በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 90፥12 ዓቀበቲቱም መውጣቷ ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ?
وَمَا أَدْرَاكَ مَا الْعَقَبَةُ
ዐውቀን በድፍረት ሆነ ሳናውቅ በስህተት ለማልነው መሓላ ከማካካሻ መካከል አንዱ ባሪያዎችን ከባርነት ነጻ ማውጣት ነው፦
ቁርኣን 58፥3 እነዚያም ከሚስቶቻቸው "እንደናቶቻችን ጀርባዎች ኹኑብን" በማለት የሚምሉ ከዚያም ወደ ተናገሩት የሚመለሱ ሳይነካኩ በፊት ባሪያን ነጻ ማውጣት በእነርሱ ላይ አለባቸው፡፡
وَالَّذِينَ يُظَاهِرُونَ مِن نِّسَائِهِمْ ثُمَّ يَعُودُونَ لِمَا قَالُوا فَتَحْرِيرُ رَقَبَةٍ مِّن قَبْلِ أَن يَتَمَاسَّا
ቁርኣን 5፥89 "አላህ በመሐላዎቻችሁ በውድቁ አይዛችሁም፥ ግን መሐላዎችን ባሰባችሁት ይይዛችኋል፡፡ ማስተሰሪያውም ቤተሰቦቻችሁን ከምትመግቡት ከመካከለኛው ምግብ አሥርን ምስኪኖች ማብላት ወይም እነርሱን ማልበስ ወይም ባሪያን ነጻ ማውጣት ነው"፡፡
لَا يُؤَاخِذُكُمُ اللَّهُ بِاللَّغْوِ فِي أَيْمَانِكُمْ وَلَـٰكِن يُؤَاخِذُكُم بِمَا عَقَّدتُّمُ الْأَيْمَانَ ۖ فَكَفَّارَتُهُ إِطْعَامُ عَشَرَةِ مَسَاكِينَ مِنْ أَوْسَطِ مَا تُطْعِمُونَ أَهْلِيكُمْ أَوْ كِسْوَتُهُمْ أَوْ تَحْرِيرُ رَقَبَةٍ ۖ
"ማስተሰሪያ" ለሚለው ቃል የገባው “ከፋራህ” كَفّارَة መሆኑን ልብ በል! “ከፋራህ” كَفّارَة ማለት "ማስተሰረያ" "ማካካሺያ" ማለት ነው። “ኒካሕ” نِكَاح የሚለው ቃል "ነከሐ" نَكَحَ ማለትም "አገባ" ወይም "ተዳራ" ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "ጋብቻ" ወይም "ትዳር" ማለት ነው፥ ባርነት ከማስቀሪያ አንዱ ባሮችን ማግባት ነው፦
ቁርኣን 24፥32 "ከእናንተም ትዳር የሌላቸውን አጋቡ! ከወንዶች ባሮቻችሁ እና ከሴቶች ባሮቻችሁም ለጋብቻ ብቁ የኾኑትን አጋቡ! ድኾች ቢኾኑ አላህ ከችሮታው ያከብራቸዋል፡፡ አላህም ስጦታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡
وَأَنكِحُوا الْأَيَامَىٰ مِنكُمْ وَالصَّالِحِينَ مِنْ عِبَادِكُمْ وَإِمَائِكُمْ ۚ إِن يَكُونُوا فُقَرَاءَ يُغْنِهِمُ اللَّهُ مِن فَضْلِهِ ۗ وَاللَّهُ وَاسِعٌ عَلِيمٌ
እዚህ አንቀጽ ላይ “አጋቡ” የሚለው የግስ መደብ የገባው ቃል “አንኪሑ” َأَنكِحُوا መሆኑን አንባቢ ልብ ይለዋል። ማንም ባሪያ ያለችው አስተምሮ፣ መልካም ሆኖላት፣ ከዚያ ነጻ አውጥቶ ያገባ ሁለት አጅር አለው፦
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 49, ሐዲስ 27
አቡ ሙሣ"ረ.ዐ." እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ማንም ባሪያ ያለችው ያስተምራት፣ መልካም ይሁንላት፣ ከዚያም ነጻ ያውጣት እና ያግባት! ለእርሱም ሁለት ትሩፋት አለው"።
عَنْ أَبِي مُوسَى ـ رضى الله عنه ـ قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم " مَنْ كَانَتْ لَهُ جَارِيَةٌ فَعَالَهَا، فَأَحْسَنَ إِلَيْهَا ثُمَّ أَعْتَقَهَا وَتَزَوَّجَهَا، كَانَ لَهُ أَجْرَانِ ".
"አጅር" أَجْر ማለት አምላካችን አሏህ በአኺራ የሚመነዳን "ምንዳ" "ትርሲት" "ስርጉት" "ትሩፋት" ነው። የዘካቱል ማል ገንዘብ ከሚውልበት ግልጋሎት አንዱ በባርነት ተገዢዎችን ነጻ ለማውጣት ነው፦
ቁርኣን 9፥60 ግዴታ ምጽዋቶች የሚከፈሉት ለድኾች፣ ለምስኪኖችም፣ በርሷም ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች፣ ልቦቻቸውም በኢሥላም ለሚለማመዱት፣ "በባርነት ተገዢዎችን ነጻ በማውጣት"፣ በባለ ዕዳዎችም፣ በአላህ መንገድም በሚሠሩ፣ በመንገደኛም ብቻ ነው፡፡ ከአላህ የተደነገገች ግዴታ ናት፡፡ አላህም ዐዋቂ ጥበበኛ ነው፡፡
إِنَّمَا الصَّدَقَاتُ لِلْفُقَرَاءِ وَالْمَسَاكِينِ وَالْعَامِلِينَ عَلَيْهَا وَالْمُؤَلَّفَةِ قُلُوبُهُمْ وَفِي الرِّقَابِ وَالْغَارِمِينَ وَفِي سَبِيلِ اللَّهِ وَابْنِ السَّبِيلِ ۖ فَرِيضَةً مِّنَ اللَّهِ ۗ وَاللَّهُ عَلِيمٌ حَكِيمٌ
ነቢያችን"ﷺ" በነቢይነት ከመላካቸው በፊት በዐረቡ ምድር ባሪያ ይሸጥ እና ይገዛ ነበር፥ ከዚያም ባሻገር እነርሱን መማታት፣ አካል ማጉደል እና መግደል መደበኛ ነገር ነበር። ነገር ግን ቁርኣን ሲወርድ ባሪያን ከባርነት ነጻ ማውጣት፣ የባሪያን አካል ያጎደለ ማጉደል፣ ባሪያን የገደለ መግደል ተደነገገ፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 21, ሐዲስ 49
ሠሙራህ ኢብኑ ጁንዱብ እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "ማንም ባሪያውን የገደለ እንገድለዋለን፥ ማንም አካሉን ያጎደለ አካሉን እናጎድለዋለን"።
عَنْ سَمُرَةَ بْنِ جُنْدُبٍ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم " مَنْ قَتَلَ عَبْدَهُ قَتَلْنَاهُ وَمَنْ جَدَعَهُ جَدَعْنَاهُ " .
ነቢያችን"ﷺ" የራሳቸውን አገልጋዮች እና የሌሎችንም ጭምር ሚስት እና ባልደረባ በማድረግ ነጻ አውጥተዋል፥ ሶፊያህ፣ ማሪያህ፣ ዘይድ፣ አነሥ፣ ቢላል፣ ዐማር፣ ሱሀይብ ተጠቃሽ ናቸው፦
ቁርኣን 90፥11 ዓቀበቲቱንም አልወጣም።
فَلَا اقْتَحَمَ الْعَقَبَةَ
ቁርኣን 90፥12 ዓቀበቲቱም መውጣቷ ምን እንደኾነች ምን አሳወቀህ?
وَمَا أَدْرَاكَ مَا الْعَقَبَةُ
ቁርኣን 90፥13 እርሱም ባሪያን መልቀቅ ነው፡፡
فَكُّ رَقَبَةٍ
"ረቀባህ" رَقَبَة ማለት "ባሪያ" ወይም "አገልጋይ" ማለት ሲሆን ባለቤቱ ባሪያ ነጻ እስኪወጣ ድረስ የሚበላውን ማብላት፣ የሚለብሰውን ማልበስ ግዴታ አለበት። ከዐቅማቸው በላይ የሆነን ጫናን መጫን ሆነ መማታት ግን ሐራም ነው፦
ሡነን ኢብኑ ማጃህ መጽሐፍ 33, ሐዲስ 34
አቢ ዘር እንደተረከው፦ "የአሏህ መልእክተኛም"ﷺ" እንዲህ አሉ፦ "አሏህ በእጃችሁ ሥር ያረጋቸው ባሮችን ወንድሞቻችሁ ናቸው፥ የምትበሉትን አብሏቸው፣ የምትለብሱትን አልብሷቸው፣ ከዐቅማቸው በላይ የሆነን ጫናን አትጫኗቸው። ከተጫናችዋቸው አግዟቸው"።
عَنْ أَبِي ذَرٍّ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ ـ صلى الله عليه وسلم ـ " إِخْوَانُكُمْ جَعَلَهُمُ اللَّهُ تَحْتَ أَيْدِيكُمْ فَأَطْعِمُوهُمْ مِمَّا تَأْكُلُونَ وَأَلْبِسُوهُمْ مِمَّا تَلْبَسُونَ وَلاَ تُكَلِّفُوهُمْ مَا يَغْلِبُهُمْ فَإِنْ كَلَّفْتُمُوهُمْ فَأَعِينُوهُمْ " .
ባሪያ ነጻ በማውጣት አጅር ከሚያገኙት አሏህ ያርገን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም