በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

ቁርኣን 29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ "እኔን ብቻ አምልኩኝ"፡፡
يَٰعِبَادِىَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ إِنَّ أَرْضِى وَٰسِعَةٌۭ فَإِيَّٰىَ فَٱعْبُدُونِ

የኦርቶዶክስ መምህራን ከእነጀሌዎቻቸው እሥልምናን በዐውደ ምሕረት ላይ ሲያበሻቅጡ፣ ሲያብጠለጥሉ፣ ሲያነውሩ እኛ ሙሥሊሞች አጸፌታ ብንመልስ "አገር፣ ጎረቤት፣ ባልንጀርነት፣ ቤተሰብ ይፈርሳል" በማለት ስሜታችንን ገታ አርገን ከአሏህ አጅር ማግኘቱን መርጠን ነበር፥ ባይሆን የተተቸውን አሳብ ብቻ ረብጣ በሆነ አሳብ ለማረቅ ሞክረናል እንጂ ገጀራ አላነሳንም። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በማሕበራዊ ሚድያ ላይ እንደፈለጉ እሥልምናን ሲሳደቡ ሲኖዶስ ሆነ መንግሥት "ተዉ" ብለው አያውቁም፥ ዛሬ ፓስተር ዮናታን አክሊሉ ለኃየሰው ኂስ ምድሪቱ ሸብረብ እስክትል ድረስ ያዙኝ ልቀቁኝ እና አሸሼ ገዳዬ ሲሉ ገርሞናል።

ፓስተር ዮናታን አክሊሉ በራሱ መድረክ ላይ ስሜታዊ ሆኖ ተአምረ ማርያም መቅድም ላይ ያሉትን አናቅጽ እየተነተነ ከሞገተ በኃላ፦ "አንዱ ኢትዮጵያን ጨለማ ውስጥ እና ድንቁርና ውስጥ ወደ ኃላ ኃላቀርነት ውስጥ የከተተው በፈጣሪ ፋንታ ፍጡርን ለማምለክ የሚደረግ ጣዖት አምላኪነት ነው" በማለት ፓለቲካ ይዘት ያለው መልእክት አስተላልፏል፥ ይህ ንግግሩ "የሰው ስሜት የጠበቀ ነው" ብዬ አላምንም።
ነገር ግን ፓስተር ዮናታን አክሊሉ ከመጽሐፉ ጠቅሶ እና አጣቅሶ ፦ "በስዕሏ ፊት ስገዱ! ለሥዕሏ ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ! ስም አጠራሩ አይታወቅ" ይህ ጣዖት አምላኪነት ነው" በማለት ተናግራል፦

ተአምረ ማርያም የዘወትር መቅድም ቁጥር 35-36 ገጽ 7
"በስዕሏ ፊት ስገዱ! ለሥዕሏ ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ! ስም አጠራሩ አይታወቅ። በሰማይ ያሉ መላእክትም ይደረግ ይሁን ይበሉ።

ለማርያም መስገድ እና ለስዕሏ መስገድ ሁለት ለየቅል ነገር ነው፥ ስዕል እኮ የማይሰማ የማይለማ የማይናገር የማይጋገር ግዑዝ ነገር ነው። ለዚህ ግዑዝ ነገር መስገድ በምን አግባብ ነው ትክክል የሚሆነው? የኦርቶዶክስ መምህራን እስካሁን ድረስ "በስዕሏ ፊት ስገዱ! ለሥዕሏ ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ" የሚለው ኃይለ-ቃል ባይብላዊ መሠረት አርገው መልስ ሲሰጡት በፍጹም አይታይም። ስለዚህ ስዕል የተቀረጸ ምስል እስከሆነ ድረስ ጣዖት አምልኮ ነው፥ "ኤዴሎን" εἴδωλον ማለት "ምስል" ማለት ሲሆን "ላትሬኦ" λατρεία ደግሞ "አምልኮ" ማለት ነው፦

1 ቆሮንቶስ 10፥14 ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! "ጣዖትን ከማምለክ" ሽሹ። Διόπερ, ἀγαπητοί μου, φεύγετε ἀπὸ τῆς εἰδωλολατρείας.

እዚህ አንቀጽ ላይ "ጣዖት ማምለክ" ለሚለው የገባው ቃል "ኤዶሎላትሬኦ" εἰδωλολατρεία ሲሆን "የተቀረጸ ምስል ማምለክ" ማለት ነው፦

ዘጸአት 20፥4 በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ "የተቀረጸውን ምስል" ለአንተ አታድርግ። οὐ ποιήσεις σεαυτῷ εἴδωλον, οὐδὲ παντὸς ὁμοίωμα, ὅσα ἐν τῷ οὐρανῷ ἄνω καὶ ὅσα ἐν τῇ γῇ κάτω καὶ ὅσα ἐν τοῖς ὕδασιν ὑποκάτω τῆς γῆς.

እዚህ አንቀጽ ላይ "የተቀረጸውን ምስል" ለሚለው የገባው ቃል "ኤዴሎን" εἴδωλον ሲሆን በላይ በሰማይ ካለው ለመልአክ ወይም በታች በምድር ካለው ለሰው ምስል መስገድ ወይም ማምለክ የተከለከለ ነው፦

ዘጸአት 20፥5 አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም። οὐ προσκυνήσεις αὐτοῖς, οὐδὲ μὴ λατρεύσεις αὐτοῖς·

"ፕሩስኩኔኦ" προσκυνέω ማለት "ስግደት" ማለት ሲሆን "ላትሬኦ" λατρεία ማለት ደግሞ "አምልኮ" ማለት ነው፥ ለተቀረጸ ምስል መስገድ ሆነ ማምለክ ክልክል እንደሆነ በአጽንሮት እና በአንክሮት ተቀምጧል።

በመቀጠል ፓስተሩ፦ "በፈጣሪ ፋንታ የተፈጠረውን ማምለክ ጣዖት አምላኪነት ነው" ብሏል፥ ይህ ሁሉም የሚስማማበት ነጥብ ነው። በዚህ መርሕ እነ ዮናታንም ከጣዖት አምላኪነት የማያመልጡበት ምክንያት የኢየሱስ ፈጣሪ በብቸኝነት ከማምለክ ይልቅ የተፈጠረውን ኢየሱስን እያመለኩ ነው።

ኦርቶዶክሳውያን፦ "እኛ ማርያምን እናከብራታለን እንጂ አናመልካትም" በማለት ፓስተሩን ከሰውታል፥ ምክንያቱም ሰዎች የማይሉትን እና የማያምኑትን እንደሚሉ እና እንደሚያምኑ አርጎ መሞገት ቁልመማዊ ሕፀፅ"strawman fallacy" ነው። ነገር ግን ፓስተሩ የማይሉትን እና የማያምኑትን እንደሚሉ እና እንደሚያምኑ አርጎ አልሞገተም፥ ምክንያቱም በኦርቶዶክስ ማርያም በግልጽ ትመለካለችና። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሐሙስ እንዚራ ስብሐት ላይ፦ "የአምልኮ መሥዋዕትንም ለአንቺ እሠዋለሁ" በማለት ያመልካታል፦

እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 12 ቁጥር 98 "ለአንቺም የምስጋና እጅ መንሻን አቀርባለሁ፣ በመፍራት እገዛልሻለሁ፣ በመስገድም እጅ እነሣሻለሁ። "የአምልኮ መሥዋዕትንም ለአንቺ እሠዋለሁ"።

የአምልኮ መሥዋዕት የሚቀርብለት አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ ለማርያም የአምልኮ መሥዋዕት ማቅረቡ ግልጽ ማሻረክ አይደለምን? "ዐማርኛ ትክክል አይደለም" እንዳንል ግዕዙ ላይ "ለኪ እሠውዕ መሥዋዕተ አምልኮ" ብሎ በግልጽ አስቀምጦታል፦

እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 4 ቁጥር 98
"እትቀነይ ለኪ በፍርሃት ወእኤምሐኪ በአስተብርኮ። ለኪ አቀርብ ቁርባነ አኮቴት ወ-"ለኪ እሠውዕ መሥዋዕተ አምልኮ"።

"ለኪ" ማለት "ለአንቺ" ማለት ነው፥ "ለ" የሚለው መስተዋድድ በማያፈናፍን መልኩ የሚጠጋው ወደ ማርያም ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በዓርብ እንዚራ ስብሐት ላይ ይቀጥልና፦ "የሚጣፍጥ የአምልኮ መሥዋዕትን ለአንቺ አቀርብልሻለሁ" በማለት ያመልካታል፦

እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 13 ቁጥር 113
"ማርያም ሆይ! ያማረ ፍጹም ምስጋና አቀርብልሻለሁ። የሚጣፍጥ የአምልኮ መሥዋዕትን ለአንቺ አቀርብልሻለሁ።

አምልኮ የአንድ አምላክ ገንዘብ እና ሐቅ ከሆነ ለማርያም የአምልኮ መሥዋዕት ማቅረቡ ግልጽ ማሻረክ ነው። "ዐማርኛ ትክክል አይደለም" እንዳንል ግዕዙ ላይ "አርብ ለኪ መሥዋዕተ አምልኮ ምዑዘ" ብሎ በግልጽ አስቀምጦታል፦
እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 4 ቁጥር 98
"አበውእ ለኪ ኦ እግዚእትየ ማርያም መዝሙረ ማኅሌት ሐዋዘ። ወአርብ ለኪ መሥዋዕተ አምልኮ ምዑዘ"።

"አርብ" ማለት "አቀርባለው" ማለት ነው፥ የአምልኮ መሥዋዕት ሊሰዋለት የሚገባው አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ ለማርያም መሠዋቱ በራሱ ዓይን ያስፈጠጠ እና ጥርስ ያስገጠጠ አምልኮ ነው።
በኢሥላም አስተምህሮት ሙሥሊሞች ለአምልኮ የምንጠቀምበት የተቀረጸ ምስል የለም፥ ከአሏህ ውጪ የምናመልከው እና የምንሰግድለት ምንነት ሆነ ማንነት የለም። አምላካችን አሏህ "ከእኔ ሌላ አምላክ የለምና አምልኩኝ" በማለቱ እኛ ሙሥሊሞች የአምልኮ ሐቅ ለእርሱ ብቻ እናቀርባለን፦

ቁርኣን 29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፤ ብትቸገሩ ተሰደዱ፡፡ "እኔን ብቻ አምልኩኝ"፡፡
يَٰعِبَادِىَ ٱلَّذِينَ ءَامَنُوٓا۟ إِنَّ أَرْضِى وَٰسِعَةٌۭ فَإِيَّٰىَ فَٱعْبُدُونِ
ቁርኣን 21፥92 ይህች አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፤ "እኔም ጌታችሁ ነኝና አምልኩኝ"፡፡
إِنَّ هَٰذِهِۦٓ أُمَّتُكُمْ أُمَّةًۭ وَٰحِدَةًۭ وَأَنَا۠ رَبُّكُمْ فَٱعْبُدُونِ

የአምልኮ ገንዘብ እና ሐቅ የሚገባው አሏህ "እኔ" ብሎ የሚናገር ነባቢ መለኮት ሲሆን ለተቀረጸ ምስል ከመስገድ እና ከማምለክ የፈጠረንን አንዱን አምላክ አሏህን በብቸኝነት እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም