በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 59፥7 መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡
وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ

“ሐዲስ” حَدِيث የሚለው ቃል “ሐደሰ” حَدَّثَ‎ ማለትም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ንግግር” ማለት ነው፥ ነቢያችን”ﷺ” በዐቂዳህ እና በፊቅህ ነጥብ ላይ የሚናገሩት ሐዲስ ሁሉ ወሕይ ነው፦

ቁርኣን 53፥3 ከልብ ወለድም አይናገርም፡፡
وَمَا يَنطِقُ عَنِ الْهَوَىٰ
ቁርኣን 53፥4 እርሱ ንግግሩ የሚወረድ ወሕይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْيٌ يُوحَىٰ

“ወሕይ” وَحْي የሚለው ቃል “አውሓ” أَوْحَىٰٓ ማለትም “ገለጠ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ግልጠተ-መለኮት” ማለት ነው። “መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ” የሚለው ይህንኑ ሡናህ ዋቢና ታሳቢ ያደረገ ነው፦

ቁርኣን 59፥7 መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡
وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ

ታዲያ ቁርኣን እና ሐዲስ ልዩነቱ ምንድን ነው? አዎ! ቁርኣን ለፍዙ ሆነ መዕናው የአላህ ነው፥ ሐዲስ ግን ለፍዙ የነቢያችን”ﷺ” ሲሆን ማዕናው የአላህ ነው። “ለፍዝ” لَفْظ ማለት “ቃል”Verbatim” ማለት ሲሆን “መዕና” مَعْنًى ማለት “መልእክት” “እሳቤ” “አሳብ”notion” ማለት ነው። የቁርኣን ተናጋሪ አላህ ብቻ ነው፥ ቃሉም የወከለው መልእክቱ፣ “እሳቤው፣ አሳቡ የራሱ ነው። ሐዲስ ደግሞ መልእክቱ፣ “እሳቤው፣ አሳቡ የአላህ ሲሆን ቃሉ ግን የራሳቸው የነቢያችን”ﷺ” ነው። አላህ የሐዲስን መልእክት ሲያወርድላቸው እሳቸው በራሳቸው ባህል፣ ወግ፣ ልምድ፣ ክህሎት፣ ትውፊት ያብራሩታል። ይህ ሐዲስ ደግሞ በሁለት ይከፈላል፥ እርሱም ሐዲሱ አን-ነበዊይ እና ሐዲሱል ቁድሢይ ነው።

ነጥብ አንድ
"ሐዲሱ አን-ነበዊይ"

“ነቢይ” نَبِيّ የሚለው ቃል “ነበአ” نَبَّأَ ማለትም “የሩቅ ወሬን አወራ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “የሩቅ ወሬ አውሪ” ማለት ነው፥ የነቢይ ገላጭ መደብ ደግሞ "ነበዊይ" نَبَوِيّ‎ ሲሆን "ነቢያዊ" ማለት ነው። በጥቅሉ "ሐዲሱ አን-ነበዊይ" حَدِيث الْنَبَوِيّ‎ ማለት "ነቢያዊ ሐዲስ" ማለት ነው፥ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ" ወይም "ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ" ተብሎ የሚናገሩት ንግግር ሁሉ ሐዲሱ አን-ነበዊይ ይባላል። ለምሳሌ፦

ጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 27, ሐዲስ 62
አቢ ዘር እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ ”የአንተ ፈገግታ በወንድምህ ፊት ለአንተ ሶደቃህ ነው”
عَنْ أَبِي ذَرٍّ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ تَبَسُّمُكَ فِي وَجْهِ أَخِيكَ لَكَ صَدَقَةٌ
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 80, ሐዲስ 102
አቢ ሙሣ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ ”ጌታውን የሚዘክር እና የማይዘክር ምሳሌ፥ ልክ እንደ ሕያው እና እንደ ሙታን ነው”
عَنْ أَبِي مُوسَى ـ رضى الله عنه ـ قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ‏ “‏ مَثَلُ الَّذِي يَذْكُرُ رَبَّهُ وَالَّذِي لاَ يَذْكُرُ مَثَلُ الْحَىِّ وَالْمَيِّتِ

ነጥብ ሁለይ
"ሐዲሱል ቁድሢይ"

"ቁድሥ" قُدْس የሚለው ቃል "ቀዱሠ" قَدُسَ ማለትም "ቀደሰ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ቅዱስ" ማለት ነው፥ የቁድሥ ገላጭ መደብ ደግሞ "ቁድሢይ" قُدْسِيّ ሲሆን "ቅዱሳዊ" ማለት ነው። በጥቅሉ "ሐዲሱል ቁድሢይ" حَدِيث الْقُدْسِيّ ማለት "ቅዱሳዊ ንግግር" ማለት ነው፥ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "አላህም እንዲህ አለ" ተብሎ የሚናገሩት ንግግር ሁሉ ሐዲሱል ቁድሢይ ይባላል። ለምሳሌ፦

ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 13, ሐዲስ 212
አቢ ሁረይራ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "አላህም እንዲህ አለ፦ “ከፆም በስተቀር የአደም ልጅ መልካም ሥራ ሁሉ ለራሱ ነው፥ ፆም ለእኔ ነው። እኔም ምንዳውን በእርሱ እከፍላለው"
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ ـ رضى الله عنه ـ يَقُولُ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم ‏ "‏ قَالَ اللَّهُ عَزَّ وَجَلَّ كُلُّ عَمَلِ ابْنِ آدَمَ لَهُ إِلاَّ الصِّيَامَ فَإِنَّهُ لِي وَأَنَا أَجْزِي بِهِ

ነቢያችን"ﷺ" ይህንን ወደ አሏህ አስጠግተው የሚነግሩን ቅዱሳዊ ንግግራቸው ከቁርኣን የሚለየው፦
1ኛ. ቁርኣን የአሏህ ንግግር ብቻ ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን በነቢያችን"ﷺ" ንግግር "አሏህ አለ" ተብሎ በኒስባህ መነገሩ ነው።
2ኛ. ቁርኣን አሏህ በጂብሪል በኩል የተናገረው የራሱ ንግግር ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን በነቢያችን"ﷺ" ሕልም "አሏህ አለ" ተብሎ በኒስባህ መነገሩ ነው።
3ኛ. ቁርኣን ሲቀራ ዒባዳህ የሚፈጸምበት ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን አይቀራም፥ በመነበቡ ዒባዳም አይፈጸምበትም።
4ኛ. ቁርኣን እያንዳንዱ ሐርፍ መቅራት አስር ሐሠናት ሲኖረው ሐዲሱል ቁድሢይ ግን በውስጡ ያሉትን በመታዘዝ እንጂ በመነበቡ ሐሠናት የለውም።
5ኛ. ቁርኣን በሡራህ፣ በአያት እና በጁዝ የተከፋፈለ ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን በምንም አልተከፋፈለም።
6ኛ. ቁርኣን በውዱእ መንካት ሙስተሐብ እና ያለ ውዱእ መንካት መክሩህ ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን ያለ ውዱእ መንካት ሙባሕ ነው።
7ኛ. ከተራክቦ በኃላ ቁርኣን ለመንካት የጀናባህ ትጥበት ፈርድ ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን ያለ ጀናባህ ትጥበት መንካት ሙባሕ ነው።
8ኛ. በሐይድ ይ ያለች እንስት ቁርኣንን መንካት ክልክል ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይን ግን መንካት ሙባሕ ነው።
9ኛ. ቁርኣን ለነቢያችን"ﷺ" ነቢይነት ታምር ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን ለነቢያችን"ﷺ" ነቢይነት ታምር አይደለም።
10ኛ. ቁርኣን ከፊቱ እና ከኃላው ውሸት እንይመጣበት አሏህ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠብቀው ቃል የገባለት የራሱ ንግግር እና በሙተዋቲር የመጣ ሲሆን ሐዲሱል ቁድሢይ ግን ሐዲስ ውስጥ ስለሚካተት መቅቡል እና መርዱድ አሉት። "መቅቡል" مَقْبُول ማለት "ቅቡል" ማለት ሲሆን ተቀባይነት ያላቸው የሚባሉት ሶሒሕ እና ሐሰን የሆኑ ናቸው። "መርዱድ" مَردُود "ውድቅ" ማለት ሲሆን ውድቅ ሐዲስ የሚባሉት ዶዒይፍ እና መውዱዕ የሆኑ ናቸው።

ዋቢ መጽሐፍ የሼይኽ ዶክተር ያሲር ቋዲ መጽሐፍ ይመልከቱ፦
Abu Ammaar Yasir Qadhi 1999. Introduction to the Sciences of the Qura̓an. Page 72-74

“አሏሁ አዕለም” اَللّٰهُ أَعْلَم‎

✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም