው፦
ማቴዎስ 15፥24 እርሱም መልሶ፦ "ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም" አለ።

ዮሐንስ 20፥21 ኢየሱስም ዳግመኛ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ" አላቸው።

"አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ" የሚለው ይሰማርበት! በ 70 ድኅረ ልደት ጀነራል ጢጦስ ኢየሩሳሌም እና ቤተ መቅደሱን በእሳት ሲያጋይ የእስራኤል ቤት ተበተኑ፦

ያዕቆብ 1፥1 የእግዚአብሔር እና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ "ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች" ሰላም ለእናንተ ይሁን።

የተበተኑት ቅድሚያ በአሶር፣ ቀጥሎ በባቢሎን፣ ለጥቆ በሮማውያን ነው። የእስራኤል ቤት አሥራ ሁለቱ ነገዶች ሲኖሩት በኢየሱስ የተሾሙት ወንጌሉን ለእስራኤል ቤት የሚናገሩት ሐዋርያትም አሥራ ሁለት ብቻ እና ብቻ ናቸው፦

ማቴዎስ 19፥28 እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።

ወንጌሉን ካሰሙ በኃላ የፍርድ ቀን በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ለመፍረድ በአሥራ ሁለት ዙፋን ላይ የሚቀመጡት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያ ብቻ ናቸው። የእስራኤል ቤት የተገረዙ አይሁዳውያን ሲሆኑ የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ዋና መሪ ጴጥሮስ ከኢየሱስ ለተገረዙት የሆነ ሐዋርያ ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ እራሱን "ለአሕዛብ ሐዋርያ" በማድረግ እራሱን ሾሟል፦

ገላትያ 2፥8 "ለተገረዙት ሐዋርያ" እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ "ለአሕዛብ ሐዋርያ" እንድሆን ሠርቶአልና።

በዚህም ምክንያት ጴጥሮስ "ለተገረዙት የሆነው ወንጌል" ከኢየሱስ አደራ እንደተሰጠው ጳውሎስ ደግሞ "ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል" አደራ እንደተሰጠው በማመላከት ሁለት ወንጌሎች ማለትም "ለተገረዙት የሆነው ወንጌል" እና "ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል" እንዳለት ጳውሎስ ተናግሯል፦

ገላትያ 2፥7 ተመልሰው ግን ጴጥሮስ "ለተገረዙት የሆነው ወንጌል" አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ "ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል" አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ።

ጳውሎስ ለአሕዛብ(ለግሪካውያን እና ለሮማውያን) የሰበከው የኢየሱስን ወንጌል እና የትንሳኤውን ወንጌል በመቀላቀል ነው፦

የሐዋርያት ሥራ 17፥18 ሌሎችም የኢየሱስን እና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው፦ "አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል" አሉ።

ጳውሎስ በግሪክ አቴና ከኤፊቆሮስ ወገን እና ኢስጦኢኮች ከተባሉት ፈላስፎች ሲገናኝ "የትንሳኤውን ወንጌል" ሲሰብክላቸው "አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል" ያሉት ምክንያት አዲሶቹ አማልክት የተባሉት ሞተው የተነሱት አማልክት"Dying-and-rising deitys" ሲሆኑ እነርሱም "አቲስ" Ἄττις የሚባለው አምላክ፣ "ዛግሩስ" Ζαγρεύς የሚባለው አምላክ፣ "ዲኦንይሱስ" Διόνυσος የሚባለው አምላክ ናቸው።
ለዚህ ነው ከ 100-165 ድኅረ ልደት ይኖር የነበረው ዐቃቢ ክርስትና እና የሄለናዊ ፈላስፋ ዮስጦስ ሰማዕቱ"Justin Martyr" የኢየሱስ ስቅለት፣ ሞት እና ትንሳኤ የጂፒተር ልጆችን ግሪካውያን ከሚያምኑበት ጋር ተመሳሳይ እንጂ የተለያየ ነገር እንዳልሆነ የተናገረው፦
እንዲሁ የአምላክ በኵር የሆነው ቃል ያለ ተራክቦ መገኘት እና መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቀለ፣ ሞተ እና ተነሳ ስንል እናንተ የጂፒተር ልጆችን ከምታምኑባቸው ጋር ተመሳሳይን እንጂ የተለያየ ነገር አላመጣንም።
The Ante-Nicene Fathers: The first Apology of justin chapter 21

ጳውሎስ ይህ ላልተገረዙት የሆነ የትንሳኤ ወንጌል ከኢየሱስ እግር ሥር እንደ ሐዋርያቱ የሰማው ሳይሆን "ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል" በማለት በመገለጥ እንዳገኘው ይናገራል፦

ገላትያ 1፥11 ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።

ሄለናዊ ግሪክ ለሆኑት ለገላቲያ ሰዎች ጳውሎስ የሰበከው ላልተገረዙት የሆነ የትንሳኤ ወንጌል ሲሆን እርሱ ከሚሰብከው ላልተገረዙት ከሆነው ወንጌል ሌላ የተገረዙት ለሆኑት የሆነውን ወንጌል የሰበከ እርግማን እንዳለበት ተናግሯል፦

ገላትያ 1፥8 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ "ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን" ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።

ጳውሎስ "ተገለጠልኝ" የሚለው ይህን የአሕዛብ ወንጌል ለዋኖቹ ለአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንደነገራቸው፣ ለእነዚህ ዋነኞች አለቆች ግድ እንደማይሰጠው እና ኬፋን(ጴጥሮስን) እንደተቃወመው ሊፈረድበት እንደሚገባ ተናግሯል፦

ገላትያ 2፥2 ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።
ገላትያ 2፥6 አለቆች የመሰሉት ግን በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥
ገላትያ 2፥11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።
ገላትያ 2፥9 "አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብ፣ ኬፋ እና ዮሐንስ እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔ እና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን።

"አምድ" ማለት "ምሰሶ" "መሠረት" ማለት ነው፥ የአምድ ብዙ ቁጥር "አዕማድ" ሲሆን "ምሰሶዎች" "መሠረቶች" ማለት ነው። አዕማድ የሆኑትን ያዕቆብን፣ ኬፋን እና ዮሐንስን "አዕማድ መስለው የሚታዩ" ብሎ መወረፍ አግባብ አይደለም፥ የወረፈበት ምክንያት ኢየሱስ ባዘዛቸው መሠረት ወደ ተገረዙት ስለሄዱ ነው። ለኤክሌሲያ አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ እነርሱም አሥራ ሁለቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ብቻ እና ብቻ ናቸው፦

ራእይ 21፥14 ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።

ጳውሎስ ሄለናዊ ግሪክ ለሆኑት ለቆሮንቶስ ሰዎች ከሰበከው ኢየሱስ እና ከተቀበሉት የአሕዛብ ወንጌል ሌላ የሐዋርያቱ ኢየሱስ እና ወንጌል መጥቶ ቢሰበክ እንዳይቀበሉ አስጠንቅቋል፦

2ኛ ቆሮንቶስ 11፥4 የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።

በመቀጠል ዐውዱ ከላይ ከጳውሎስ የተለየ ወንጌል የሚሰብኩትን "እነዚህ" በማለት ዋኖቹ ሐዋርያት እንደሆኑ ጠቅሷል፦

2ኛ ቆሮንቶስ 11፥5 "ከ-"እነዚህ" ከዋነኞቹ ሐዋርያት በአንድ ነገር እንኳ እንደ ጎደልሁ ራሴን አልቆጥርም።

እነዚህን ዋነኞቹን ሐዋርያት ያዕቆብን፣ ኬፋን እና ዮሐንስን "ውሸተኞች ሐዋርያት እና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና" በማለት ይዘልፋቸዋል፦

2ኛ ቆሮንቶስ 11፥13 እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፥ ውሸተኞች ሐዋርያት እና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና።

አዲስ ኪዳን ላይ ካሉት ሦስት አራተኛ የሆኑት አሥራ ሦስት ደብዳቤዎች የጳውሎስ ደብዳቤዎች ናቸው፥ እነዚህን ደብዳቤዎች የአሕዛብ ወንጌል ሲሆኑ እነዚህን መጽሐፍት በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «የፈጣሪ ንግግር ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፦

ቁርኣን 2፥79 ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉ እና ከዚያም በእርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው፡፡
فَوَيْلٌ لِّلَّذِينَ يَكْتُبُونَ الْكِتَابَ بِأَيْدِيهِمْ ثُمَّ يَقُولُونَ هَـٰذَا مِنْ عِندِ اللَّهِ لِيَشْتَرُوا بِهِ ثَمَنًا قَلِيلًا ۖ

አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም