በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 2፥26 በእርሱ ብዙዎችን ያጠማል፥ በእርሱም ብዙዎችን ያቀናል፡፡ በእርሱም አመጸኞችን እንጅ ሌላን አያጠምም፡፡
يُضِلُّ بِهِ كَثِيرًا وَيَهْدِي بِهِ كَثِيرًا ۚ وَمَا يُضِلُّ بِهِ إِلَّا الْفَاسِقِينَ

አንድ ሰው ቁርኣንን ከሰማ ጊዜ ጀምሮ ሑጃህ ይቆምበታል፥ "ሑጃህ" حُجَّة ማለት "አስረጅ" ማለት ነው። ቁርኣን የተሟላ የአሏህ ሑጃህ ነው፦

ቁርኣን 6፥149 «የተሟላው አስረጅ የአላህ ነው፥ በሻም ኖሮ ሁላችሁንም ባቀናችሁ ነበር» በላቸው”፡፡
قُلْ فَلِلَّهِ الْحُجَّةُ الْبَالِغَةُ ۖ فَلَوْ شَاءَ لَهَدَاكُمْ أَجْمَعِينَ

አሏህ ሰውን አስገድዶ ለሁሉም ሂዳያህ መስጠት ቢፈልግ ችሎታው አለው፥ ቅሉ ግን የሰውን ነጻ ፈቃድ የሚጻረር ስለሆነ አሏህ ቁርኣንን ሑጃህ አርጎ አውርዷል። ቁርኣን ወደዚያች እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፥ ቁርኣን ካመንክበት ሂዳያህ የምትወፈቅበት ሑጃህ ይሆንልካል ወይም ከካድከው ደላላህ የምታገኝበት ሑጃህ ይሆንብካል፦

ቁርኣን 17፥9 ይህ ቁርኣን ወደዚያች እርሷ ቀጥተኛ ወደ ኾነችው መንገድ ይመራል፡፡
إِنَّ هَـٰذَا الْقُرْآنَ يَهْدِي لِلَّتِي هِيَ أَقْوَمُ وَيُبَشِّرُ الْمُؤْمِنِينَ
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 2, ሐዲስ 1
አቡ ማሊክ አል-አሽዐሪይ እንደተረከው፦ “የአሏህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ “ቁርኣን አስረጅ ይሆልካል ወይ አስረጅ ይሆንብካል”።
عَنْ أَبِي مَالِكٍ الأَشْعَرِيِّ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ” الْقُرْآنُ حُجَّةٌ لَكَ أَوْ عَلَيْكَ “

"ሂዳያህ" هِدَايَة የሚለው ቃል "ሀዳ" هَدَى ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ምሪት"guidance" ማለት ነው፥ "ሃዲያህ" هَدِيَّة የሚለው ቃል እራሱ "ስጦታ" ማለት ሲሆን ሂዳያህ ከአሏህ የሚሰጥ ተውፊቅ ነው። "ዶላላህ" ضَلَّة የሚለው ቃል "ዶለ" ضَلَّ ከሚለው ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ጥመት"misguidance" ማለት ነው፥ ዶላላህ ከአሏህ የሆነ ቅጣት ሲሆን ኪሳራ ነው። አምላካችን አሏህ በቁርኣን ብዙዎችን ያጠማል፥ በቁርኣን ብዙዎችን ያቀናል። የሚያቀናው የቁርኣንን መልእክት ተቀብለው የሚታዘዙትን ሲሆን የሚያጠመው ደግሞ የቁርኣንን መልእክት የሚያስተባብሉትን አመጸኞች ነው፦

ቁርኣን 39፥23 ይህ የአላህ መምሪያ ነው፡፡ በእርሱ የሚሻውን ሰው ይመራበታል፡፡ አላህም የሚያጠመው ሰው ለእርሱ ምንም አቅኚ የለውም፡፡
ذَٰلِكَ هُدَى اللَّهِ يَهْدِي بِهِ مَن يَشَاءُ ۚ وَمَن يُضْلِلِ اللَّهُ فَمَا لَهُ مِنْ هَادٍ
ቁርኣን 2፥26 በእርሱ ብዙዎችን ያጠማል፥ በእርሱም ብዙዎችን ያቀናል፡፡ በእርሱም አመጸኞችን እንጅ ሌላን አያጠምም፡፡
يُضِلُّ بِهِ كَثِيرًا وَيَهْدِي بِهِ كَثِيرًا ۚ وَمَا يُضِلُّ بِهِ إِلَّا الْفَاسِقِينَ
ቁርኣን 63፥6 አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አይመራምና፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ

"ማጥመም" ማለት "አለማቅናት" ማለት ከሆነ ቁርኣን ለሑጃህ ሲነበብ የተመራም ሰው የሚመራው ጥቅሙ ለራሱ ብቻ ነው፥ የጠመመም ሰው የሚጠመው ጉዳቱ በራሱ ላይ ነው፦

ቁርኣን 27፥92 ቁርኣንንም እንዳነብ ታዝዣለሁ፡፡ የተመራም ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፡፡ የጠመመ ሰውን «እኔ ከአስጠንቃቂዎች ነኝ እንጅ ሌላ አይደለሁም» በለው፡፡
وَأَنْ أَتْلُوَ الْقُرْآنَ ۖ فَمَنِ اهْتَدَىٰ فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ ۖ وَمَن ضَلَّ فَقُلْ إِنَّمَا أَنَا مِنَ الْمُنذِرِينَ
ቁርኣን 10፥108 «እናንተ ሰዎች ሆይ! እውነቱ ከጌታችሁ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ በእርሱ የተመራም ሰው የሚመራው ለራሱ ነው፡፡ የጠመመም ሰው የሚጠመው ጉዳቱ በራሱ ላይ ነው፡፡ እኔም በእናንተ ላይ ተጠባበቂ አይደለሁም» በላቸው፡፡
قُلْ يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَكُمُ الْحَقُّ مِن رَّبِّكُمْ ۖ فَمَنِ اهْتَدَىٰ فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ ۖ وَمَن ضَلَّ فَإِنَّمَا يَضِلُّ عَلَيْهَا ۖ وَمَا أَنَا عَلَيْكُم بِوَكِيلٍ

ከጌታችን የመጣው እውነት ቁርኣን ሲሆን ይህንን እውነት ያስተባበለ ሰው ይጠማል፥ የተቀበለ ሰው ይቀናል። ቁርኣን ተነቦለት አሻፈረኝ ካለ ነቢያች"ﷺ" በእርሱ ላይ ተጠባባቂ አይደሉም፥ እርሳቸው ከአስጠንቃቂ መልእክተኞች አንዱ እንጂ ሌላ አይደሉም። አምላካችን አሏህ መልእክተኛን እስከሚልክ ድረስ ማንንም አይቀጣም፦

ቁርኣን 17፥15 የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፥ የጠመመም ሰው የሚሚጠመው ጉዳቱ በእርሷ ላይ ነው፡፡ ተሸካሚም ነፍስ የሌላይቱን ነፍስ ኃጢኣት አትሸከምም፡፡ መልእክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም፡፡
مَّنِ اهْتَدَىٰ فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ ۖ وَمَن ضَلَّ فَإِنَّمَا يَضِلُّ عَلَيْهَا ۚ وَلَا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَىٰ ۗ وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّىٰ نَبْعَثَ رَسُولًا

"ዐድል" عَدْل ማለት "ፍትሕ" ማለት ሲሆን የቁርኣንን መልእክት ሰምቶ ያስተባለለውን አመጸኛ በዱንያህ አሏህ የሚቀጣው ቅጣት ማጥመም ሲሆን ፍትሕ ነው፥ "ፈድል" فَضْل ማለት "ችሮታ" ማለት ሲሆን የቁርኣንን መልእክት ሰምቶ ያመነው አማኝ በዱንያህ አሏህ የሚወፍቀው ስጦታ ፈድል ነው፦

ቁርኣን 22፥54 አላህም እነዚያን ያመኑትን ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ "መሪ" ነው፡፡
وَإِنَّ اللَّهَ لَهَادِ الَّذِينَ آمَنُوا إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ

አሏህ በስም መደብ "ሃዲ" هَادِ ማለትም "መሪ" ተብሏል እንጂ በስም መደብ "ሙዲል" مُضِلّ ማለትም "አጥማሚ" አልተባለም፥ አሏህ ማቅናቱ ባሕርይው ሲሆን ማጥመሙ ግን ቅጣቱ ነው። አሏህ እነዚያን ያመኑትን ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ ይመራል፥ ፍላጎት ያለው ሰው አምኖ የጌታውን መንገድ ይይዛል። አሏህም ወደ እርሱ በንስሓ የሚመለሰውን ሰው ይመራል፦

ቁርኣን 76፥29 ይህቺ መገሠጫ ናት፡፡ የሻም ሰው ወደ ጌታው መንገድን ይይዛል፡፡
إِنَّ هَـٰذِهِ تَذْكِرَةٌ ۖ فَمَن شَاءَ اتَّخَذَ إِلَىٰ رَبِّهِ سَبِيلًا
ቁርኣን 13፥27 «አላህ የሚሻውን ያጠምማል፥ የተመለሰውንም ሰው ወደ እርሱ ይመራል» በላቸው፡፡
قُلْ إِنَّ اللَّهَ يُضِلُّ مَن يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ أَنَابَ

እውነትትን ካወቁ በኋላ ከእውነት መዞር ጥመት እንጂ ሌላ ምንም የለም፥ እውነት ከመጣ በኃላ የፈለገ ማመን የፈለገ መካድ ይችላል፦

ቁርኣን 10፥32 እርሱ እውነተኛ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእውነትም በኋላ ጥመት እንጂ ሌላ ምን አለ? ከእውነት እንዴት ትዞራላችሁ?።
فَذَٰلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمُ الْحَقُّ ۖ فَمَاذَا بَعْدَ الْحَقِّ إِلَّا الضَّلَالُ ۖ فَأَنَّىٰ تُصْرَفُونَ
ቁርኣን 18፥29 «እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የሻም ሰው ይመን፤ የሻም ሰው ይካድ» በላቸው፡፡
وَقُلِ الْحَقُّ مِن رَّبِّكُمْ ۖ فَمَن شَاءَ فَلْيُؤْمِن وَمَن شَاءَ فَلْيَكْفُرْ
ቁርኣን 4፥170 እናንተ ሰዎች ሆይ! መልክተኛው እውነትን ከጌታችሁ አመጣላችሁ፡፡ እመኑም ለእናንተ የተሻለ ይኾናል፡፡ ብትክዱም በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአላህ ነውና፡፡
يَا أَيُّهَا النَّاسُ قَدْ جَاءَكُمُ الرَّسُولُ بِالْحَقِّ مِن رَّبِّكُمْ فَآمِنُوا خَيْرًا لَّكُمْ ۚ وَإِن تَكْفُرُوا فَإِنَّ لِلَّهِ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ

ማመን ለአማኙ የተሻለ ነው፥ መካድ ግን እራሱ ከሃዲውን እንጂ አሏህን ምንም አይጎዳም። ከእምነታቸው፣ መልክተኛውም እውነት መኾኑን ከመሰከሩ እና የተብራሩ አንቀጾችም ከመጡላቸው በኋላ የካዱን ሕዝቦች አሏህ አያቀናም(ያጠማል)፦

ቁርኣን 3፥86 ከእምነታቸው፣ መልክተኛውም እውነት መኾኑን ከመሰከሩ እና የተብራሩ አንቀጾችም ከመጡላቸው በኋላ የካዱን ሕዝቦች አላህ እንዴት ያቀናል? አላህ በዳዮችንም ሕዝቦች አያቀናም፡፡
كَيْفَ يَهْدِي اللَّهُ قَوْمًا كَفَرُوا بَعْدَ إِيمَانِهِمْ وَشَهِدُوا أَنَّ الرَّسُولَ حَقٌّ وَجَاءَهُمُ الْبَيِّنَاتُ ۚ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ

እውነትን ዐውቀው እና የተብራሩ አንቀጾች ከመጡላቸው በኃላ ቢያስተባብሉ በደለኞች ናቸው፥ በደለኞች በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው፦

ቁርኣን 31፥11 በእውነቱ በዳዮቹ በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው፡፡
بَلِ الظَّالِمُونَ فِي ضَلَالٍ مُّبِينٍ

አሏህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ እና ኹኔታ እስከሚለውጡ ድረስ ማንንም አያጠምም፥ ከእውነት በተዘነበሉም ጊዜ ግን ልቦቻቸውን በማጥመም አዘነበላቸው፦

ቁርኣን 13፥11 አላህ በሕዝቦች ዘንድ ያለውን ጸጋ በራሳቸው ያለውን ኹኔታ እስከሚለውጡ ድረስ አይለውጥም፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يُغَيِّرُ مَا بِقَوْمٍ حَتَّىٰ يُغَيِّرُوا مَا بِأَنفُسِهِمْ
ቁርኣን 61፥5 ከእውነት በተዘነበሉም ጊዜ አላህ ልቦቻቸውን አዘነበላቸው፡፡ አላህም አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡
فَلَمَّا زَاغُوا أَزَاغَ اللَّهُ قُلُوبَهُمْ ۚ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ

አምላካችን አሏህ በቁርኣን ውስጥ ከምሳሌው ሁሉ ለሰዎች ገልጿል፥ እርሱ ትንሿን ትንኝን ኾነ ከበላይዋ ያለ ትልቅ ነገር ምሳሌ ለማድረግ አያፍርም፦

ቁርኣን 17፥89 በዚህም ቁርኣን ውስጥ ከምሳሌው ሁሉ ለሰዎች በእርግጥ መላለስን፡፡ አብዛኞቹም ሰዎች ክህደትን እንጂ ሌላን እምቢ አሉ፡፡
وَلَقَدْ صَرَّفْنَا لِلنَّاسِ فِي هَـٰذَا الْقُرْآنِ مِن كُلِّ مَثَلٍ فَأَبَىٰ أَكْثَرُ النَّاسِ إِلَّا كُفُورًا
ቁርኣን 2፥26 አላህ ማንኛውንም ነገር ትንኝን ኾነ ከበላይዋ የኾነንም ምሳሌ ለማድረግ አያፍርም፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يَسْتَحْيِي أَن يَضْرِبَ مَثَلًا مَّا بَعُوضَةً فَمَا فَوْقَهَا

እነዚያ ያመኑት ቁርኣን ከጌታቸው የመጣ እውነት መኾኑን ያውቃሉ፥ እነዚያም የካዱትማ «አላህ በዚህ ምንን ምሳሌ ሽቷል» ይላሉ፡፡ በቁርኣን ብዙዎችን ያጠማል፥ በቁርኣን ብዙዎችን ያቀናል፡፡ በእርሱም አመፀኞችን እንጅ ሌላን አያጠምም፦

ቁርኣን 2፥26 እነዚያ ያመኑትማ እርሱ ከጌታቸው የመጣ እውነት መኾኑን ያውቃሉ፡፡ እነዚያም የካዱትማ «አላህ በዚህ ምንን ምሳሌ ሽቷል» ይላሉ፡፡ በእርሱ ብዙዎችን ያጠማል፥ በእርሱም ብዙዎችን ያቀናል፡፡ በእርሱም አመፀኞችን እንጅ ሌላን አያጠምም፡፡
فَأَمَّا الَّذِينَ آمَنُوا فَيَعْلَمُونَ أَنَّهُ الْحَقُّ مِن رَّبِّهِمْ ۖ وَأَمَّا الَّذِينَ كَفَرُوا فَيَقُولُونَ مَاذَا أَرَادَ اللَّهُ بِهَـٰذَا مَثَلًا ۘ يُضِلُّ بِهِ كَثِيرًا وَيَهْدِي بِهِ كَثِيرًا ۚ وَمَا يُضِلُّ بِهِ إِلَّا الْفَاسِقِينَ

ቀጣዩ አንቀጽ "አመጸኞች" የሚለውን ቃል ለማመልከት "እነዚያ" የሚል አመልካች ተውላጠ ስም በመጠቀም እነዚያ አመጸኞች የአሏህን ቃል ኪዳን ከአጠበቀባቸው በኋላ የሚያፈርሱ፣ እንዲቀጠል በእርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቆርጡ እና በምድርም ላይ የሚያበላሹ እንደሆኑ ይናገራል፥ እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፦

ቁርኣን 2፥27"እነዚያ" የአላህን ቃል ኪዳን ከአጠበቀባቸው በኋላ የሚያፈርሱ፣ እንዲቀጠል በእርሱ ያዘዘውን ነገር የሚቆርጡ እና በምድርም ላይ የሚያበላሹ ናቸው። እነዚያ እነርሱ ከሳሪዎቹ ናቸው፡፡
الَّذِينَ يَنقُضُونَ عَهْدَ اللَّهِ مِن بَعْدِ مِيثَاقِهِ وَيَقْطَعُونَ مَا أَمَرَ اللَّهُ بِهِ أَن يُوصَلَ وَيُفْسِدُونَ فِي الْأَرْضِ ۚ أُولَـٰئِكَ هُمُ الْخَاسِرُونَ

አሏህ በቁርኣን ውስጥ ከገለጸው ምሳሌ የእነዚያም የካዱት ምሳሌ እንደዚያ ድምጽን እና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ እንስሳ ላይ እንደሚጮህ ብጤ ነው፦

ቁርኣን 2፥171 የእነዚያም የካዱት ምሳሌ እንደዚያ ድምጽን እና ጥሪን በስተቀር ሌላን በማይሰማ እንስሳ ላይ እንደሚጮህ ብጤ ነው፡፡ እነርሱም ደንቆሮዎች፣ ዲዳዎች፣ ዕውሮች ናቸው፤ ስለዚህ እነርሱ አያውቁም፡፡
وَمَثَلُ الَّذِينَ كَفَرُوا كَمَثَلِ الَّذِي يَنْعِقُ بِمَا لَا يَسْمَعُ إِلَّا دُعَاءً وَنِدَاءً ۚ صُمٌّ بُكْمٌ عُمْيٌ فَهُمْ لَا يَعْقِلُونَ

ከእነዚያ እውነትን እያወቁ ከካዱት በተቃራኒው እውነትን ለማወቅ በአሏህ መንገድ እየታገሉ የሚፍጨረጨሩትን አሏህ የልባቸውን እሾት ስለሚያውቅ ሂዳያህ ይወፍቃቸዋል፥ "የትኛው ሰው በልቡ ቅን ነው" የሚለውን አሏህ ዐዋቂ ነው፦

ቁርኣን 29፥69 እነዚያም በእኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፡፡
وَالَّذِينَ جَاهَدُوا فِينَا لَنَهْدِيَنَّهُمْ سُبُلَنَا
ቁርኣን 28፥56 አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ አታቀናም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል፥ እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው፡፡
إِنَّكَ لَا تَهْدِي مَنْ أَحْبَبْتَ وَلَـٰكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَن يَشَاءُ ۚ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ
ቁርኣን 68፥7 ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የጠመመውን ሰው ዐዋቂ ነው፡፡ እርሱም ተመሪዎቹን ዐዋቂ ነው፡፡
إِنَّ رَبَّكَ هُوَ أَعْلَمُ بِمَن ضَلَّ عَن سَبِيلِهِ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ

"ሙህተድ" مُهْتَد ማለት "ተመሪ" "ቅን" ማለት ነው። አሏህ ሙህተዲንን ዐዋቂ ነው። እኛ ግን ሂዳያህ ሰጪም ነሺም አይደለንም፥ ማን ሂዳያህ እንደሚገባው ያውቃል። አምላካችን አሏህ አሸናፊ እና ጥበበኛ ስለሆነ የሚሻውን በቁርኣን ያጠማል፥ የሚሻውን በቁርኣን ያቀናል፦

ቁርኣን 14፥4 አላህም የሚሻውን ያጠማል፥ የሚሻውንም ያቀናል፡፡ እርሱም አሸናፊው ጥበበኛው ነው፡፡
فَيُضِلُّ اللَّهُ مَن يَشَاءُ وَيَهْدِي مَن يَشَاءُ ۚ وَهُوَ الْعَزِيزُ الْحَكِيمُ

"አላህም የሚሻውን ያጠማል፥ የሚሻውንም ያቀናል" የሚለው ኃይለ-ቃል "ዓም" ሆኖ የመጣ ነው፥ "ዓም" عَامّ ማለት "ጥቅል"general" ማለት ነው። ለምሳሌ፦ "ለሚሻውም ሰው ይምራል፥ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል" የሚለው ኃይለ-ቃል "ዓም" ሆኖ የመጣ ነው፦

ቁርኣን 2፥284 ለሚሻውም ሰው ይምራል፥ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡
فَيَغْفِرُ لِمَن يَشَاءُ وَيُعَذِّبُ مَن يَشَاءُ ۗ وَاللَّهُ عَلَىٰ كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ

ነገር ግን "ለሚሻውም ሰው ይምራል፥ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል" የሚለው ዓም በሌሎች አናቅጽ "ኻስ" ሆኖ ይመጣል፥ "ኻስ" خَاصّ ማለት "ተናጥል"specifical" ማለት ነው። ምሕረት እና ቅጣት በማመን እና በመካድ እንደሆነ "ኻስ" ሆኖ መጥቷል፦

ቁርኣን 5፥9 እነዚያንም ያመኑትንና በጎ ሥራዎችን የሠሩትን አላህ (ገነትን) ተስፋ አደረገላቸው፡፡ ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡
وَعَدَ اللَّهُ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ ۙ لَهُم مَّغْفِرَةٌ وَأَجْرٌ عَظِيمٌ
ቁርኣን 67፥6 ለእነዚያም በጌታቸው ለካዱት የገሀነም ቅጣት አልላቸው፡፡ መመለሻይቱም ከፋች!
وَلِلَّذِينَ كَفَرُوا بِرَبِّهِمْ عَذَابُ جَهَنَّمَ ۖ وَبِئْسَ الْمَصِيرُ
ቁርኣን 4፥147 ብታመሰግኑ እና ብታምኑ አላህ እናንተን በመቅጣት ምን ያደርጋል? አላህም ወሮታን መላሽ ዐዋቂ ነው፡፡
مَّا يَفْعَلُ اللَّهُ بِعَذَابِكُمْ إِن شَكَرْتُمْ وَآمَنتُمْ ۚ وَكَانَ اللَّهُ شَاكِرًا عَلِيمًا
ቁርኣን 4፥48 አላህ በእርሱ ማጋራትን በፍጹም አይምርም፡፡ ከዚህ ሌላ ያለውንም ኀጢአት ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يَغْفِرُ أَن يُشْرَكَ بِهِ وَيَغْفِرُ مَا دُونَ ذَٰلِكَ لِمَن يَشَاءُ ۚ

እንግዲያውስ አሏህ የሚሻውን በማመኑ እንደሚምር እና የሚሻውን በመካዱ የሚቀጣ ከሆነ በተመሳሳይም የሚሻውን በማመኑ ያቀናዋል፥ የሚሻውን በመካዱ ያጠመዋል። ምሪት እና ጥመት በማመን እና በመካድ እንደሆነ "ኻስ" ሆኖ መጥቷል፦
22፥54 አላህም እነዚያን ያመኑትን ወደ ቀጥተኛው መንገድ በእርግጥ "መሪ" ነው፡፡
وَإِنَّ اللَّهَ لَهَادِ الَّذِينَ آمَنُوا إِلَىٰ صِرَاطٍ مُّسْتَقِيمٍ

ቁርኣን 13፥27 «አላህ የሚሻውን ያጠምማል፥ የተመለሰውንም ሰው ወደ እርሱ ይመራል» በላቸው፡፡
قُلْ إِنَّ اللَّهَ يُضِلُّ مَن يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ أَنَابَ
ቁርኣን 3፥86 አላህ በዳዮችንም ሕዝቦች አያቀናም፡፡ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الظَّالِمِينَ
31፥11 በእውነቱ በዳዮቹ በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው፡፡
بَلِ الظَّالِمُونَ فِي ضَلَالٍ مُّبِينٍ

ስለዚህ "የሚሻው" የሚለው ቃል በጥቅሉ ሠበብ እና መሥቡብ ሁሉ በአሏህ መሺኣህ ሥር መሆኑን አመላካች ነው፥ ጥመት እና ቅጣት ዐድል ሆነው መምጣታቸው እንዲሁ ምሪት እና ምሕረት ፈድል ሆነው መምጣታቸው በራሱ ከሑጃህ በኃላ ያሉ ወሮታ እና አጸፌታ፣ ምንዳ እና ትሩፋት፣ ስርጉት እና ትርሲት መሆናቸውን ቁልጭ እና ፍንትው አርጎ ያሳያል፦

ቁርኣን 2፥175 እነዚያ ጥመትን በቅንነት ቅጣትንም በምሕረት የገዙ ናቸው፡፡ በእሳት ላይም ምን ታጋሽ አደረጋቸው?
أُولَـٰئِكَ الَّذِينَ اشْتَرَوُا الضَّلَالَةَ بِالْهُدَىٰ وَالْعَذَابَ بِالْمَغْفِرَةِ ۚ فَمَا أَصْبَرَهُمْ عَلَى النَّارِ

"እነዚያ" የሚለው አመልካች ተውላጠ ስም የሚያመለክተው እውነትን ያስተባበሉ ከሓድያን ሲሆን እነርሱም ጥመትን በቅንነት ቅጣትንም በምሕረት የገዙ ናቸው። አሏህ ፍትኸኛ፣ ጥበበኛ እና ዐዋቂ እንጂ እንደ ፍጡራን በዘፈቀደ የሚፈርድ አይደለም፥ ልብን የሚያውቅ፣ የሚቆጣጠር እና የሚመረምር አምላክ ፍርደ ገምድል በፍጹም አይደለም። አሏህ ቅንጣት ታክል ማንንም አይበድልም፥ ነገር ግን ሰው እራሱን የሚበድነው ማመን እና መታዘዝ ሲችል በመካድ እና በማመጽ ነው፦

ቁርኣን 18፥49 ጌታህም አንድንም አይበድልም፡፡
وَلَا يَظْلِمُ رَبُّكَ أَحَدًا
ቁርኣን 4፥40 አላህ የብናኝን ክብደት ያህል አይበድልም፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ مِثْقَالَ ذَرَّةٍ
ቁርኣን 10፥44 አላህ ሰዎችን ምንም አይበድልም፡፡ ግን ሰዎች እራሳቸውን ይበድላሉ፡፡
إِنَّ اللَّهَ لَا يَظْلِمُ النَّاسَ شَيْئًا وَلَـٰكِنَّ النَّاسَ أَنفُسَهُمْ يَظْلِمُونَ

አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይወፍቀን! ከደላላህ ቅጣት ይጠብቀን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም