በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
ቁርኣን 5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልእክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልእክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
የተለያዩ ሰዎች በአንድ ጊዜ በተለያየ ሥፍራ ሆነውን የሚለምኑትን ልመና የሚሰማ አንድ አምላክ ብቻ ነው፥ ልመና የአምልኮ ክፍል ስለሆነ ልመናን የሚቀበል እና የሚሰማ ኢየሱስን የላከው አንዱ አምላክ አብ ብቻ ነው፦
ማቴዎስ 7፥11 በሰማያት ያለው አባታችሁ "ለሚለምኑት" እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?
πόσῳ μᾶλλον ὁ Πατὴρ ὑμῶν ὁ ἐν τοῖς οὐρανοῖς δώσει ἀγαθὰ τοῖς αἰτοῦσιν αὐτόν.
"በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት" የሚለው ኃይለ ቃል ተለማኝ አብ ለማኝ ፍጡራን እንደሆኑ ቁልጭ አርጎ ያሳያል። ኢየሱስ እራሱ አንዱን አምላክ ጠይቆ መልስ የሚጠብቅ ለማኝ ነበር፦
ዮሐንስ 11፥22 አሁንም ከአምላክ የምትለምነውን ሁሉ አምላክ እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።
καὶ νῦν οἶδα ὅτι ὅσα ἂν αἰτήσῃ τὸν Θεὸν δώσει σοι ὁ Θεός.
ኢየሱስ አምላክን ለምኖ የሚሰጠው ከሆነ እርሱ ለማኝ ነቢይ እንጂ ተለማኝ አምላክ በፍጹም አይደለም፥ ኢየሱስ ይህንን አንድ አምላክ ሌሊቱን ሙሉ ሲለምን በአምልኮ አሳልፏል፦
ሉቃስ 6፥12 በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ አምላክ ሲጸልይ አደረ።
Ἐγένετο δὲ ἐν ταῖς ἡμέραις ταύταις ἐξελθεῖν αὐτὸν εἰς τὸ ὄρος προσεύξασθαι, καὶ ἦν διανυκτερεύων ἐν τῇ προσευχῇ τοῦ Θεοῦ.
ኢየሱስ በጸሎት የሚለምን ለማኝ ከሆነ ጸሎቱን ሰምቶ የሚመልስለት አምላኩ ተለማኝ ነው። ሰዎችም የእርሱ ፈለግ ተከትለው አምላኩን ቢለምኑ ልመናቸውን ይሰማል፦
ዮሐንስ 15፥16 አብም በስሜ "የምትለምኑትን" ሁሉ ይሰጣችኃል።
ἵνα ὅ τι ἂν αἰτήσητε τὸν Πατέρα ἐν τῷ ὀνόματί μου δῷ ὑμῖν.
"በስሜ" የሚለው ይሰመርበት! በኢየሱስ ስም አብ ሲለመን ልመናውን ሰምቶ አብ ይሰጣል። አብን በኢየሱስ ስም ሲለመን ኢየሱስ ደግሞ አብን አማላጅ ሆኖ ይለምናል፦
ዮሐንስ 14፥14 ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
ἐάν τι αἰτήσητε ἐν τῷ ὀνόματί μου, ἐγὼ ποιήσω.
"አደርጋው"I will do" የሚለው መጻኢ ግሥ "ፓኤሶ" ποιήσω ሲሆን ምን እንደሚያደርግ ዐውዱ ላይ ተገልጿል፦
ዮሐንስ 14፥15 እኔም አብን "እለምናለሁ"፥ κἀγὼ ἐρωτήσω τὸν Πατέρα
"እለምናለሁ"I will pray" በማለት "አደርጋለው" የሚለው ድርጊት ጸሎት እንደሆነ እንቅጩን ፍርጥ አርጎ ተናግሯል። ኢየሱስ ለማኝ እንዲሁ አምላክ ደግሞ ተለማኝ ከሆነ ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ አብን ስለ አማኞች ይለምናል፦
ሮሜ 8፥34 በአምላክ ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ "የሚማልደው" ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ὅς ἐστιν ἐν δεξιᾷ τοῦ Θεοῦ, ὃς καὶ ἐντυγχάνει ὑπὲρ ἡμῶν.
"ኢንቱካኖ" ἐντυγχάνω ማለት "ጠራ" "ማለደ" "አማለደ" ማለት ሲሆን ኢየሱስ ለማኝ መሆኑን አምላክ ተለማኝ መሆኑን ፍንትው አርጎ ያሳያል፥ በቋንቋ ደረጀ "ማለደ" ማለት "ለመነ" "ደጅ ጠና" ማለት ነው። ኢየሱስ አማላጅ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም የጻፍኩትን ያንብቡ፦ https://t.me/Wahidcom/3374
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ፦"አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኃል" ባለው መሠረት ሐዋርያት አብን በተግባር ለምነውታል፦
የሐዋርያት ሥራ 4፥29 አሁንም ጌታ ሆይ! ወደ ዛቻቸው ተመልከት! ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።
የሐዋርያት ሥራ 4፥30 ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ባሪያ በኢየሱስ ስም ምልክት እና ድንቅ ይደረግ።
ἐν τῷ τὴν χεῖρά ἐκτείνειν σε εἰς ἴασιν καὶ σημεῖα καὶ τέρατα γίνεσθαι διὰ τοῦ ὀνόματος τοῦ ἁγίου Παιδός σου Ἰησοῦ.
"ፓይዶስ" Παιδός ማለት "ባሪያ" "አገልጋይ" ማለት ነው፥ በዚህ ባሪያ ስም የሚለመነው ጌታ አብ እንደሆነ በቂ ማሳያ ነው። ኢየሱስ ሰማይ ላይ እንደ አምላክ ተገልጋይ ሳይሆን አገልጋይ ነው፦
ዕብራውያን 8፥2 እርሱም የመቅደስ እና የእውነተኛይቱ ድንኳን "አገልጋይ" ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።
"በኢየሱስ ስም" ማለት ደግሞ "ኢየሱስ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባዘዛቸው መሠረት ወደ አብ መጸለይ በኢየሱስ ስም መጸለይ" ማለት ነው፥ "በ" የሚል መስተዋድድ ባለበት ቃል ላይ "ስም" የሚል ቃላት አንዳንድ ናሙና እንመልከት፦
1ኛ ስሙኤል 25፥9 የዳዊትም ጕልማሶች መጡ፥ ይህንም ቃል ሁሉ "በዳዊት ስም" ለናባል ነግረው ዝም አሉ።
"በዳዊት ስም" የሚለው ይሰመርበት! የዳዊትም ጕልማሶች ለናባል "በዳዊት ስም" ነገሩት ማለት "በዳዊት ትእዛዝ" ነገሩት ከሆነ እንግዲያውስ "በኢየሱስ ስም" አብን መለመን ማለት "በኢየሱስ ትእዛዝ" አብን መለመን ማለት ነው። ሌላ ናሙና እንመልከት፦
ማቴዎስ 10፥42 ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ "በደቀ መዝሙር ስም" የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም።
"በደቀ መዝሙር ስም" የሚለው ይሰመርበት! "በደቀ መዝሙር ስም" ጽዋ ውኃ ለታናናሾች ማጠጣት ዋጋ እንደሚያሰጥ ሁሉ "በኢየሱስ ስም" ጽዋ ውኃ ማጠጣት ዋጋ ያሰጣል፦
ማርቆስ 9፥41 የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ "በስሜ" ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ።
እንደ እናንተ ስሑት ሙግት "በኢየሱስ ስም" ማለት ልክ "በአሏህ ስም" እንደ ማለት ከሆነ "በዳዊት ስም" "በደቀ መዝሙር ስም" ማለት "በአምላክ ስም" ማለት ነው ብላችሁ ለምን አልተረዳችሁትም? ዳዊት እና ኢየሱስ ነቢያት ሲሆኑ ሐዋርያቱ ደግሞ ጻድቃን ናቸው፥ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፦
ማቴዎስ 10፥41 ነቢይን "በነቢይ ስም" የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም "በጻድቅ ስም" የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
"በነቢይ ስም" እና "በጻድቅ ስም" የሚለው ይሰመርበት! ያ ማለት ነቢይን እንደ ነቢይ የሚቀበል ጻድቅን እንደ ጻድቅ የሚቀበል ዋጋ አለው፥ ዐውደ ንባቡ ላይ "እናንተን የሚቀበል" በማለት ሐዋርያትን እንደ ጻድቅ መቀበል እንዲሁ "እኔን የሚቀበል" በማለት መልእክተኛውን ኢየሱስን እንደ ነቢይ መቀበል ምንዳ እና ትሩፋት አለው፦
ማቴዎስ 10፥40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
ስለዚህ "በኢየሱስ ስም" የተባለው "በዳዊት ስም" "በደቀ መዝሙር ስም" "በነቢይ ስም" "በጻድቅ ስም" በተባለበት ስሌት እና ቀመር ነው። “በ” የሚለውን “ለ” ብሎ ከተረዱት እንግዲያውስ “በ”-ጽዮን” የሚለውን “ለ”-ጽዮን” ብለው መረዳት ይኖርባቸዋል፦
መዝሙር 65፥1 አቤቱ “በ”-ጽዮን ለአንተ ምስጋና ይገባል።
לַמְנַצֵּ֥חַ מִזְמֹ֗ור לְדָוִ֥ד שִֽׁיר׃ לְךָ֤ דֻֽמִיָּ֬ה תְהִלָּ֓ה אֱלֹ֘הִ֥ים בְּצִיֹּ֑ון
ስለዚህ “ኢየሱስ ይመለካል” ብሎ ኲታ ገጠም ርእስ አርጎ በደምሳሳው መሞገት ወትሮም ቢሆን ዘንድሮም የሚያዋጣ ሙግት አይደለም፥ የሚለምንን ለማኝ መለመን በራሱ ሺርክ ነው። በኢሥላም ግን የመርየም ልጅ ኢየሱስ ከእርሱ በፊት እንዳሉት መልእክተኞች የሆነ መልእክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፦
ቁርኣን 5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልእክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልእክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡
مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም