በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ቁርኣን 59፥24 እርሱ አላህ ፈጣሪው፣ አስገኚው፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አሉት፡፡
هُوَ اللَّهُ الْخَالِقُ الْبَارِئُ الْمُصَوِّرُ ۖ لَهُ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ
በግዕዝ "አስማት" ማለት "ስም" ለሚለው ብዜት ሲሆን "ስሞች" ግን "ስም" ለሚለው ጸያፍ ርቢ ነው፥ ይህንን በአውንታዊ ከተረዳን ዘንዳ አምላካችን አሏህ በቁርኣን የተገለጹ ዘጠና ዘጠኝ ባሕርያቱን የሚገልጹ የተዋቡ አስማት አሉት። ከስሞቹ አንዱ "አል ባሪእ" ነው፥ "አል ባሪእ" الْبَارِئ የሚለው ቃል "በረአ" بَرَأَ ማለትም "ተገኘ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "አስገኚው" ማለት ነው፦
ቁርኣን 59፥24 እርሱ አላህ ፈጣሪው፣ "አስገኚው"፣ ቅርጽን አሳማሪው ነው፡፡ ለእርሱ መልካሞች ስሞች አሉት፡፡
هُوَ اللَّهُ الْخَالِقُ الْبَارِئُ الْمُصَوِّرُ ۖ لَهُ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَىٰ
እዚህ አንቀጽ ላይ "አስገኚው" ለሚለው የገባው ቃል "አል ባሪእ" الْبَارِئ ነው፥ አምላካችን አሏህ ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር በማስገኘቱ "አስገኚ" ተብሏል። "ተገኚ" ደግሞ "መብሩዕ" مَبْرُوء ሲሆን "ተፈጣሪ" ነው፥ አሏህ አስገኚ ሲሆን ፍጡር ደግሞ "ተገኚ" ነው። "በሪያህ" بَرِيَّة ማለት "ግኝት" ማለት ነው፦
ቁርኣን 98፥7 እነዚያ ያመኑት እና መልካሞችንም የሠሩት እነዚያ እነርሱ ከ"ፍጥረት" ሁሉ በላጭ ናቸው፡፡
إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ أُولَـٰئِكَ هُمْ خَيْرُ الْبَرِيَّةِ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ፍጥረት" ለሚለው የገባው ቃል "አል በሪያህ" الْبَرِيَّة ሲሆን "ግኝት" ማለት ነው።
"ረብ" رَبّ የሚለው ቃል "ረበ" رَبَّ ማለትም "ጌተ" "ተንከባከበ" "አሳደገ" ከሚል ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ጌታ" "ተንከባካቢ" "አሳዳጊ" ማለት ነው፦
ቁርኣን 17፥24 ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው፡፡ «ጌታዬ ሆይ! በትንሽነቴ "እንዳሳደጉኝ" እዘንልላቸውም» በል፡፡
وَاخْفِضْ لَهُمَا جَنَاحَ الذُّلِّ مِنَ الرَّحْمَةِ وَقُل رَّبِّ ارْحَمْهُمَا كَمَا رَبَّيَانِي صَغِيرًا
እዚህ አንቀጽ ላይ "እዳሳደጉኝ" ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል "ረበያኒ" رَبَّيَانِي ሲሆን ስንፈለቅቀው ሥርወ ቃሉ "ረበ" رَبَّ ነው፦
ቁርኣን 26፥18 ፈርዖንም አለ «ልጅ ኾነህ በእኛ ውስጥ "አላሳደግንህምን"? በእኛ ውስጥም ከዕድሜህ ብዙ ዓመታትን አልተቀመጥክምን?
قَالَ أَلَمْ نُرَبِّكَ فِينَا وَلِيدًا وَلَبِثْتَ فِينَا مِنْ عُمُرِكَ سِنِينَ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ለም" لَمْ የሚለው ሐርፉን ነፍይ ሲነሳ "አሳደግንህ" ለሚለው የገባው ቃል "ኑረባከ" نُرَبِّكَ እንደሆነ ከተግባባን 17፥24 ዐውዱ ላይ በሙሰና "ለሁማ" لَهُمَا የተባሉት ወላጆች ናቸው፦
ቁርኣን 17፥23 ጌታህም እንዲህ ሲል አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ "በወላጆቻችሁም" መልካምን ሥሩ፡፡
وَقَضَىٰ رَبُّكَ أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا إِيَّاهُ وَبِالْوَالِدَيْنِ إِحْسَانًا
ወንድ ወላጅ "ዋሊድ" وَالِد ሲባል፣ ሴት ወላጅ "ዋሊዳህ" وَالِدَة ስትባት፣ ሁለቱም በሙሰና ደግሞ "ዋሊደይኒ" وَالِدَيْنِ ይባላሉ፥ ከሁለቱ የሚገኘው ልጅ ደግሞ "ወለድ" وَلَد ይባላል። ወላጆች በሌላ ተለዋዋጭ ቃል "አበዋን" أَبَوَان ይባላሉ፦
ቁርኣን 12፥100 "ወላጆቹንም" በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፡፡
وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ወላጆቹ" ለሚለው የገባው ቃል "አበወይሂ" أَبَوَيْهِ ሲሆን መደቡ "አብ" أَب ነው፥ "ኡም" أُمّ የሚለው ቃል "አመ" أَمَّ ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን "እናት" ማለት ብቻ ሳይሆን "ማዕከል" "ምንጭ" "መሠረት" ማለትም ነው፦
ቁርኣን 6፥92 የከተሞችን እናት እና በዙሪያዋ ያሉትን ሰዎች ልታስጠነቅቅበት አወረድነው፡፡
وَلِتُنذِرَ أُمَّ الْقُرَىٰ وَمَنْ حَوْلَهَا
እዚህ አንቀጽ ላይ መካህ "ኡም" أُمّ ተብላለች፥ ወላጅ ስለሆነች ሳይሆን ለዓለማችን ማዕከት ስለሆነች ነው። እንቀጥል፦
ቁርኣን 3፥7 እርሱ ያ በአንተ ላይ መጽሐፉን ያወረደ ነው፡፡ ከእርሱ ግልጽ የኾኑ አንቀጾች አልሉ፡፡ እነሱ የመጽሐፉ "መሠረት" ነው፡፡
هُوَ الَّذِي أَنزَلَ عَلَيْكَ الْكِتَابَ مِنْهُ آيَاتٌ مُّحْكَمَاتٌ هُنَّ أُمُّ الْكِتَابِ
እዚህ አንቀጽ ላይ አያቱል ሙሕከማት "ኡም" أُمّ ተብለዋል፥ በሌላ አንቀጽ ደግሞ ለሕወል መሕፉዝ "ኡም" أُمّ ተብሏል፦
ቁርኣን 13፥39 የመጽሐፉ "መሠረት" እርሱ ዘንድ ነው፡፡
وَعِندَهُ أُمُّ الْكِتَابِ
ቁርኣን 43፥4 እርሱም በመጽሐፉ "እናት" ውስጥ እኛ ዘንድ በእርግጥ ከፍተኛ ጥበብ የተመላ ነው፡፡
وَإِنَّهُ فِي أُمِّ الْكِتَابِ لَدَيْنَا لَعَلِيٌّ حَكِيمٌ
ተወዳጁ ነቢያችን"ﷺ" ደግሞ በሐዲስ ላይ ሰባት የተደጋገሙ አናቅጽ የያዘችው ሡረቱል ፋቲሓህ "ኡም" أُمّ እንደሆነች ነግረውናል፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 47, ሐዲስ 3415
አቢ ሁረይራህ”ረ.ዐ” እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ "አል ሐምዱሊሏህ የቁርኣን "እናት"፣ የመጽሐፉ "እናት" እና ሰባት የተደጋገሙ ናት።
عَنِ ابْنِ أَبِي ذِئْبٍ، عَنِ الْمَقْبُرِيِّ، عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم “ الْحَمْدُ لِلَّهِ أُمُّ الْقُرْآنِ وَأُمُّ الْكِتَابِ وَالسَّبْعُ الْمَثَانِي
መካህ፣ አያቱል ሙሕከማት፣ ለሕወል መሕፉዝ እና ሡረቱል ፋቲሓህ "ኡም" أُمّ የተባሉት "ማዕከል" "መሠረት" "ምንጭ" ለማለት መዕነዊይ እንጂ "ወላጅ" ለማለት ሐሣሢይ አይደለም፥ "መዕነዊይ" مَعْنَوِيّ ማለት "ፍካሬአዊ"allegorical" ማለት ሲሆን "ሐሣሢይ حَسَّاسِيّ ማለት ደግሞ "እማሬአዊ"literal" ማለት ነው።
አምላካችን አሏህ ሙሣፊርን "ኢብኑሥ ሠቢል" اِبْن السَّبِيل ይላቸዋል፥ "ኢብን" اِبْن ማለት "ልጅ" ማለት ነው፦
ቁርኣን 2፥215 ምንን ለማንም እንደሚለግሱ ይጠይቁካል፥ “ከመልካም ነገር የምትለግሱት ለወላጆች፣ ለቅርብ ዘመዶች፣ ለየቲሞችም፣ ለድሆችም እና "ለመንገደኞች" ነው” በላቸው፡፡
يَسْأَلُونَكَ مَاذَا يُنفِقُونَ ۖ قُلْ مَا أَنفَقْتُم مِّنْ خَيْرٍ فَلِلْوَالِدَيْنِ وَالْأَقْرَبِينَ وَالْيَتَامَىٰ وَالْمَسَاكِينِ وَابْنِ السَّبِيلِ
እዚህ አንቀጽ ላይ "መንገደኞች" ለሚለው የገባው ቃል "ኢብኑሥ ሠቢል" اِبْن السَّبِيل ሲሆን "የመንገድ ልጅ" ማለት ነው፥ መንገደኛ በመንገድ ሥር መሆኑን ለማሳየት የመጣ መዕነዊይ እንጂ ሐሣሢይ አይደለም። "ኢብን" اِبْن ሥርወ ቃሉ "በና"بَنَى ሲሆን "በና"بَنَى ማለት "ገነባ" ማለት ነው፦
ቁርኣን 66፥11 «ጌታዬ ሆይ! አንተ ዘንድ በገነት ውስጥ ለእኔ ቤትን "ገንባልኝ"፡፡ ከፈርዖን እና ከሥራውም አድነኝ፡፡ ከበደለኞቹ ሕዝቦችም አድነኝ» ባለች ጊዜ፡፡
إِذْ قَالَتْ رَبِّ ابْنِ لِي عِندَكَ بَيْتًا فِي الْجَنَّةِ وَنَجِّنِي مِن فِرْعَوْنَ وَعَمَلِهِ وَنَجِّنِي مِنَ الْقَوْمِ الظَّالِمِينَ
የፈርዖን ሚስት "ገንባ" ላለችበት የገባው ግሥ "ኢብኒ" ابْنِ ነው፥ አሏህ ሰማይን እንደፈጠረ እሙን ቢሆንም "ገነባናት" ለሚለው የገባው ቃል "በነይና-ሃ" بَنَيْنَاهَا ነው፦
ቁርኣን 56፥47 ሰማይንም በኀይል ገነባናት፡፡
وَالسَّمَاءَ بَنَيْنَاهَا بِأَيْدٍ
ስለዚህ "ኢብን" اِبْن መዕነዊይ በሆነ አገላለጽ ሊመጣ ይችላል። በዐረቢኛ "አብ" أَب ማለት "ባለቤት" በሚል ይመጣል፥ ለምሳሌ፦ የዐብዱል ሙጧሊብ ልጅ ዐብዱል ዑዛ በቁርኣን "አቢ ለሀብ" أَبِي لَهَب ተብሏል፦
ቁርኣን 111፥1 የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ፥ እርሱም ከሰረ፡፡
تَبَّتْ يَدَا أَبِي لَهَبٍ وَتَبَّ
"አቢ" أَبِي የሚለው ኢሥሙል መጅሩር "አብ" أَب የሚለውን መደብ አመላካች ነው፥ "ለሀብ" لَهَب ማለት "መንቀልቀል" ማለት ነው። "መንቀልቀል" የተባለው እሳት ጀሀነም ውስጥ ነው፦
ቁርኣን 111፥3 የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት በእርግጥ ይገባል፡፡
سَيَصْلَىٰ نَارًا ذَاتَ لَهَبٍ
ቁርኣን 77፥31 አጠላይ ያልኾነ ከእሳቱም ላንቃ የማያድን ወደ ኾነው አዝግሙ፡፡
لَّا ظَلِيلٍ وَلَا يُغْنِي مِنَ اللَّهَبِ
በጥቅሉ "አቢ ለሀብ" أَبِي لَهَب ማለት "የመንቀልቀል ባለቤት" ማለት ነው ነው፥ "አብ" أَب እዚህ ዐውድ ላይ ወላጅ "አባት" ማለት ሳይሆን "ባለቤት" ማለት ነው።
አምላካችን አሏህ አስገኚ፣ ዓለማትን የሚያስተናብር ጌታ፣ የንግሥና እና የፍርዱ ቀን ባለቤት መሆኑን በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ በቁርኣን ተቀምጧል።
በባይብል ደግሞ "አብ" אָב የሚለው የዕብራይስጥ ቃል "አስገኚ" ለሚለው ቃል ሥነ-ዘይቤአዊ አገላለጽ"analogical expression" ሆኖ መጥቷል፦
ዘዳግም 32፥6 የገዛህ አባትህ አይደለምን? የፈጠረህ እና የመሠረተህ እርሱ ነው።
הֲלוֹא־ הוּא֙ אָבִ֣יךָ קָּנֶ֔ךָ ה֥וּא עָֽשְׂךָ֖ וַֽיְכֹנְנֶֽךָ׃
አንዱ አምላክ ስለ ፈጠረ እና ስለ መሠረተ "አብ" אָב መባሉ በእማሬአዊ "ወላዲ" ሳይሆን በፍካሬአዊ "አስገኚ" ማለት ነው። አምላክ "አባት" መባሉ "ባለቤት" መባልን ያሳያል፥ ለምሳሌ የዮሐንስ የማዕረግ ስም "አቡ ቀለምሲስ" ሲሆን "የራእይ ባለቤት" ማለት ሲሆን "አባ ወራ" እራሱ "ባለቤት" ማለት ነው። የዝናብ ባለቤት አምላክ ሲሆን ለዝናብ አባት ተብሏል፦
ኢዮብ 38፥28 በውኑ ለዝናብ "አባት" አለውን ወይስ የጠልን ነጠብጣብ "የወለደ" ማን ነው?
הֲיֵשׁ־לַמָּטָ֥ר אָ֑ב אֹ֥ו מִי־הֹ֝ולִ֗יד אֶגְלֵי־טָֽל׃
እዚህ አንቀጽ ላይ "አባት" ተብሎ በዕብራይስጡ የገባ ቃል "አብ" אָ֑ב መሆኑን ልብ አድርግ! "አባት" ሲባል "ባለቤት" "አስገኚ" "ምንጭ" "ባለቤት" በሚል ቀመር ከተረዳን ዘንዳ የኢየሱስ "አባት" ሲባል የኢየሱስ "አስገኚ" በሚል እንረዳለን፦
ቆላስይስ 1፥3 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አባት አምላክን ሁልጊዜ እናመሰግናለን።
Εὐχαριστοῦμεν τῷ Θεῷ Πατρὶ τοῦ Κυρίου ἡμῶν Ἰησοῦ Χριστοῦ.
አንዱ አምላክ የኢየሱስ "አባት" ነው ሲባል የኢየሱስ "አስገኚ" በሚል ተቀጽሎ እንደመጣ በቀላሉ እንረዳለን። አንዱ አምላክ ሁሉንም አማንያን ስለሚያስተናብር "አንድ አባት" ተብሏል፦
ሚልክያስ 2፥10 ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?
הֲלֹ֨וא אָ֤ב אֶחָד֙ לְכֻלָּ֔נוּ הֲלֹ֛וא אֵ֥ל אֶֽחָ֖ד בְּרָאָ֑נוּ
ዮሐንስ 8፥41 አንድ አባት አለን፥ እርሱም አምላክ ነው።
ἕνα Πατέρα ἔχομεν τὸν Θεόν.
ኤፌሶን 4፥6 አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።
εἷς Θεὸς καὶ Πατὴρ πάντων,
እኛ እያንዳንዳችን ወላጅ አባት አለን፥ ወላጃችንን "አባት" ብለን እንጠራለን፥ ኢየሱስ "አንዱ የሰማዩን አምላክ እንጂ "ማንንም "አባት" ብላችሁ አትጥሩ" ሲለን "አባት" የሚለው ካለመኖር ወደ መኖር ያስገኘ "አስገኚ" ብቻ አመላካች ነው፦
ማቴዎስ 23፥9 "አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና" በምድር ላይ ማንንም፦ "አባት" ብላችሁ አትጥሩ።
καὶ πατέρα μὴ καλέσητε ὑμῶν ἐπὶ τῆς γῆς· εἷς γάρ ἐστιν ὑμῶν ὁ Πατὴρ ὁ οὐράνιος.
"አባት" ለአንዱ አምላክ ሲቀጸል በራሱ "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" ማለት እንጂ "የባሕርይ አባት" ማለት አይደለም። ለምሳሌ፦ አምላክ "እሳት" ተብሏል፦
ዕብራውያን 12፥29 አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ "እሳት" ነው።
ዘዳግም 4፥24 አምላክህ ያህዌህ የሚበላ እሳት እና ቀናተኛ አምላክ ነው።
"እሳት" ማለት "ቁጠኛ" "ቀጪ" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ፍካሬአዊ አነጋገር መሆኑን ከተረዳን ዘንዳ በተመሳሳይም "አባት" ማለት "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" "ባለቤት" በሚል እንረዳለን። አምላክ "ድንጋይ" ተብሏል፦
ዘዳግም 32፥4 እርሱ "ዓለት" ነው።
הַצּוּר֙
"ዓለት" ማለት "ድንጋይ" ማለት ነው፥ "ድንጋይ" ማለት "መሸሸጊያ" "አንባ" የሚለውን ለመግለጽ የመጣ ፍካሬአዊ አነጋገር መሆኑን ከተረዳን ዘንዳ በተመሳሳይም "አባት" ማለት "አስገኚ" "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" "ባለቤት" በሚል እንረዳለን።
በ 325 ድኅረ ልደት የተከናወነው የኒቂያ ጉባኤ፦ "ከአምላክ የተገኘ አምላክ" በማለት አሏህን ወላዲ መሢሑን ተወላዲ በማድረግ ለአሏህ ቁራጭን አደረጉለት፦
ቁርኣን 43፥15 ከባሮቹም ለእርሱ ቁራጭን ልጅ አደረጉለት፡፡ ሰው በእርግጥ ግልጽ ከሓዲ ነው፡፡
وَجَعَلُوا لَهُ مِنْ عِبَادِهِ جُزْءًا ۚ إِنَّ الْإِنسَانَ لَكَفُورٌ مُّبِينٌ
አሏህ አንድ ነው፥ እርሱ ከማንነቱ እና ከምንነቱ ማንንም አልወለደም። ከእርሱ ማንነት እና ምንነት የተወለደ ማንም የለም፥ ከእርሱ የተወለደ ማንም አምላክ የለም፦
112፥1 በል «እርሱ አላህ አንድ ነው፡፡
قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ
112፥3 አልወለደም፤ አልተወለደምም፡፡
لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ
ቁርኣን 23፥91 አላህ ምንም ልጅን አልወለደም፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡
مَا اتَّخَذَ اللَّهُ مِن وَلَدٍ وَمَا كَانَ مَعَهُ مِنْ إِلَـٰهٍ
“ወለድ” وَلَد የሚለው ቃል “ወለደ” وَلَدَ ማለትም “ወለደ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ወልድ” ወይም “ልጅ” ማለት ነው። "ከአምላክ አካል አካልን ወስዶ እና ከባሕርይው ባሕርይን ወስዶ፥ አብን መስሎ እና አህሎ መገኘት ወይም መወለድ" የሚለውን እሳቤ ቁርኣን ስለማይቀበል ወደዚያ የሚጠጋ "አባት" የሚለውን ስያሜ ለአሏህ አይጠቀምም። እኛ ሙሥሊሞችም አንጠቀምም፥ ከዚያ ይልቅ "አብ" የሚለው ትርጉሙ "አስገኚ" ወይም "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" አሊያም "ባለቤት" የሚል ፍቺ ካለው በቁርኣን በግልጽ አሏህ "አስገኚ" የተባለበትን "አል ባሪእ" الْبَارِئ እና "አስተናባሪ" "ተንከባካቢ" የተባለበትን "አር ረብ" الْرَبّ እንዲሁ "ባለቤት" የሚለውን "አል ማሊክ" الْمَالِك እንጠቀማለን።
አምላካችን አሏህ በተውሒድ ሙዋሒድ አርጎ ያጽናን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም