በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 5፥116 አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሣ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- "እኔን እና እናቴን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን?» በሚለው ጊዜ አስታውስ ፡፡
وَإِذْ قَالَ اللَّهُ يَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ أَأَنتَ قُلْتَ لِلنَّاسِ اتَّخِذُونِي وَأُمِّيَ إِلَـٰهَيْنِ مِن دُونِ اللَّهِ
እኛ ሙሥሊሞች፦ "ዐበይት ክርስቲያኖች ማለትም ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና አንግሊካን ማርያምን ያመልካሉ" ስንል በተቃራኒው እነርሱ፦ "እናከብራታለን እንጂ አናምልካትም" ብለው ዓይናቸውን በጨው አጥበው ይዋሻሉ፥ ምክንያቱም "እናመልካታለን" ካሉ አምልኮ የሚገባው አንድ አምላክ እንደሆነ ባይብል ላይ በቅጡ ሰፍሯል፦
1ኛ ሳሙኤል 7፥3 ልባችሁንም ወደ ያህዌህ አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ።
ማቴዎስ 4፥10 ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ።
"እርሱንም ብቻ አምልኩ" "እርሱንም ብቻ አምልክ" የሚል ጥብቅ ትእዛዝ አስምርበት! "እርሱ" ተብሎ የተቀመጠ ነጠላ ተሳቢ ተውላጠ ስም አንድ ቀዋሜ ማንነትን ቁልጭ እና ፍንትው አርጎ ያሳያል፥ አምልኮ የሚገባው ይህ አንዱ ማንነት ብቻ ነው። ይህንን ጥቅስ ሲያዩ ጭራሽ ወደ ማርያም፦ "ከልጅሽ ጋር አስታርቂን ብለን እጠይቃታለን እንጂ ወደ እርሷ አንጸልይም" የሚል ቅጥፈት ይቀጥፋሉ።
፨ሲጀመር ሁሉን ዐዋቂ፣ ሁሉን ሰሚ እና ሁሉን ተመልካች አንዱ አምላክ ሆኖ ሳለ የማወቅ፣ የመስማት እና የመመልከት ውስንነት ያለበትን ፍጡር በሌለበት መለማመን ሆነ መጠየቅ ሺርክ ነው።
፨ሲቀጥል ወደ ማርያም ድብን አርጋችሁ ትጸልያላችሁ፥ የአዋልድ መጻሕፍቶቻችሁ ይህንን ያሳብቃሉ፦
መጽሐፈ አርጋኖን ዘሰኞ ምዕራፍ 2 ቁጥር 1
"እኔ በዚህ ጸሎት በጸለይሁ ጊዜ ወደ አንደበቴ ነገር ጆሮሽን ዘንበል አድርገሽ ስሚ፥ ሰምተሽም ቸል አትበይ። በብሩኅ ልቦና በንጹሕ አሳብ የአንደበቴን ነገር ተቀበይው እንጂ"።
ክብረ ድንግል ማርያም 1
"እርሷን "ደስ ይበልሽ" እያልን ይቅርታ እንድትሰጠው ወደ እርሷ እንጸልያለን"።
፨ሢሰልስ በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ ለማርያም አምልኮ እንደሚገባት ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ ተብሎ የሚሽሞነሞነው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ተናግሯል፦
እንዚራ ስብሐት ምዕራፍ 12 ቁጥር 98, "ለአንቺም የምስጋና እጅ መንሻን አቀርባለሁ፣ በመፍራት እገዛልሻለሁ፣ በመስገድም እጅ እነሣሻለሁ። የአምልኮ መሥዋዕትንም ለአንቺ እሠዋለሁ"።
የአምልኮ መሥዋዕት ሊሰዋለት የሚገባው አንድ አምላክ ሆኖ ሳለ ለማርያም መሠዋቱ በራሱ ዓይን ያስፈጠጠ እና ጥርስ ያስገጠጠ ሺርክ ነው።
፨ሲያረብብ በ 376 ድኅረ-ልደት የተነሱት ኮልይሪዲያን"collyridian" ክርስቲያኖች ኢየሱስ "ቴዎስ" θεός ብለው ባሉበት አፋቸው ማርያምን በግልጽ "ቴአ" θεά ማለትም "ሴት አምላክ" ይሏታል፥ ካቶሊክ፣ ኦርቶዶስ፣ አንግሊካን ኢየሱስን "ኩሪዮስ" κύριος ብለው ባሉበት አፋቸው ማርያምን በግልጽ "ኩሪያ" κυρία ማለትም "ሴት ጌታ" ይሏታል። በአገራችን ኦርቶዶክሶች ደግሞ ኢየሱስን "እግዚእ" ብለው ባሉበት አፋቸው ማርያምን በግልጽ "እግዚኢት" ማለትም "ሴት ጌታ" ይሏታል፥ ኢየሱስን "እግዚኢነ" ማለትም "ጌታችን" እንደሚሉት ሁሉ ማርያምን "እግዚኢትነ" ማለትም "ጌታችን" ይሉአታል። "አምላክ" ለሚለው ነጠላ ቃል ብዜት "አማልክት" ሲሆን ጸያፍ ርቢው "አምላኮች" ነው፥ እናማ ከዚህ የበለጠ ማርያምን አምላክ አድርጎ መያዝ አለን? ይህ አምልኮ ካልሆነ ምን ይባላል? ይህ አምልኮተ ማርያም ከልጇ የተገኘ ትምህርት ስላልሆነ አምላካችን አሏህ ኢየሱስን፦ "አንተ ለሰዎቹ፡- "እኔን እና እናቴን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? ብሎ ይጠይቀዋል፦
ቁርኣን 5፥116 አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሣ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- "እኔን እና እናቴን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን?» በሚለው ጊዜ አስታውስ ፡፡
وَإِذْ قَالَ اللَّهُ يَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ أَأَنتَ قُلْتَ لِلنَّاسِ اتَّخِذُونِي وَأُمِّيَ إِلَـٰهَيْنِ مِن دُونِ اللَّهِ
እርሱም፦ "በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን ማለት ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም" በማለት መልስ ይሰጣል፦
ቁርኣን 5፥117 በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬን እና ጌታችሁን አላህን ማለት ማለትን እንጂ ለእነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡
مَا قُلْتُ لَهُمْ إِلَّا مَا أَمَرْتَنِي بِهِ أَنِ اعْبُدُوا اللَّهَ رَبِّي وَرَبَّكُمْ
"አምላክ" የሚለውም ቃል "መለከ" ማለትም "አመለከ" ከሚል የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን "የሚመለክ" ማለት ነው። ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት (2005) ገጽ 708)
ከዚህ አንጻር ዐበይት ክርስትና ማርያምን አያመልኳትምን? እንዴታ! ድብን አርገው ያመልካሉ። አንድ ሰው ፍላጎቱን አምላኩ አድርጎ ያዘ ማለት ፍላጎቱን አምላኬ ብሎ ጠራ ማለት ሳይሆን ለአምላክ የሚሰጠውን የአምልኮ ክፍል ለፍላጎቱ ቅድሚያ ሰጠ ማለት ነው፦
ቁርኣን 25፥43 ፍላጎቱን አምላኩ አድርጎ የያዘውን ሰው አየህን? አንተ በእርሱ ላይ ጠባቂ ትሆናለህን?
أَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَـٰهَهُ هَوَاهُ أَفَأَنتَ تَكُونُ عَلَيْهِ وَكِيلًا
የማርያምን አምላክ አርጎ መያዝ በዚህ ሒሳብ መረዳት ይቻላል። በተመሳሳይ ጳውሎስ፦ "ሆዳቸው አምላካቸው ነው" ብሏል፦
ፊልጵስዩስ 3፥19 መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው።
ያ ማለት ማለት ሆዳቸውን "አምላኬ" ብለው ጠሩ ማለት ሳይሆን ለአምላክ የሚሰጠውን የአምልኮ ክፍል ለሆዳቸው ቅድሚያ ሰጡ ማለት ነው፥ የማርያምን አምላክ አርጎ መያዝ በዚህ ስሌት መረዳት ይቻላል። በዐበይት ክርስትና አምልኮተ ማርያም የተዘፈቃችሁ ካላችሁ ሞት ሳይመጣባችሁ አሊያም የፍርዱ ቀን ከመምጣቱ በፊት ወደ አሏህ በንስሓ ተመለሱ!
አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።
✍ከወሒድ ዐቃቢ ኢሥላም
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም