በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 5፥111 ወደ ሐዋርያትም «በእኔ እና በመልእክተኛዬ እመኑ» በማለት ባዘዝኩ ጊዜ አስታውስ፡፡
وَإِذْ أَوْحَيْتُ إِلَى الْحَوَارِيِّينَ أَنْ آمِنُوا بِي وَبِرَسُولِي

"ሐዋርይ" حَوَارِيّ የሚለው ቃል "ሓረ" حَارَ ማለት "ተጓዘ" "ሄደ" "ተላከ" "ሖረ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ተጓዥ" "ሂያጅ" "ተላላኪ" "ሐዋርያ" ማለት ነው፥ የሐዋርይ ብዙ ቁጥር ደግሞ "ሐዋሪዪን" حَوَارِيِّين ወይም "ሐዋርዩን" حَوَارِيُّون‎ ሲሆን "ተጓዦች" "ሂያጆች" "ተላላኪዎች" "ሐዋርያት" ማለት ነው፦

ቁርኣን 5፥111 ወደ ሐዋርያትም «በእኔ እና በመልእክተኛዬ እመኑ» በማለት ባዘዝኩ ጊዜ አስታውስ፡፡
وَإِذْ أَوْحَيْتُ إِلَى الْحَوَارِيِّينَ أَنْ آمِنُوا بِي وَبِرَسُولِي

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሐዋርያት" ለሚለው የገባው ቃል "ሐዋርዪን" حَوَارِيِّين ሲሆን የዒሣ ሐዋርያትን ያመለክታል፥ "ባዘዝኩ" ለሚለው የገባው ቃል "አውሐይት" أَوْحَيْتُ የግሥ መደብ ሲሆን የስም መደቡ "ወሕይ" وَحْي ማለትም "ግልጠተ መለኮት"revelation" ነው። ሐዋርያት ለዒሣ የዓይን እና የጆሮ እማኞች ሲሆኑ አሏህ ለዒሣ በሰጠው ወሕይ በኢንጂል ለሐዋርያት፦ "በእኔ እና በመልእክተኛዬ እመኑ" ብሎ ሲያዛቸው እነርሱም፦ «አመንን፥ እኛ ሙሥሊሞች መኾናችንን መስክር» አሉ፦

ቁርኣን 5፥111 «አመንን፥ እኛ ሙሥሊሞች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡
قَالُوا آمَنَّا وَاشْهَدْ بِأَنَّنَا مُسْلِمُونَ

"ኢሥላም" إِسْلَام‎ የሚለው ቃል "አሥለመ" أَسْلَمَ ማለትም "ታዘዘ" "ተገዛ" "አመለከ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን አንዱን አምላክ በብቸኝነት "መታዘዝ" "መገዛት" "ማምለክ" ማለት ነው፥ አንዱን አምላክ በብቸኝነት ታዛዥ፣ ተገዢ፣ አምላኪ ደግሞ በነጠላ "ሙሥሊም" مُسْلِم በብዜት "ሙሥሊሚን" مُسْلِمِين ወይም "ሙሥሊሙን" مُسْلِمُون ይባላል። ሐዋርያት አንዱን አምላክ የሚያማልኩ ሙሥሊሞች እንደሆኑ አስመስክረዋል፥ በቁርኣን የሐዋርያት ስም እና የቁጥራቸው መጠን አልተገለጸም።

ወደ ባይብል ስንመጣ የሐዋርያት ስም ዝርዝር የተዘረዘረ ሲሆን የቁጥራቸው መጠን አሥራ ሁለት ነው፦

ሉቃስ 6፥13 በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም "ሐዋርያት" ብሎ ሰየማቸው።
καὶ ὅτε ἐγένετο ἡμέρα, προσεφώνησεν τοὺς μαθητὰς αὐτοῦ, καὶ ἐκλεξάμενος ἀπ’ αὐτῶν δώδεκα, οὓς καὶ ἀποστόλους ὠνόμασεν,

"አፓስቶሎስ" ἀπόστολος ማለት "ሐዋርያ" ማለት ነው፥ "አፓስቶሉስ" ἀποστόλους ደግሞ የአፓስትሎስ ብዙ ቁጥር ሲሆን "ሐዋርያት" ማለት ነው፥ ሐዋርያት የቁጥራቸው መጠን አሥራ ሁለት ሆነው ሳለ ኢየሱስ በተልኮ ጊዜ አብሮት ያልነበረው ጳውሎስ መጥቶ "የክርስቶስ ሐዋርያት ነን" ብሎ አረፈው፦

1ኛ ተሰሎንቄ 2፥6 የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።
οὔτε ζητοῦντες ἐξ ἀνθρώπων δόξαν, οὔτε ἀφ’ ὑμῶν οὔτε ἀπ’ ἄλλων,

ይህ አካሄዱ ትክክል ስላልሆነ ኢየሱስ በራእይ ዮሐንስ ላይ ሐዋርያት ሳይሆኑ "ሐዋርያት ነን" የሚሉቱን ሐሰተኞች እንደሆኑ ተናግሯል፦

ራእይ 2፥2 እንዲሁም ሳይሆኑ፦ "ሐዋርያት ነን" የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ።

በዕብራውያን ባህል የአንድ ሰው ስም ካልተጠቀሰ በብዜት የመናገር ልማድ አለው፥ ለምሳሌ፦ ሄሮድስ ሲሞት "የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋል" ተብሏል፦

ማቴዎስ 2፥20 የሕፃኑን ነፍስ "የፈለጉት" "ሞተዋል"።

የሕፃኑን ነፍስ ለመግደል የፈለገው እና የሞተው ሄሮድስ ሆኖ ሳለ "የፈለጉት" "ሞተዋል" በሚል ብዜት መጠቀሙ ስም አለመጠቀሱ ካመለከተ የጳውሎስ ስም ስላልተጠቀሰ "ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው" በሚል ተጠቅሷል። ኢየሱስ ከሾማቸው አሥራ ሁለት ሐዋርያት ውጪ "ኢየሱስ ተገለጠልኝ" ብሎ "የክርስቶስ ሐዋርያት ነን" ብሎ የተናገረ ከጳውሎስ ውጪ ማንም የለም፣ ኢየሱስ ጳውሎስን "ሐዋርያ" ያለበት የለም፣ ጳውሎስ "ተገለጠልኝ" ሲል "ተገለጠለት" ብሎ ለቴዎፍሎስ ደብዳቤ የጻፈለት ሉቃስ የጳውሎስ ተማሪ ሲሆን ከጳውሎስ ሰምቶ እንጂ በቦታው በዓይኑ ያየው እና በጆሮ የሰማው አይደለም። ለጳውሎስ ይህንን መልእክት የሰጠው እራሱ ሰይጣን እንደሆነ ተናግሯል፦

2ኛ ቆሮንቶስ 12፥7 ስለዚህም "በ-"መገለጥ" ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ "የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ"።
καὶ τῇ ὑπερβολῇ τῶν ἀποκαλύψεων. διὸ ἵνα μὴ ὑπεραίρωμαι, ἐδόθη μοι σκόλοψ τῇ σαρκί, ἄγγελος Σατανᾶ, ἵνα με κολαφίζῃ,

"መልእክተኛ" የሚለው ቃል "አንገሎስ" ወይም "አገሎስ" ἄγγελος ሲሆን "መልአክ" ማለት ነው፥ ግዕዙ፦ "መልአከ ሰይጣን" ማለትም "የሰይጣን መልአክ" ይለዋል። "መገለጥ" ለሚለው የገባው ቃል ደግሞ "አፓልካሊፕሶን" ἀποκαλύψεων ሲሆን ይህንን አፓልካሊፕስ የሰጠው ሰይጣን በመልአኩ እንጂ ከጌታ አይደለም፦

1ኛ ቆሮ 7፥12 ሌሎችንም እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም።
2ኛ ቆሮ 11፥17 እንደዚህ ታምኜ ስመካ “የምናገረው በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም”።

"እኔ እላለሁ፥ ጌታም አይደለም" ካለ የራሱ ደብዳቤ እንጂ ከጌታ ያገኘው ቃል አይደለም፥ "የምናገረው በሞኝነት እንጂ ጌታ እንዳዘዘኝ አልናገርም" ካለ መገለጥ የሚለው ከሰይጣን መልአክ የመጣለት መልእክት ነው። ስለዚህ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ለእኛ ለሙሥሊም ለንጽጽር መረጃ ይሆን ይሆናል እንጂ ማስረጃ መሆን አይችልም፥ ክርስቲያኖች፦ "ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ አለ" የምትሉት ባለማወቅ ነውና ይህንን ስታውቁ ንስሓ ወደ አሏህ ገብታችሁ ወደ ኢሥላም እንድትመጡ ጥሪአችን ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም