በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
ቁርኣን 18፥50 ለመላእክትም ለአደም ስገዱ! ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ! ወዲያውም ሰገዱ፥ ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር ከጂን ነበር ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ"፡፡
وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ كَانَ مِنَ الْجِنِّ فَفَسَقَ عَنْ أَمْرِ رَبِّهِ
“ኢብሊሥ” إِبْلِيس የሚለው ቃል "በለሠ" بَلَسَ ማለትም "ተስፋ ቆረጠ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ተስፋ የቆረጠ" ማለት ነው፥ "ኢብሊሥ” إِبْلِيس የሚለው ቃል 11 ጊዜ በ 11 ቦታ ከጂን ለሆነ ፍጡር የተሰጠ የግብር ስም ነው፦
ቁርኣን 18፥50 ለመላእክትም ለአደም ስገዱ! ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ! ወዲያውም ሰገዱ፥ ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር ከጂን ነበር። ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ"፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ كَانَ مِنَ الْجِنِّ فَفَسَقَ عَنْ أَمْرِ رَبِّهِ
"ከጂን ነበር" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት "ጂኒ" جِنِّيّ የሚለው ቃል "ጀነ" جَنَّ ማለትም "ሰወረ" "ደበቀ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ስውር" "ድብቅ" ማለት ነው፥ "ጂን" جِنّ ደግሞ የጂኒ ብዙ ቁጥር ነው። ኢብሊሥ ጥንተ ተፈጥሮው ከጂን ነው፦
ኢማም ሙሥሊም መጽሐፍ 55, ሐዲስ 78
ዓኢሻህ”ረ.ዐ.” እንደተረከችው፦ የአሏህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "መላእክት ከብርሃን ተፈጥረዋል፣ ጃን ከእሳት ነበልባል ተፈጥሯል፣ አደም ለእናንተ እንደተገለጸላችሁ ከሚጭለቀለቅ ሸክላ ተፈጥሯል"፡፡ عَنْ عَائِشَةَ، قَالَتْ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم خُلِقَتِ الْمَلاَئِكَةُ مِنْ نُورٍ وَخُلِقَ الْجَانُّ مِنْ مَارِجٍ مِنْ نَارٍ وَخُلِقَ آدَمُ مِمَّا وُصِفَ لَكُمْ .
"ጃን" جَانّ ልክ እንደ "ሰው" ለጂኒዎች ጥቅላዊ ስም ነው፥ መላእክት እና ጃን "ወ" وَ ማለትም "እና" በሚል መስተጻምር መጠቀሙ በራሱ መላእክት እና ጂን ሁለት የተለያዩ ኑባሬዎች እንደሆኑ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። እዚህ ድረስ ከተግባባን "ኢብሊሥ መልአክ ነበር" ብለው ሚሽነሪዎች የሚሞግቱት በዚህ ጥቅስ ነው፦
ቁርኣን 17፥61 ለመላእክትም "ለአደም ስገዱ" ባልናቸው ጊዜ አስታውስ! ወዲያውም ሰገዱ፥ ኢብሊስ ብቻ ሲቀር፡፡ وَإِذْ قُلْنَا لِلْمَلَائِكَةِ اسْجُدُوا لِآدَمَ فَسَجَدُوا إِلَّا إِبْلِيسَ
፨ሲጀመር "ለ" የሚለው መስተዋድድ "መላእክት" በሚል መነሻ ቅጥያ ላይ መግባቱ አሏህ "ስገዱ" ያለው "ለመላእክት ብቻ" እንደሆነ ማስረጃ መሆን በፍጹም አይችልም። ይህንን በአንድ ተመሳሳይ ሙግት እንሞግት፦
ቁርኣን 7፥79 "ለ"-እነርሱም ልቦች አሏቸው፥ ግን አይገነዘቡበትም፣ "ለ"-እነርሱም ዓይኖች አሉዋቸው፥ ግን ዐያዩበትም፣ "ለ"-እነርሱም ጆሮዎች አሉዋቸው ግን አይሰሙበትም፡፡ لَهُمْ قُلُوبٌ لَّا يَفْقَهُونَ بِهَا وَلَهُمْ أَعْيُنٌ لَّا يُبْصِرُونَ بِهَا وَلَهُمْ آذَانٌ لَّا يَسْمَعُونَ بِهَا
ዐውዱ ላይ "እነርሱ" የተባሉት "ይልቁንም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፥ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው" የተባሉትን ነው፥ ቅሉ ግን "ለ" የሚለው መስተዋድድ "እነርሱ" በሚለው ቃል ላይ መነሻ ቅጥያ ሆኖ መምጣቱ ልቦች፣ ዓይኖች፣ ጆሮዎች አሉዋቸው የተባሉት ዘንጊዎቹ እና የተሳሳቱት ብቻ ናቸው እንደማንል ሁሉ አሏህ "ስገዱ" ያለው ለመላእክት ብቻ ሳይሆን ለኢብሊሥም ጭምር ነው፦
ቁርኣን 7፥12 አላህ፦ «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ» አለው፡፡قَالَ مَا مَنَعَكَ أَلَّا تَسْجُدَ إِذْ أَمَرْتُكَ
አሏህ ለኢብሊሥ ያለው "ባዘዝኳችሁ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ" ሳይሆን "ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ" ነው፥ "ባዘዝኩህ" የሚለው ኃይለ-ቃል አሏህ ለአደም "ስገድ" ብሎ አዞት እንደነበር ቁልጭና ፍንትው አድርጎ ያሳያል። "ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ" ማለቱ በራሱ እንዲሰግድ የታዘዙት መላእክት ብቻ አለመሆናቸውን ቁልጭ አርጎ ያሳያል፦
ቁርኣን 18፥50 ከጌታውም ትእዛዝ ወጣ፡፡ فَفَسَقَ عَنْ أَمْرِ رَبِّهِ
፨ሲቀጥል "ለመላእክትም ለአደም ስገዱ! ባልናቸው ጊዜ የሆነውን አስታውስ! ወዲያውም ሰገዱ፥ ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር" በሚል አንቀጽ ውስጥ "ሲቀር" "በቀር" ለሚለው የገባው ቃል "ኢላ" إِلَّا ሲሆን ኢሥቲስናእ ነው። "ኢሥቲስናእ" اِسْتِثْنَاء የሚለው ቃል "ኢሥተስና" اِسْتَثْنَى ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "በስተቀረት"exception" ማለት ነው፥ ኢሥቲስናእ በሁለት ይከፈላል። አንዱ "ኢሥቲስናኡል ሙተሲል" اِسْتِثْنَاء الْمُتَّصِل ሲሆን "ሙተሲል" مُتَّصِل ማለት "የተያያዘ"attached" ማለት ነው፦
ቁርኣን 43፥67 ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው፡፡ አላህን ፈሪዎች ብቻ "ሲቀሩ"፡፡ الْأَخِلَّاءُ يَوْمَئِذٍ بَعْضُهُمْ لِبَعْضٍ عَدُوٌّ إِلَّا الْمُتَّقِينَ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ኢላ" إِلَّا የሚለው ኢሥቲስናኡል ሙተሲል ስለሆነ ተመሳሳይ ጥንተ ተፈጥሮን ያሳያል፥ ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት የሚሆነው እና አሏህን ፈሪዎች ጥንተ ተፈጥሯቸው ተመሳሳይ ነው። ተጨማሪ ይህንን ጥቅስ መመልከት ይቻላል፦
ቁርኣን 103፥2 ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ውስጥ ነው፡፡ إِنَّ الْإِنسَانَ لَفِي خُسْرٍ
ቁርኣን 103፥3 እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ በእውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ "ሲቀሩ"፡፡ إِلَّا الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ وَتَوَاصَوْا بِالْحَقِّ وَتَوَاصَوْا بِالصَّبْرِ
ሁለተኛው ደግሞ "ኢሥቲስናኡል ሙንቀጢዕ" اِسْتِثْنَاء الْمُنقَطِع ሲሆን "ሙንቀጢዕ" مُنقَطِع ማለት "ያልተያያዘ"detached" ማለት ነው፦
ቁርኣን 26፥77 «እነርሱም ለእኔ ጠላቶች ናቸው፥ ግን የዓለማት ጌታ "ሲቀር"»፡፡ فَإِنَّهُمْ عَدُوٌّ لِّي إِلَّا رَبَّ الْعَالَمِينَ
ኢብራሂም "እነርሱም ለእኔ ጠላቶች ናቸው" ያላቸው እና "ሲቀር" ያለው "የዓለማት ጌታ" ሁለት የተለያዩ ኑባሬዎች እንደሆኑ ሁሉ በተመሳሳይ የሰዋስው አወቃቀር "መላእክት" እና "ኢብሊሥ" ሁለት የተለያዩ ኑባሬዎች ናቸው። በተጨማሪ አንድ ጥቅስ እንመልከት፦
ቁርኣን 17፥67 በባሕሩም ውስጥ ጉዳት ባገኛችሁ ጊዜ የምትጠሩዋቸው ሁሉ ይጠፋሉ፥ እርሱ(አላህ) "ሲቀር"፡፡ وَإِذَا مَسَّكُمُ الضُّرُّ فِي الْبَحْرِ ضَلَّ مَن تَدْعُونَ إِلَّا إِيَّاهُ
ጣዖታዊያን በባሕሩም ውስጥ ጉዳት ባገኛቸው ጊዜ የሚጠሩዋቸው ጣዖታታት የሰው እጅ ሥራዎች ሲሆኑ ይጠፋሉ፥ አሏህ ግን ሕያው ፈጣሪ ስለሆነ አይጠፋም። ስለዚህ "በቀር" "በስተቀር" ስለተባለ ዐውዱ እና አጠቃላይ አሳቡ ሳይታይ "አንድ ምድብ ነው" ማለት ስህተት እንዳለው ከተረዳን ዘንዳ "በቀር" ስላለ ኢብሊሥን የመላእክት ጥንተ ተፈጥሮ ውስጥ ማካተት ስህተት ነው።
ኢብሊሥ ከጂን እንጂ ከመላእክት አለመሆኑ ሐሠን አል-በስሪይ እንደተናገረው በኢብኑ ጀሪር ተተርኳል፥ በኢሥናዱም ሶሒሕ ነው። ኢብኑ ከሲር በመቀጠል በተፍሢሩ ላይ አድ-ደሓክ፣ ሠዒድ ኢብኑ ጀቢር፣ ኢብኑ ኢሥሐቅ ወዘተ "ኢብሊሥ መልአክ ነበር" ያሉት ከኢሥራዒልያት ትርክት እንደሆነ ተናግሯል፦
ተፍሢሩል ኢብኑ ከሲር 18፥50
"ሐሠን አል-በስሪይ እንደተናገረው፦ "ኢብሊሥ ከመላእክት አይደለም፥ ለአንዲት ቅጽበት እንኳን አልነበረም። ልክ አደም"ዐ.ሠ." ለሰው ሥረ-መሠረት እንደሆነ ሁሉ ኢብሊሥም ለጂን ሥረ-መሠረት ነው"። ይህ በኢብኑ ጀሪር ተተርኳል፥ በኢሥናዱም ሶሒሕ ነው። قال الحسن البصري : ما كان إبليس من الملائكة طرفة عين قط ، وإنه لأصل الجن ، كما أن آدم ، عليه السلام ، أصل البشر . رواه ابن جرير بإسناد صحيح
ተፍሢሩል ኢብኑ ከሲር 18፥50
"በእርግጥ በዚህ ሪዋያህ ከቀደምቶቹ የተተረከው ዘገባ አብዛኛውን ከኢሥራኢልያት እንደሆነ ይጤናል"። وقد روي في هذا آثار كثيرة عن السلف ، وغالبها من الإسرائيليات التي تنقل لينظر فيها
፨ሢሰልስ መላእክት የተፈጠሩበት ንጥረ ነገር ብቻ ሳይሆን ባሕርያቸውም ይለያል፥ መላእክት ፆታ የላቸውም፦
ቁርኣን 43፥19 "መላእክትንም እነርሱ የአልረሕማን ባሮች የኾኑትን ሴቶች አደረጉ"፡፡ ሲፈጠሩ ነበሩን? መመስከራቸው በእርግጥ ትጻፋለች፡፡ ይጠየቃሉም፡፡ وَجَعَلُوا الْمَلَائِكَةَ الَّذِينَ هُمْ عِبَادُ الرَّحْمَـٰنِ إِنَاثًا ۚ أَشَهِدُوا خَلْقَهُمْ ۚ سَتُكْتَبُ شَهَادَتُهُمْ وَيُسْأَلُونَ
ቁርኣን 37፥150 ወይስ እኛ እነርሱ የተጣዱ ሆነው "መላእክትን ሴቶች አድርገን ፈጠርን? أَمْ خَلَقْنَا الْمَلَائِكَةَ إِنَاثًا وَهُمْ شَاهِدُونَ
ከመላእክት መካከል ሴቶች ቢኖሩ ኖሮ ቁሬሾች፦ "መላእክት ሴቶች ናቸው" ማለታቸውን አይቃወምም ነበር፥ አሏህ መላእክትን ሴቶች አድርጎ አልፈጠረም። ጂኒዎች ግን ጾታ አላቸው፥ ዝርያ ስላላቸው የሚራቡ ወንድ እና ሴት ናቸው፦
ቁርኣን 18፥50 "እርሱን እና ዘሮቹን እነርሱ ለእናንተ ጠላቶች ሲኾኑ ከእኔ ላይ ረዳቶች አድርጋችሁ ትይዛላችሁን? ለበዳዮች ልዋጭነቱ ከፋ! أَفَتَتَّخِذُونَهُ وَذُرِّيَّتَهُ أَوْلِيَاءَ مِن دُونِي وَهُمْ لَكُمْ عَدُوٌّ ۚ بِئْسَ لِلظَّالِمِينَ بَدَلًا
ቁርኣን 72፥6 እነሆም "ከሰዎች የኾኑ ወንዶች በጂኒ ወንዶች ይጠበቁ ነበሩ"፡፡ ኩራትንም ጨመሩዋቸው፡፡ وَأَنَّهُ كَانَ رِجَالٌ مِّنَ الْإِنسِ يَعُوذُونَ بِرِجَالٍ مِّنَ الْجِنِّ فَزَادُوهُمْ رَهَقًا
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 1, ሐዲስ 312
ዘይድ ኢብኑ አርቀም እንደተረከው የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” አሉ፦ “ቆሻሻ ቦታዎች በሰይጣናት ይጎበኛሉ፥ ከእናንተም ወደዚያ ሲገባ፦ "አሏህ ሆይ! ከወንድ እና ከሴት ሰይጣናት በአንተ እጠበቃለው" ይበል። عَنْ زَيْدِ بْنِ أَرْقَمَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ “ إِنَّ هَذِهِ الْحُشُوشَ مُحْتَضَرَةٌ فَإِذَا دَخَلَ أَحَدُكُمْ فَلْيَقُلِ اللَّهُمَّ إِنِّي أَعُوذُ بِكَ مِنَ الْخُبُثِ وَالْخَبَائِثِ ” .
ኢብሊሥ ከጂን ስለሆነ አሏህን የማመጽ እና የመታዘዝ ነጻ ፈቃድ ስላለው በጌታው ላይ አምጾ ኮራ፥ መላእክት ግን የማመጽ እና የመታዘዝ ነጻ ፈቃድ ስለሌላቸው በባሕያቸው ውስጥ ኩራትና አመጽ የለም። አሏህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፥ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፦
ቁርኣን 38፥74 ኢብሊሥ ብቻ ሲቀር፡፡ "ኮራ"፤ ከከሓዲዎቹም ሆነ፡፡ إِلَّا إِبْلِيسَ اسْتَكْبَرَ وَكَانَ مِنَ الْكَافِرِينَ
ቁርኣን 16፥49 "እነርሱም አይኮሩም" وَهُمْ لَا يَسْتَكْبِرُونَ
ቁርኣን 21፥19 እርሱ ዘንድ ያሉትም መላእክት እርሱን ከመገዛት አይኮሩም፡፡ አይሰለቹምም፡፡ وَمَنْ عِندَهُ لَا يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِهِ وَلَا يَسْتَحْسِرُونَ
ቁርኣን 66፥6 አላህ ያዘዛቸውን ነገር በመጣስ አያምጹም፤ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ፡፡ لَّا يَعْصُونَ اللَّهَ مَا أَمَرَهُمْ وَيَفْعَلُونَ مَا يُؤْمَرُونَ
፨ሲያረብብ መላእክት በአሏህ ላይ አምጸው የሚገቡበት ጀሀነም ሆነ ታዘው የሚገቡበት ጀነት የላቸውም። ጂኒዎች ግን በምርጫቸው አምነው ጀነት ወይም ክደው ጀሀነም መግባት ይችላሉ፦
ቁርኣን 11፥119 የጌታህም ቃል፦ "ገሀነምን ከጂኒዎ እና ከሰዎች ሁሉ በእርግጥ እሞላታለሁ" በማለት ተፈጸመች። وَتَمَّتْ كَلِمَةُ رَبِّكَ لَأَمْلَأَنَّ جَهَنَّمَ مِنَ الْجِنَّةِ وَالنَّاسِ أَجْمَعِينَ
ቁርኣን 55፥45 ከጌታችሁም ጸጋዎች በየትኛው ታስተባብላላችሁ? فَبِأَيِّ آلَاءِ رَبِّكُمَا تُكَذِّبَان
ቁርኣን 55፥46 በጌታውም ፊት መቆምን ለፈራ ሁለት ገነቶች አሉት፡፡ وَلِمَنْ خَافَ مَقَامَ رَبِّهِ جَنَّتَانِ
ሱረቱር ረሕማን ዐውዱ ላይ ያሉት ሰው እና ጃን ናቸው፥ "ጌታችሁ" የሚለው ቃል "ረቢኩማ" رَبِّكُمَا ሲሆን ሁለተኛ መደብ ሙሰና ሰውን እና ጃንን ያመለክታል። “ታስተባብላላችሁ” የሚለው ቃል “ቱከዚባኒ” تُكَذِّبَانِ ሲሆን ሁለተኛ መደብ ሙሰና ሰውን እና ጃንን ያመለክታል፦
ቁርኣን 55፥14 ሰውን እንደ ሸክላ ከሚቅጨለጨል ደረቅ ጭቃ ፈጠረው፡፡ خَلَقَ الْإِنسَانَ مِن صَلْصَالٍ كَالْفَخَّارِ
ቁርኣን 55፥15 "ጃንንም ከእሳት ከኾነ ነበልባል ፈጠረው"፡፡ وَخَلَقَ الْجَانَّ مِن مَّارِجٍ مِّن نَّارٍ
የትንሳኤ ቀን ለሁለቱም የተቀጠረ ቀጠሮ ነው፥ የዚያን ቀን የተውበት በር ስለተዘጋ ሰው ሆነ ጂን ከኃጢኣቱ አሏህን ይቅርታ እንዲጠይቅ አይጠየቅም። ከዛ ይልቅ "የዚህንም ቀናችሁን ቅጣት ማግኘትን የሚያስጠነቅቋችሁ ከእናንተው የኾኑ መልእክተኞች አልመጧችሁምን" በመባል ፍርድ ያገኛሉ፦
ቁርኣን 44፥40 የመለያው ቀን ለሁሉም ቀጠሯቸው ነው፡፡ إِنَّ يَوْمَ الْفَصْلِ مِيقَاتُهُمْ أَجْمَعِينَ
ቁርኣን 55፥39 በዚያም ቀን ሰው እና ጃን ከኃጢኣቱ ገና አይጠየቅም፡፡ فَيَوْمَئِذٍ لَّا يُسْأَلُ عَن ذَنبِهِ إِنسٌ وَلَا جَانٌّ
ቁርኣን 6፥130 የጂኒዎች እና የሰዎች ጭፍሮች ሆይ! አንቀጾቼን በእናንተ ላይ የሚተርኩ የዚህንም ቀናችሁን ቅጣት ማግኘትን የሚያስጠነቅቋችሁ ከእናንተው የኾኑ መልእክተኞች አልመጧችሁምን? ይባላሉ፡፡ يَا مَعْشَرَ الْجِنِّ وَالْإِنسِ أَلَمْ يَأْتِكُمْ رُسُلٌ مِّنكُمْ يَقُصُّونَ عَلَيْكُمْ آيَاتِي وَيُنذِرُونَكُمْ لِقَاءَ يَوْمِكُمْ هَـٰذَا
ለጂኒዎች ጀነት እና ጀሃነም እንዲሁ የትንሳኤ ቀን ቀጠሮ እንዳላቸው እና የተፈጠሩበት አላማ ካየን ዘንዳ በነጻ ምርጫቸው አምነው ሙሥሊም አልያም ክደው ኩፋር የመሆን ምርጫ አላቸው፦
ቁርኣን 72፥14 «እኛም ከእኛ ውስጥ ሙሥሊሞች አሉ፡፡ ከእኛም ውስጥ በዳዮች አሉ፡፡ የሠለሙም ሰዎች እነዚያ ቅንን መንገድ መረጡ፡፡» وَأَنَّا مِنَّا الْمُسْلِمُونَ وَمِنَّا الْقَاسِطُونَ ۖ فَمَنْ أَسْلَمَ فَأُولَـٰئِكَ تَحَرَّوْا رَشَدًا
ስለዚህ "ኢብሊሥ መልአክ ነበር" የሚለው ትርክት ቁርኣን ላይ ሆነ ሐዲስ ላይ የለም። አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም